ዘኍል 36 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምላገቡ ሴቶች የተመደበ ርስት 1 የዮሴፍ ልጅ ምናሴ የወለደው የማኪር ልጅ የገለዓድ ጐሣ የሆኑት የቤተሰብ አለቆች ወደ ሙሴና ወደ ሌሎቹም የእስራኤል ሕዝብ አለቆች ቀርበው እንዲህ አሉ፤ 2 “ምድሪቱን በዕጣ ለእስራኤል ሕዝብ እንድታከፋፍል እግዚአብሔር አንተን ጌታችንን አዞሃል፤ እንዲሁም የዘመዳችንን የጸሎፍሐድን ድርሻ ለሴቶች ልጆቹ እንድትሰጥ አዞሃል፤ 3 ነገር ግን እነርሱ ከሌላ ነገድ የሆኑ ወንዶችን ቢያገቡ ርስታቸው የዚያ ነገድ መሆን እንደሚገባውና የእኛም ድርሻ ሊቀነስ እንደሚችል አስታውስ። 4 ንብረት በሚመለስበት ዓመት የተሸጠ ንብረት ሁሉ ለባለቤቱ በሚመለስበት ጊዜ የጸሎፍሐድ ሴቶች ልጆች ርስት አግብተው ወደ ሄዱበት ነገድ ለዘለቄታው ተጨማሪ ሆኖ ይተላለፋል፤ ይህም በእኛ ነገድ ይዞታ ላይ ጒድለትን ያስከትላል።” 5 ስለዚህ ሙሴ ለእስራኤል ሕዝብ ከእግዚአብሔር የተቀበለውን ትእዛዝ እንዲህ ሲል አስተላለፈ፤ “የምናሴ ነገድ የተናገሩት ሁሉ ትክክል ነው፤ 6 ስለዚህ እግዚአብሔር ‘የጸሎፍሐድ ሴቶች ልጆች ከገዛ ነገዳቸው ወገን እስከ ሆነ ድረስ የወደዱትን ማግባት ይችላሉ’ ይላል። 7 በዚህ ዐይነት የማንኛውም እስራኤላዊ ርስት ወደ ሌላ ነገድ አይተላለፍም፤ ከገዛ ነገዱ ጋር የተያያዘ ይሆናል፤ 8 በእስራኤላዊ ነገድ መካከል ርስት የተካፈለች ማንኛይቱም ሴት ከዚያው ነገድ የሆነ ወንድ ማግባት ይኖርባታል፤ በዚህ ዐይነት እያንዳንዱ እስራኤላዊ የቀድሞ አባቶቹን ርስት በይዞታው ማቈየት ይችላል።” 9 ስለዚህ ያም ርስት ከአንዱ ነገድ ወደ ሌላው ነገድ ሊተላለፍ አይቻልም፤ እያንዳንዱ ነገድ የራሱን ርስት እንደ ያዘ ይኖራል። 10 የጸሎፍሐድ ሴቶች ልጆች እግዚአብሔር ሙሴን እንዳዘዘው አደረጉ። 11 የጸሎፍሐድ ሴቶች ልጆች ማሕላ፥ ቲርጻ፥ ሖግላ፥ ሚልካ እና ኖዓ ከአባታቸው ወንድሞች ልጆች ጋር ተጋቡ። 12 ከዮሴፍ ልጅ ከምናሴ ነገድ ጐሣዎች መካከል ባሎችን አገቡ፤ ርስታቸውም በአባታቸው ነገድ የጸና ሆነ። 13 ለእስራኤላውያን በኢያሪኮ ትይዩ ከዮርዳኖስ ወንዝ ባሻገር ባለው በሞአብ ሜዳ ላይ በነበሩበት ጊዜ እግዚአብሔር በሙሴ አማካይነት የሰጣቸው ትእዛዞችና ሥርዓቶች እነዚህ ናቸው። |