መዝሙር 12 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምርዳታ ለማግኘት የቀረበ ጸሎት 1 እግዚአብሔር ሆይ! አንድም ታማኝ ሰው ስላልቀረ እባክህ እርዳን፤ ታማኞች ሰዎች በሰው ዘር መካከል ጠፍተዋል። 2 አንዱ ለአንዱ ውሸትን ይናገራል፤ በሚያቈላምጥ አንደበት የሚናገሩትም በሁለት ልብ ነው። 3 እግዚአብሔር ሆይ! የሚያቈላምጡ ከንፈሮችንና የሚመኩ አንደበቶችን ዝጋ። 4 እነርሱ፦ “በመናገራችን የፈለግነውን እናገኛለን፤ እንደ ፈቀድን እንናገራለን፤ ሊከለክለን የሚችል ማን ነው?” ይላሉ። 5 እግዚአብሔር ግን “ችግረኞች ተጨቊነዋል፤ ስደተኞች በመከራ ብዛት ይቃትታሉ፤ ስለዚህ እነርሱ የሚፈልጉትን ደኅንነት ለመስጠት እነሣለሁ” ይላል። 6 የእግዚአብሔር የተስፋ ቃሎች የታመኑ ናቸው፤ በእሳት ምድጃ ሰባት ጊዜ እንደ ነጠረ ብር የጠሩ ናቸው። 7 እግዚአብሔር ሆይ! አንተ ሁልጊዜ ጠብቀን፤ ክፉ ከሆኑት ከዚህ ዘመን ሰዎች አድነን። 8 ክፉ ነገር በሰዎች ዘንድ በሚመሰገንበት ጊዜ ክፉ ሰዎች በኩራት ይመላለሱበታል። |