መዝሙር 11 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምበእግዚአብሔር መታመን 1 እግዚአብሔር ከለላዬ ነው፤ እንዴት “እንደ ወፍ ወደ ተራራዎች ሽሽ” ትሉኛላችሁ። 2 ኃጢአተኞች በጨለማ አድብተው ልበቅኖችን ለመግደል ቀስታቸውን ገትረዋል፤ ፍላጻቸውንም በአውታር አዘጋጅተዋል። 3 መሠረቶች ሲፈርሱ ጻድቅ ሰው ምን ማድረግ ይችላል? 4 እግዚአብሔር በተቀደሰ መቅደሱ ነው፤ ዙፋኑም በሰማይ ነው፤ የሰውን ልጆች ይመለከታል። አተኲሮም በማየት ዐይኖቹም ይመረምሩአቸዋል። 5 እግዚአብሔር ጻድቃንንና ኃጢአተኞችን ይፈትናል፤ ዐመፅ የሚወዱትን ግን ይጠላቸዋል። 6 በክፉዎች ላይ የእሳት ፍምንና ዲንን ያዘንባል፤ የሚጋረፍ ነፋስም የእነርሱ ዕድል ፈንታ ነው። 7 እግዚአብሔር ጻድቅ ስለ ሆነ የጽድቅን ሥራ ይወዳል፤ ትክክለኛ ሥራ የሚሠራ ሰው ሁሉ ፊቱን ያያል። |