መዝሙር 13 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምርዳታ ለማግኘት የቀረበ ጸሎት 1 እግዚአብሔር ሆይ፥ እስከ መቼ ትረሳኛለህ? የምትረሳኝ ለዘለዓለም ነውን? እስከ መቼስ ከእኔ ትሰወራለህ? 2 ችግርን እስከ መቼ መቻል ይኖርብኛል? እስከ መቼ ልቤ ቀንና ሌሊት በሐዘን ይሞላል? እስከ መቼስ ጠላቴ በእኔ ላይ የበላይነትን ያገኛል? 3 እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ! እባክህ አድምጠኝና መልስ ስጠኝ፤ የሞት እንቅልፍ አንቀላፍቼ እንዳልወድቅ ብርታቱን ስጠኝ። 4 ጠላቶቼ “አሸነፍነው” ብለው እንዲመኩ፥ በእኔም መውደቅ ደስ እንዲላቸው አታድርግ። 5 እኔ በማያቋርጥ ፍቅርህ እተማመናለሁ፤ በማዳንህ እደሰታለሁ። 6 እግዚአብሔር ሆይ! በጎ ነገር ስላደረግህልኝ ለአንተ እዘምራለሁ። |