ዘኍል 3 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየአሮን ወንዶች ልጆች 1 እግዚአብሔር ሙሴን በሲና ተራራ ላይ ባነጋገረው ጊዜ የአሮንና የሙሴ ትውልድ ይህ ነበር። 2 አሮን አራት ወንዶች ልጆች ነበሩት፤ እነርሱም በኲሩ ናዳብ ሲሆን የቀሩት አቢሁ፥ አልዓዛርና ኢታማር ነበሩ። 3 እነዚህም በክህነት እንዲያገለግሉ ተቀብተው ነበር። 4 ነገር ግን ከእነርሱ ውስጥ ናዳብና አቢሁ በሲና በረሓ በእግዚአብሔር ፊት ያልተቀደሰ እሳት ጭረው በማቅረባቸው ተቀሥፈው ሞቱ፤ እነርሱም ልጆች አልነበሩአቸውም፤ ስለዚህም አልዓዛርና ኢታማር ብቻ አባታቸው አሮን በሕይወት በነበረበት ዘመን ሁሉ በክህነት ያገለግሉ ነበር። የሌዋውያን ተግባር 5 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 6 “የሌዊን ነገድ አቅርበህ ለካህኑ አሮን አገልጋዮች እንዲሆኑ መድባቸው፤ 7 እነርሱም አሮንንና መላውን ማኅበር በመገናኛው ድንኳን በማገልገል ተግባራቸውን ይፈጽማሉ። 8 በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ለሚገኙ መገልገያ ዕቃዎች ኀላፊዎች ይሆናሉ። እስራኤላውያንንም በድንኳኑ ውስጥ በማገልገል ተግባራቸውን ይፈጽማሉ። 9 ከእስራኤላውያን ሁሉ ተለይተው ለአሮንና ለልጆቹ ያገለግሉ ዘንድ ሌዋውያንን መድባቸው። 10 የክህነቱንም ሥራ ያከናውኑ ዘንድ አሮንንና ልጆቹን ሹማቸው፤ ከእነርሱ በቀር ሌላ ሰው ይህን ሥራ ለማከናወን ቢሞክር በሞት ይቀጣ።” 11 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 12-13 “እነሆ ሌዋውያን የእኔ አገልጋዮች ናቸው፤ የግብጻውያንን በኲር ሁሉ በገደልኩ ጊዜ ከያንዳንዱ እስራኤላዊ የሚወለደውን በኲርና ከእንስሶቹም በኲር የሆነውን ሁሉ ለእኔ የተለየ እንዲሆን አድርጌ ነበር፤ አሁን ግን በኲር ሆነው የሚወለዱትን ወንዶች ልጆች የራሴ በማድረግ ፈንታ ሌዋውያንን መርጬአለሁ፤ እነርሱ የእኔ አገልጋዮች ይሆናሉ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።” የሌዋውያን መቈጠር 14 እግዚአብሔር ሙሴን በሲና ተራራ ላይ እንዲህ አለው፦ 15 “ሌዋውያንን በየወገናቸውና በየቤተሰባቸው መድበህ ቊጠር፤ ከተወለደ አንድ ወር የሞላውንና ከዚያ በላይ የሆነውን ወንድ ሁሉ ቊጠር።” 16 ሙሴም በእግዚአብሔር ቃል እንደታዘዘው ቈጠረ። 17 ሌዊ ሦስት ወንዶች ልጆች ነበሩት፤ እነርሱም ጌርሾን፥ ቀዓትና ሜራሪ ይባላሉ። 18 የጌርሾንም ወንዶች ልጆች ሊብኒና ሺምዒ ይባሉ ነበር፤ 19 የቀዓትም ወንዶች ልጆች ዓምራም፥ ይጽሐር፥ ኬብሮንና ዑዚኤል ይባሉ ነበር። 20 የሜራሪ ወንዶች ልጆች ማሕሊናና ሙሺ ይባሉ ነበር፤ እነዚህም በየስማቸው የቤተሰብ አባቶች ነበሩ። 21 የሊብኒና የሺምዒ ቤተሰቦች በጌርሾን ጐሣ ውስጥ ተጠቃለው ነበር፤ 22 ዕድሜው አንድ ወር ከሆነው ሕፃን አንሥቶ የተመዘገቡት የወንዶች ብዛት ሰባት ሺህ አምስት መቶ ነበር። 23 የጌርሾናውያን ወገን የሚሰፍረው ከድንኳኑ በስተጀርባ በምዕራብ በኩል ነበር። 24 የጌርሾናውያን ወገን መሪ የላኤል ልጅ ኤልያሳፍ ነበር። 25 በመገናኛው ድንኳን የጌርሾን ልጆች ኀላፊነት የነበረው በመገናኛው ድንኳን፥ ከውጪና ከውስጥ በኩል ባለው መሸፈኛ፥ በመግቢያው ደጃፍ መጋረጃ፥ 26 በቅጥር ግቢው መጋረጃዎች፥ በድንኳኑና በመሠዊያው ዙሪያ ባለው የቅጥር ግቢው በር መጋረጃ፥ በአውታሮቹ፥ እንዲሁም ለእነርሱ መጠቀሚያ በሚሆኑ ዕቃዎች ሁሉ ላይ ነው። 27 የዓምራም፥ የይጽሃር፥ የኬብሮንና የዑዚኤል ቤተሰቦች በቀዓት ጐሣ ውስጥ ተጠቃለው ነበር፤ 28 አንድ ዓመትና ከዚያም በላይ የሆኑት ወንዶች ቊጥር ስምንት ሺህ ስድስት መቶ ነበር፤ እነርሱም የመገናኛውን ድንኳን ይጠብቁት ነበር። 29 የቀዓት ልጆች ቤተሰቦች የሚሰፍሩት በድንኳኑ በስተደቡብ በኩል ነበር። 30 የቀዓትም ጐሣ መሪ የዑዚኤል ልጅ የሆነው ኤሊጻፋን ነበር። 31 የእነርሱም ኀላፊነት በቃል ኪዳኑ ታቦት፥ በገበታው፥ በመቅረዙ፥ በመሠዊያዎቹ፥ ካህናቱ በተቀደሰው ስፍራ በሚገለገሉባቸው ንዋያተ ቅድሳት፥ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን በሚያስገባው መጋረጃ ላይ ሲሆን፥ በአጠቃላይ እነዚህን ነገሮች በሚመለከት አገልግሎት ኀላፊነቱ የእነርሱ ነበር። 32 የሌዋውያን ሁሉ አለቃ የካህኑ የአሮን ልጅ አልዓዛር ነበር፤ እርሱ በተቀደሰው ስፍራ ለሚያገለግሉት ሰዎች ሁሉ የበላይ ኀላፊ ነበር። 33 የማሕሊና የሙሺ ቤተሰቦች በሜራሪ ጐሣ ውስጥ ተጠቃለው ነበር። እነዚህ የሜራሪ ቤተሰቦች ናቸው። 34 ከእነርሱም ዕድሜው አንድ ወር ከሆነው ሕፃን አንሥቶ፥ የተቈጠሩት የወንዶች ብዛት ስድስት ሺህ ሁለት መቶ ነበር፤ 35 የሜራሪ ጐሣ መሪ የጹርኤል ልጅ አቢኤል ነበር፤ እነርሱም የሚሰፍሩት በድንኳኑ በስተሰሜን ነበር። 36 የእነርሱም ኀላፊነት በድንኳኑ ተራዳዎችና በመወርወሪያዎቻቸው፥ በምሰሶቹና ምሰሶቹ በሚቆሙባቸው እግሮች፥ እንዲሁም በሌሎች የመገልገያ ዕቃዎች ላይ ሲሆን፥ በአጠቃላይ እነዚህን ነገሮች በሚመለከት ሥራ ኀላፊነቱ የእነርሱ ነበር። 37 እንዲሁም በቅጥር ግቢው ዙሪያ ባሉት፥ ምሰሶች፥ የተራዳ እግሮች፥ ካስማዎችና አውታሮች ላይ ኀላፊነት ነበራቸው። 38 በመገናኛው ድንኳን በስተምሥራቅ፥ በፀሐይ መውጫ በኩል የሚሰፍሩት ሙሴ አሮንና የአሮን ልጆች ነበሩ፤ በመቅደሱ ውስጥ ስለ እስራኤል ሕዝብ ለሚፈጸም ማንኛውም ዐይነት የአገልግሎት ሥነ ሥርዓት ኀላፊዎች እነርሱ ነበሩ፤ ማንም ሌላ ሰው ወደ መቅደሱ ቢቀርብ በሞት ይቀጣል። 39 እግዚአብሔር ባዘዛቸው መሠረት ሙሴና አሮን ዕድሜው አንድ ወር ከሆነው ሕፃን አንሥተው በየቤተሰባቸው የመዘገቡአቸው ሌዋውያን ወንዶች በሙሉ ኻያ ሁለት ሺህ ነበሩ። ሌዋውያን በኲር ሆነው ለሚወለዱ እስራኤላውያን ምትክ መሆናቸው 40 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ “በኲር ሆነው የተወለዱትን የእስራኤላውያን ወንዶች ልጆች ዕድሜአቸው አንድ ወርና ከዚያም በላይ የሆነውን ቈጥረህ በየስማቸው መዝግብ፤ 41 በእስራኤል የበኲር ልጆች ሁሉ ምትክ ሌዋውያንን እንዲሁም በእስራኤላውያን የእንስሶች በኲር ሁሉ ምትክ የሌዋውያንን እንስሶች ውሰድ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።” 42 ሙሴም እግዚአብሔር እንዳዘዘው ከእስራኤላውያን መካከል በኲር ሆኖ የተወለደውን ሁሉ ቈጠረ። 43 ዕድሜአቸው አንድ ወርና ከዚያ በላይ የሆናቸውን በኲር ሆነው የተወለዱትን ወንዶች ሁሉ በስማቸው ዝርዝር መሠረት ኻያ ሁለት ሺህ ሁለት መቶ ሰባ ሦስት ነበር። 44 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ 45 “እንግዲህ በኲር ሆነው በሚወለዱት እስራኤላውያን ወንዶች ልጆች ምትክ ሌዋውያንን ለእኔ ለይልኝ፤ እንዲሁም በኲር ሆነው በሚወለዱት የእስራኤላውያን እንስሶች ምትክ የሌዋውያንን እንስሳት ለእኔ የተለዩ እንዲሆኑ አድርግ። 46 በኲር ሆነው የተወለዱት የእስራኤላውያን ወንዶች ልጆች ብዛት፥ ከሌዋውያን ብዛት በሁለት መቶ ሰባ ሦስት ስለሚበልጥ እነዚህን ትርፍ የሆኑትን ወንዶች ልጆች በገንዘብ መዋጀት ይኖርብሃል። 47 ለያንዳንዱ መዋጃ በመቅደሱ ሚዛን መሠረት አምስት ሰቅል የሚመዝን ብር ትወስዳለህ፤ አንዱ ሰቅል ኻያ ጌራ ነው (ጌራ 0.6 ግራም ነው)። 48 ይህንንም የመዋጃ ገንዘብ ለአሮንና ለልጆቹ ስጥ።” 49 ሙሴም በሌዋውያን ከተዋጁት የተረፉት ሁለት መቶ ሰባ ሦስት ሰዎች የተሰበሰበውን የመዋጃ ገንዘብ ተቀበለ። 50 ከእስራኤላውያን በኲሮች በመቅደሱ ሚዛን መሠረት ገንዘቡን አንድ ሺህ ሦስት መቶ ሥልሳ አምስት ሰቅል ብር ወሰደ። 51 እግዚአብሔር ባዘዘው ቃል መሠረት ሙሴ የመዋጃውን ገንዘብ ለአሮንና ለልጆቹ ሰጠ። |