ዘኍል 35 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምለሌዋውያን የተመደቡ ከተሞች 1 በኢያሪኮ ትይዩ ከዮርዳኖስ ወንዝ ማዶ ባለው በሞአብ ሜዳ ላይ እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ 2 “እስራኤላውያን ድርሻቸው ከሆነ ርስት ለሌዋውያን የሚኖሩባቸውን ከተሞችንና በከተሞቹም ዙሪያ የግጦሽ መሬት እንዲሰጡአቸው ንገር። 3 እነዚህም ከተሞች የሌዋውያን ይዞታ ሆነው እነርሱ ይኖሩባቸዋል፤ የግጦሽ መሬቱም ለከብቶቻቸውና ለሌሎች እንስሶቻቸው ይሆናል። 4 የግጦሽ መሬቱ ከከተማው ቅጽር ግንብ በሁሉ አቅጣጫ እስከ አራት መቶ ኀምሳ ሜትር ይስፋ። 5 በዚህም ዐይነት ከተማው በመካከል ሆኖ በአራቱም አቅጣጫ ከማእዘን እስከ ማእዘን የሚኖረው ርቀት ዘጠኝ መቶ ሜትር ይሆናል። 6 ማናቸውም ሰው፥ በስሕተት ሰውን ቢገድል ሸሽቶ የሚጠጋባቸው ስድስት ከተሞችን ለሌዋውያን ትሰጣላችሁ፤ በተጨማሪም አርባ ሁለት ከተሞችን፥ 7 ከነግጦሽ መሬታቸው ትሰጣላችሁ፤ በዚህም ዐይነት በአጠቃላይ አርባ ስምንት ከተሞች ይኖራቸዋል። 8 ከእስራኤላውያን ይዞታ እንደየርስታቸው መጠን፥ ብዛት ካላቸው ነገዶች ብዙ ከተሞችን፥ አነስ ካሉ ነገዶች ጥቂት ከተሞችን ወስደህ ለሌዋውያን ስጥ።” የመማጠኛ ከተሞች ( ዘዳ. 19፥1-13 ፤ ኢያሱ 20፥1-9 ) 9 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው፦ 10 “ለእስራኤላውያን እንዲህ በላቸው፦ የዮርዳኖስን ወንዝ ተሻግራችሁ ወደ ከነዓን ምድር ስትገቡ፥ 11 አንድ ሰው ባለማወቅ ተሳስቶ ሰው ቢገድል አምልጦ የሚደበቅበት የመማጠኛ ከተሞችን ምረጥ። 12 በዚያም የበቀል እርምጃ ለመውሰድ ከሚፈልግ ከሟቹ ዘመድ ሊሰወር ይችላል፤ በግድያ ወንጀል የተከሰሰ ሰው ለፍርድ ሳይቀርብ መገደል የለበትም፤ 13 ስድስት ከተሞችን ምረጡ፤ 14 ከእነርሱም ሦስቱ ከዮርዳኖስ ወንዝ በስተምሥራቅ፥ ሦስቱ ደግሞ በከነዓን ምድር ይሁኑ፤ 15 እነርሱም ለእስራኤላውያንና ለጊዜውም ሆነ ለዘለቄታው በእስራኤል ለሚኖሩ መጻተኞች የመማጠኛ ከተሞች ይሆናሉ፤ ባለማወቅ ተሳስቶ ሰው የሚገድል ማንኛውም ግለሰብ ከእነርሱ ወደ አንዱ አምልጦ መጠጋት ይችላል። የነፍስ ግድያ በቀል 16 “አንድ ሰው ሌላውን ሰው በብረት መሣሪያ እስኪሞት ድረስ ቢመታው ያ ሰው ነፍሰ ገዳይ ነው፤ ነፍሰ ገዳዩም ይገደል። 17 አንድ ሰው ሌላውን ሰው ሊገድል በሚችል ድንጋይ ቢመታውና ያ የተመታው ሰው ቢሞት ያ የመታው ሰው ነፍሰ ገዳይ ነው፤ ነፍሰ ገዳዩም ይገደል፤ 18 አንድ ሰው ሌላውን ሰው ሊገድል በሚችል የእንጨት መሣሪያ መትቶ ቢገድለው ያ ሰው ነፍሰ ገዳይ ነው፤ ነፍሰ ገዳዩም ይገደል። 19 የሟቹ ቅርብ ዘመድ ነፍሰ ገዳዩን የመግደል መብት ይኖረዋል፤ ስለዚህ ባገኘው ጊዜ ሊገድለው ይችላል። 20 “አንድ ሰው ሌላውን ሰው በጥላቻ ቢገፋው ወይም ሸምቆ አንዳች ነገር ቢወረውርበትና ይህ አድራጎቱ ሞትን ቢያስከትል፥ 21 ወይም በጠላትነት ተነሣሥቶ በቡጢ በመምታት ቢገድለው የግድያ ወንጀል ስለ ፈጸመ መገደል አለበት፤ የሟች ቅርብ ዘመድ ነፍሰ ገዳዩን የመግደል መብት ይኖረዋል፤ ስለዚህ ባገኘው ጊዜ ሊገድለው ይችላል። 22 “ነገር ግን አንድ ሰው ገፍትሮ በመጣልም ሆነ አንዳች ነገር በላዩ በመወርወር ሌላ ሰው የሚገድለው ከጥላቻ የተነሣ ሳይሆን በድንገት ተሳስቶ ከሆነ፤ 23 ወይም ጠላትነት ሳይኖርና ሰውን ለመጒዳት ታስቦ ሳይሆን ሞትን የሚያስከትል ድንጋይ ወርውሮ ሳይታሰብ በሌላ ሰው ላይ ቢያርፍና ሞትን ቢያስከትል፥ 24 እንዲህ ያለው ሁኔታ በሚፈጸምበት ጊዜ ማኅበሩ በገዳዩና በተበቃዩ መካከል ፍርድ የሚሰጠው በሚከተለው ሥርዓት መሠረት ነው። 25 ማኅበሩ በግድያ ወንጀል የተከሰሰውን ሰው ከተበቃይ እጅ በመታደግ አምልጦ ወደነበረበት ወደ መማጠኛ ከተማዋ መመለስ አለበት፤ በዘመኑ ሊቀ ካህናት የሆነው ሰው እስከሚሞትበት ድረስ እዚያው መቈየት ይኖርበታል። 26 በግድያ ወንጀል የተከሰሰው ሰው አምልጦ ከመማጸኛው ከተማ ለቆ ከሄደ፥ 27 የሟች ዘመድ አግኝቶ ከገደለው የዚህ ዐይነቱ የበቀል እርምጃ በነፍሰ ገዳይነት አያስጠይቅም። 28 በግድያ ወንጀል የተከሰሰው ሰው ሊቀ ካህናቱ እስኪሞት ድረስ በዚያው በመማጸኛ ከተማ መቈየት አለበት፤ ሊቀ ካህናቱ ከሞተ በኋላ ግን ወደ ቤቱ መመለስ ይችላል፤ 29 ይህ ሕግና ሥርዓት በምትኖሩበት አገር ሁሉ ለእናንተና ለዘሮቻችሁ መመሪያ ይሆናል። 30 “በግድያ ወንጀል የተከሰሰ ማንኛውም ሰው የሞት ፍርድ ሊበየንበት የሚችለው ሁለት ወይም ከሁለት በላይ የሆኑ ሰዎች የመሰከሩበት እንደ ሆነ ነው፤ የአንድ ሰው ምስክርነት ግን ለግድያ ወንጀል የተከሰሰውን ሰው ሊያስጠይቀው አይችልም። 31 ማንኛውም ነፍሰ ገዳይ በሞት መቀጣት አለበት፤ ገንዘብ በመክፈል ከዚህ ቅጣት ሊያመልጥ አይችልም። 32 አንድ ሰው ወደ መማጸኛ ከተማ ሸሽቶ ቢያመልጥ ሊቀ ካህናቱ ከመሞቱ በፊት ወደ ቤቱ መመለስ ይችል ዘንድ ገንዘብ እንዲከፍል አትፍቀዱለት። 33 ይህን ብታደርጉ የምትኖሩበትን ምድር ታረክሳላችሁ፤ የነፍስ ግድያ ወንጀል ምድሪቱን ያረክሳል፤ ስለዚህ የነፍሰ ገዳዩ ደም ካልፈሰሰ በቀር ምድሪቱን ከደም ለማንጻት የሚፈጸም ሌላ ሥርዓት የለም። 34 እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ስለ ሆንኩና በእናንተ በእስራኤል ሕዝብም መካከል ስለምኖር የእኔ መኖሪያ የሆነውንና እናንተ የምትኖሩበትን ምድር አታርክሱ።” |