ዘኍል 30 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምስለ ስእለት የተሰጠ መመሪያ 1 ሙሴ ለእስራኤል የነገድ መሪዎች አላቸው፤ እግዚአብሔር ያዘዘው ነገር ይህ ነው፦ 2 አንድ ሰው ለእግዚአብሔር አንድ ነገር ለመስጠት ቢሳል ወይም ከአንድ ነገር ራሱን ለመከልከል በመሐላ ቃል ቢገባ፥ አደርጋለሁ ያለውን ሁሉ መፈጸም አለበት እንጂ የሰጠውን የተስፋ ቃል ማስቀረት አይገባውም። 3 ገና በአባትዋ ቤት የምትኖር ልጃገረድ ለእግዚአብሔር አንድ ነገር ለመስጠት ብትሳል፥ ወይም ከአንድ ነገር ራስዋን ለመከልከል ቃል ብትገባ፥ 4 አባትዋ ስለዚህ ጉዳይ ሰምቶ ካልተቃወማት በቀር ስእለትዋን ወይም የገባችውን ቃል መፈጸም አለባት። 5 አባትዋ ስለ ጉዳዩ ሰምቶ ስእለትዋን እንዳትፈጽም የሚቃወማት ከሆነ ግን ስእለትዋን የመፈጸም ግዴታ አይኖርባትም፤ ስእለትዋን ለመፈጸም ያልቻለችው አባትዋ ስለ ከለከላት በመሆኑ እግዚአብሔር ይቅርታ ያደርግላታል። 6 ባል ያላገባች ሴት አስባም ሆነ በግድየለሽነት ስእለት ካደረገች ወይም ከአንድ ነገር ለመከልከል ቃል ከገባች በኋላ ባል ብታገባ፥ 7 ባልዋ ስለ ጉዳዩ ሰምቶ ካልከለከላት በቀር ስእለትዋንም ሆነ የገባችውን ቃል መፈጸም አለባት። 8 ባልዋ ስለ ጉዳዩ ሰምቶ ከከለከላት ግን የመፈጸም ግዴታ የለባትም፤ ስእለትዋን ለመፈጸም ያልቻለችው ባልዋ ስለ ከለከላት በመሆኑ እግዚአብሔር ይቅርታ ያደርግላታል። 9 ባልዋ የሞተባት ሴት ወይም ከባልዋ የተፋታች ሴት ማንኛቸውንም ስእለት ሆነ ወይም ከአንድ ነገር ለመከልከል የገባችውን ቃል መፈጸም አለባት። 10 ባል ያገባች ሴት ስእለት ብትሳል ወይም ከአንድ ነገር ለመከልከል በመሐላ ቃል ብትገባ፥ 11 ባልዋ ስለ ጉዳዩ ሰምቶ ካልተቃወማት በቀር ስእለትዋንም ሆነ ከአንድ ነገር ለመከልከል የገባችውን መሐላ መፈጸም ይኖርባታል፤ 12 ባልዋ ስለ ጉዳዩ ሰምቶ ስእለትዋን እንዳትፈጽም ቢከለክላት ግን የመፈጸም ግዴታ የለባትም፤ ስእለትዋን ለመፈጸም ያልቻለችው ባልዋ ስለ ከለከላት በመሆኑ እግዚአብሔር ይቅርታ ያደርግላታል። 13 ባልዋ ማንኛውንም ስእለት ሆነ መሐላ የመፍቀድ ወይም የመቃወም መብት አለው። 14 ነገር ግን ባልዋ ስለ ጉዳዩ በሰማበት ቀን ማግስት ምንም ተቃውሞ ያላቀረበ ከሆነ ስእለትዋንና በመሐላ የገባችውን ቃል ሁሉ መፈጸም ይኖርባታል፤ ስለ ጉዳዩ በሰማበት ቀን ተቃውሞ አለማቅረቡ ፈቃደኛ መሆኑን ያረጋግጣል። 15 ነገር ግን ቈየት ብሎ ስእለቱን የሚቃወም ከሆነ ለስእለቱ አለመፈጸም ኀላፊ ይሆናል። 16 ሳታገባ በአባትዋ ቤት የምትኖር ልጃገረድ ወይም ያገባች ሴት ስእለት ወይም የመሐላ ቃል በምትገባበት ጊዜ የአባት ወይም የባል ኀላፊነትንና መብትን በተመለከተ እግዚአብሔር ለሙሴ የሰጠው ደንብ ይህ ነው። |