መዝሙር 108 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየእግዚአብሔርን ርዳታ ለማግኘት የቀረበ ጸሎት ( መዝ. 57፥7-11 ፤ 60፥5-12 ) 1 አምላኬ ሆይ! ልቤ ጽኑ ነው፤ ነቅቼ በሁለንተናዬ እዘምራለሁ፤ በዜማ አመሰግንሃለሁ። 2 በገናዬና መሰንቆዬም ተነሡ፤ እኔም በማለዳ እነሣለሁ። 3 እግዚአብሔር ሆይ! በመንግሥታት መካከል አመሰግንሃለሁ፤ በአሕዛብ መካከል የምስጋና መዝሙር አቀርብልሃለሁ። 4 ዘለዓለማዊው ፍቅርህ ከሰማያት በላይ ነው፤ ታማኝነትህም ወደ ጠፈር ይደርሳል። 5 አምላክ ሆይ! ከሰማያት በላይ ከፍ ከፍ በል፤ ክብርህም ከምድር ሁሉ በላይ ይሁን። 6 የምትወደው ሕዝብህ ይድን ዘንድ፥ ጸሎታችንን ስማ፤ በኀይልህም ታደገን። 7 እግዚአብሔር በመቅደሱ ሆኖ እንዲህ አለ፦ “ድል አድርጌ ሴኬምን እሸነሽናለሁ፤ የሱኮትንም ሸለቆ ለሕዝቤ አከፋፍላለሁ። 8 ገለዓድና ምናሴ የእኔ ናቸው፤ ኤፍሬም የራሴ መከላከያ ቊር ነው፤ ይሁዳም በትረ መንግሥቴ ነው። 9 ሞአብ መታጠቢያዬ ነው፤ ኤዶም የእኔ መሆኑን ለማረጋገጥ ጫማዬን አኖርበታለሁ፤ በፍልስጥኤማውያንም ላይ በድል አድራጊነት እደነፋለሁ።” 10 አምላክ ሆይ! ወደተመሸገችው ከተማ ማን ይወስደኛል? እስከ ኤዶምስ ማን ይመራኛል? 11 አምላክ ሆይ! አንተ ጥለኸናል፤ ከሠራዊታችንም ጋር ወደ ጦር ሜዳ መውጣት ትተሃል። 12 የሰው ርዳታ ከንቱ ነው፤ ስለዚህ ጠላቶቻችንን ድል እንድናደርግ አንተ እርዳን። 13 እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ከሆነ እናሸንፋለን፤ እርሱ ጠላቶቻችንን ያዋርዳቸዋል። |