መዝሙር 132 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምስለ ቤተ መቅደስ የቀረበ ውዳሴ 1 እግዚአብሔር ሆይ! ልቤ በኩራት የተወጠረ አይደለም፤ ዳዊትን አስታውሰው፤ የተቀበለውን መከራ ሁሉ አትርሳ። 2 እግዚአብሔር ሆይ! ለአንተ የገባውን ቃል ኪዳንና ሁሉን ለምትችል ለያዕቆብ አምላክ ለአንተ እንዲህ ሲል የተሳለውን ስእለት አስታውስ፤ 3-5 “ለእግዚአብሔር የመኖሪያ ስፍራ እስከማዘጋጅ፥ ለያዕቆብ አምላክ ቤት እስከምሠራ ድረስ፥ ወደ ቤት አልገባም፤ ወይም በአልጋ ላይ አልተኛም፤ ዕረፍት ወይም እንቅልፍ አይኖረኝም።” 6 በኤፍራታ ሆነን ስለ ቃል ኪዳኑ ታቦት ሰማን፤ በጁአሪም ምድር አገኘነው። 7 ከዚህ በኋላ “ኑ ወደ እግዚአብሔር ቤት እንሂድ፤ በእግሩ ማረፊያ ሥር እንስገድ” አልን። 8 እግዚአብሔር ሆይ! የኀይልህ መግለጫ ከሆነችው ከቃል ኪዳን ታቦት ጋር ወደምታርፍበት ወደ ቤተ መቅደስ ግባ። 9 ካህናትህ የጽድቅን ሥራ ይሥሩ! ታማኞችህ በደስታ ይዘምሩ! 10 ስለ አገልጋይህ ስለ ዳዊት ስትል መርጠህ የቀባኸውን አትተወው። 11 እግዚአብሔር ለዳዊት እንዲህ ሲል የማይሻር ቃል ኪዳን ገባለት፦ “ከልጆችህ አንዱን አነግሠዋለሁ፤ 12 ልጆችህ ቃል ኪዳኔንና የምሰጣቸውን ትእዛዞች ከጠበቁ ልጆቻቸው ከአንተ በኋላ ለዘለዓለም ይነግሣሉ።” 13 እግዚአብሔር ጽዮንን መርጦአታል፤ መኖሪያውም ሊያደርጋት ይፈልጋል። 14 ይህች የዘለዓለም ማረፊያ ስፍራዬ ናት፤ በዚያች ለመኖር እመኝ ስለ ነበር መኖሪያዬ አደረግኋት። 15 ለጽዮን ምግብዋን አበዛለሁ፤ ድኾችዋንም እስከሚጠግቡ አበላቸዋለሁ። 16 ካህናትዋን በሚያደርጉት ሁሉ እባርካቸዋለሁ፤ በውስጥዋም የሚኖሩ ታማኞች በደስታ ይዘምራሉ። 17 ከዳዊት ዘር ንጉሥ እንዲወጣ አደርጋለሁ፤ የቀባሁትንም ኀያል አደርገዋለሁ። 18 ጠላቶቹ ኀፍረትን እንዲከናነቡ አደርጋቸዋለሁ፤ እርሱ ግን የሚያንጸባርቅ ዘውድ ይቀዳጃል። |