ዘኍል 31 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምበምድያማውያን ላይ የተደረገ ጦርነት 1 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 2 “በእስራኤል ሕዝብ ላይ ስለ ፈጸሙት በደል ምድያማውያንን ቅጣ፤ ይህንንም ካደረግህ በኋላ አንተ ትሞታለህ።” 3 ስለዚህ ሙሴ ሕዝቡን እንዲህ አለ፦ “ምድያማውያን በእግዚአብሔር ላይ ስለ ፈጸሙት በደል አደጋ ጥላችሁ ትበቀሉአቸው ዘንድ ለጦርነት ተዘጋጁ፤ 4 ከእያንዳንዱ የእስራኤል ነገድ አንዳንድ ሺህ ወንዶችን መርጣችሁ ወደ ጦርነቱ ላኩ።” 5 ስለዚህ ከብዙ ሺህ እስራኤላውያን መካከል ከያንዳንዱ ነገድ አንዳንድ ሺህ ተውጣጥቶ ዐሥራ ሁለት ሺህ የታጠቀ ሠራዊት ለጦርነት ተዘጋጀ። 6 ሙሴም ከየነገዱ አንዳንድ ሺህ ሰው በካህኑ በአልዓዛር ልጅ በፊንሐስ መሪነት ወደ ጦርነት ላካቸው፤ ፊንሐስም ከመቅደሱ አንዳንድ ንዋየ ቅድሳትንና ለጦርነት መቀስቀሻ (ክተት) የሚሆን መለከት በእጁ ይዞ ነበር። 7 እነርሱም እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት በምድያማውያን ላይ አደጋ ጥለው ወንዶቹን በሙሉ ገደሉ። 8 አምስቱንም የምድያም ነገሥታት ኤዊን፥ ሬቄምን፥ ጹርን፥ ሑርንና ሬባዕን ገደሉ፤ የቢዖርን ልጅ በለዓምንም ገደሉት። 9 የእስራኤል ሕዝብ ምድያማውያን ሴቶችንና ሕፃናትን ማረኩ፤ የከብት፥ የበግና የፍየል መንጋዎቻቸውን ወሰዱ፤ ሀብታቸውን ሁሉ በዘበዙ፤ 10 ከተሞቻቸውንና የሰፈሩበትን ቦታ ሁሉ አቃጠሉ፤ 11 እስረኞችንና እንስሶችን ሳይቀር የማረኩትን ነገር ሁሉ ሰብስበው 12 ከዮርዳኖስ ማዶ በኢያሪኮ ትይዩ በሞአብ ሜዳ ላይ ሰፍረው ወደነበሩት ወደ ሙሴና ወደ አልዓዛር እንዲሁም ወደ መላው ማኅበር አመጡአቸው። የሠራዊቱ መመለስ 13 ሙሴ፥ አልዓዛርና ሌሎቹም የማኅበሩ መሪዎች ሠራዊቱን ለመቀበል ከሰፈር ወጡ፤ 14 ሙሴ ግን ከጦርነት በተመለሱት በጭፍራ አለቆች፥ በሻለቆችና በመቶ አለቆች ላይ ተቈጣ፤ 15 እንዲህም ሲል ጠየቃቸው፦ “ሴቶችን በሙሉ በሕይወት ያስቀራችሁት ለምንድን ነው? 16 በፔዖር ሳለን የበለዓምን ምክር ተቀብለው ሕዝቡ በእግዚአብሔር ላይ ያላቸውን እምነት እንዲተዉ ያደረጉ ሴቶች መሆናቸውን ዘነጋችሁን? በእግዚአብሔር ሕዝብ ላይ የአባር ቸነፈር መቅሠፍት ያመጣም ያ ስሕተት ነበር። 17 ስለዚህ አሁን እያንዳንዱን ወንድ ልጅና እያንዳንዲቱን ከወንድ ጋር የተገናኘች ሴት ግደሉ። 18 ነገር ግን ከወንድ ጋር ያልተገናኙትን ልጃገረዶቹን በሕይወት እንዲኖሩ አድርጋችሁ ለራሳችሁ አስቀሩ። 19 ከእናንተ መካከል ሰው የገደለ ወይም ሬሳ የነካ ሁሉ ለሰባት ቀን ከሰፈር ውጪ ይቈይ፤ በሦስተኛውና በሰባተኛው ቀን ራሳችሁንና የማረካችኋቸውን ሴቶች አንጹ። 20 እንዲሁም ማንኛውንም ልብስ ወይም ከቈዳ፥ ከፍየል ጠጒር ወይም ከእንጨት የተሠራ ነገር ሁሉ አጽዱ።” 21 ካህኑ አልዓዛር ከዘመቻ ለተመለሱት ወንዶች እንዲህ አለ፤ “እግዚአብሔር ለሙሴ የሰጠው የሕጉ ሥርዓት መመሪያዎች እነዚህ ናቸው፦ 22-23 እንደ ወርቅ፥ ብር፥ ነሐስ፥ ብረት፥ ቆርቆሮ ወይም እርሳስ የመሳሰሉ እሳት የማይጐዳቸው ነገሮች በእሳት ውስጥ አልፈው መጥራት ይኖርባቸዋል፤ እሳት መቋቋም የማይችለውን ነገር ሁሉ ለመንጻት ሥርዓት በተመደበው ውሃ ታጠሩታላችሁ። 24 በሰባተኛው ቀን ልብሳችሁን ታጥባላችሁ፤ ከዚያም በኋላ የነጻችሁ ስለምትሆኑ ወደ ሰፈር መግባት ይፈቀድላችኋል።” የምርኮ ክፍያ 25 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 26 “አንተና አልዓዛር ከቀሩት የማኅበሩ መሪዎች ጋር በመሆን እስረኞችንና እንስሶችን ጭምር በምርኮ የተገኘውን ማንኛውንም ነገር ቊጠሩ። 27 በሁለት መድባችሁም አንደኛውን ክፍል ወደ ጦርነት ለሄዱ ወታደሮች፥ ሁለተኛውን ክፍል ለቀሩት የማኅበሩ አባላት ስጡ። 28 ለወታደሮቹ ከተመደበው ክፍል፥ ከአምስት መቶ እስረኞች አንዱን፥ እንዲሁም ከከብቱ፥ ከአህዮቹ፥ ከበጎቹና ከፍየሎቹ ከአምስት መቶው አንዱን እጅ ለእኔ ለእግዚአብሔር መባ አድርጋችሁ ለዩ፤ 29 ለእኔ ለእግዚአብሔር ልዩ ስጦታ በማድረግም ለካህኑ ለአልዓዛር ስጡት። 30 ለቀሩት የማኅበሩ አባላት ከተሰጠውም ክፍል ከኀምሳ እስረኞች አንዱን፥ በዚሁ መጠን ከከብቱ፥ ከአህዮቹ፥ ከበጎቹና ከፍየሎቹ ለይታችሁ ለተቀደሰው ድንኳን ኀላፊዎች ለሆኑት ሌዋውያን ስጡ።” 31 ሙሴና አልዓዛርም እግዚአብሔር ያዘዛቸውን ሁሉ አደረጉ። 32-35 ለራሳቸው ካስቀሩት ጭምር ወታደሮቹ የማረኩት ንብረት ዝርዝር የሚከተለው ነው፦ ስድስት መቶ ሰባ አምስት ሺህ በጎች፥ ሰባ ሁለት ሺህ የቀንድ ከብቶች፥ ሥልሳ አንድ ሺህ አህዮችና፥ ሥልሳ ሁለት ሺህ ከወንድ ጋር ግንኙነት ያላደረጉ ሴቶች። 36 ከጠቅላላው ምርኮ ግማሹ፥ ወደ ጦርነት ዘምተው ለተመለሱ ሰዎች የተከፈለ ሲሆን፥ እነኚህም ሦስት መቶ ሠላሳ ሰባት ሺህ አምስት መቶ በጎች ነበሩ። 37 ከእነዚህም ስድስት መቶ ሰባ አምስቱ ለእግዚአብሔር መባ ሆነው የተሰጡ ነበሩ፤ 38 ለወታደሮቹ የተሰጡት የቀንድ ከብቶች ብዛት ሠላሳ ስድስት ሺህ ሲሆን ከእነርሱም ሰባ ሁለቱ ለእግዚአብሔር መባ ሆነው የተሰጡ ነበሩ፤ 39 ለወታደሮቹ የተሰጡት አህዮች ሠላሳ ሺህ አምስት መቶ ሲሆኑ ከእነዚህም ሥልሳ አንዱ ለእግዚአብሔር መባ ሆነው የተሰጡ ነበሩ፤ 40 ለወታደሮቹ የተሰጡት ከወንድ ጋር ግንኙነት ያላደረጉ ሴቶች ዐሥራ ስድስት ሺህ ሲሆኑ፥ ከእነዚህም ሠላሳ ሁለቱ ለእግዚአብሔር አገልግሎት የተለዩ ነበሩ። 41 ስለዚህም ሙሴ እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት መባውን ለእግዚአብሔር ልዩ ስጦታ በማድረግ ለአልዓዛር ሰጠው። 42 የማኅበሩ አባሎች ድርሻ ከወታደሮቹ ድርሻ ጋር ተመሳሳይና እኩል ነበር፤ 43 ይኸውም ሦስት መቶ ሠላሳ ሰባት ሺህ አምስት መቶ በጎች፥ 44 ሠላሳ ስድስት ሺህ የቀንድ ከብቶች፥ 45 ሠላሳ ሺህ አምስት መቶ አህዮችና፥ 46 ዐሥራ ስድስት ሺህ ከወንድ ጋር ያልተገናኙ ሴቶች ነበሩ። 47 ከዚህም ድርሻ ሙሴ ከኀምሳው አንድ እስረኛ፥ ከኀምሳው አንድ እንስሳ ወስዶ እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት በእግዚአብሔር ድንኳን ላይ ኀላፊነት ላላቸው ለሌዋውያን ሰጠ። 48 ከዚህ በኋላ የሠራዊቱ አዛዦች የነበሩት የሺህ አለቆችና የመቶ አለቆች ወደ ሙሴ ቀርበው እንዲህ አሉ፤ 49 “እኛ አገልጋዮችህ፥ በእኛ ትእዛዝ ሥር የነበሩትን ወታደሮች ሁሉ ቈጥረናል፤ ከእነርሱ አንድም የጐደለ የለም። 50 ስለዚህ እያንዳንዳችን ያገኘነውን የወርቅ ጌጣጌጥ ማለትም የእግር አልቦውን፥ የእጅ አንባሩን፥ የጣት ቀለበቱን፥ የጆሮ ጒትቻውንና የአንገት ድሪውን ሁሉ ለኃጢአታችን ማስተስረያ ለእግዚአብሔር ቊርባን ይሆን ዘንድ ይዘን መጥተናል።” 51 ሙሴና አልዓዛር በጌጣጌጥ መልክ ተሠርቶ የነበረውን ወርቅ ሁሉ ተቀበሉ። 52 ከሺህ አለቆችና ከመቶ አለቆች ለጌታ የቀረበው የወርቅ መባ ክብደት ሁለት መቶ ኪሎ ያኽል ነበር። 53 የጦር ሹማምንት ያልሆኑት ወታደሮች ግን ያመጡትን ምርኮ ለራሳቸው አስቀሩ። 54 ስለዚህ ሙሴና ካህኑ አልዓዛር ወርቁን ከሺህ አለቆችና ከመቶ አለቆች ተቀብለው ለእስራኤላውያን መታሰቢያ ይሆን ዘንድ ወደ መገናኛው ድንኳን አመጡት። |