መዝሙር 124 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምእግዚአብሔር ወገኖቹን የሚጠብቅ መሆኑ 1 እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ባይሆን ምን ይበጀን ነበር? እስራኤል እንዲህ ብሎ ይመልስ፤ 2 “እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ባይሆን ጠላቶቻችን ባጠቁን ጊዜ 3 በታላቅ ቊጣ በእኛ ላይ ተነሥተው ከነሕይወታችን በዋጡን ነበር፤ 4 ጐርፍ በወሰደን፥ ውሃም በሸፈነን ነበር፤ 5 ብርቱ ማዕበልም ባሰጠመን ነበር።” 6 ጠላቶቻችን እንዲደመስሱን ያላደረገ እግዚአብሔር ይመስገን። 7 እንደ ወፍ ከአዳኞች ወጥመድ አምልጠናል፤ ወጥመዱ ተሰበረ፤ እኛም ነጻ ወጣን። 8 ይህንንም ርዳታ ያገኘነው ሰማይንና ምድርን ከፈጠረ ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው። |