መዝሙር 112 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየደግ ሰው ደስታ 1 እግዚአብሔር ይመስገን! እግዚአብሔርን የሚፈራና ትእዛዞቹንም በመፈጸም እጅግ ደስ የሚለው ሰው እንዴት የተባረከ ነው! 2 የደግ ሰው ልጆች በምድር ላይ ብርቱዎች ይሆናሉ፤ የቅኖች ትውልድ ይባረካል። 3 ቤተሰቦቹ ሀብታሞችና ባለጸጎች ይሆናሉ፤ ጽድቅም ለዘለዓለም የእርሱ ይሆናል። 4 ምሕረትና ቸርነት፥ ቅንነትም ለሚያደርግ ለደግ ሰው በጨለማ ውስጥ ብርሃን ይወጣለታል። 5 ሥራውን በቅንነት የሚመራ፥ ለጋሥ የሆነና ሳይሰስት የሚያበድር ኑሮው የተሳካለት ይሆናል። 6 በእውነት እርሱ ምንጊዜም ቢሆን አይናወጥም፤ ጻድቅ ሰው ለዘለዓለም ይታሰባል። 7 እምነቱ ጽኑ ስለ ሆነና በእግዚአብሔርም ስለሚተማመን፥ ክፉ ወሬ አያስደነግጠውም። 8 በእግዚአብሔር ያለው እምነት እጅግ የጸና ስለ ሆነ ከቶ አይፈራም፤ በመጨረሻም የጠላቶቹን ውድቀት ያያል። 9 ለችግረኞች በልግሥና ይሰጣል፤ ቸርነቱም የማያቋርጥ ነው፤ ኀይልንና ክብርን ይጐናጸፋል። 10 ክፉዎች ይህን አይተው ይቈጣሉ፤ ተስፋ በመቊረጥም ጥርሳቸውን ያፋጫሉ፤ የክፉዎችም ምኞት ከንቱ ይሆናል። |