Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ዘኍል 28 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


የዘወትር መሥዋዕት
( ዘፀ. 29፥38-46 )

1 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤

2 “ለእስራኤል ሕዝብ የምትሰጣቸው ትእዛዝ ይህ ነው፦ መዓዛው ደስ የሚያሰኝ በእሳት የሚቃጠል የምግብ ቊርባን እንዲያቀርቡልኝ ንገራቸው።”

3 “ለእኔ የሚቀርበውም በእሳት የሚቃጠል የምግብ ቊርባን የሚከተለው ነው፦ በየቀኑ ለሚቀርበው የሚቃጠል መሥዋዕት አንድ ዓመት የሞላቸውና ምንም ነውር የሌለባቸው ሁለት የበግ ጠቦቶች ይሁኑ፤

4 የመጀመሪያው ጠቦት ጠዋት፥ ሁለተኛውም ጠቦት ማታ እንዲቀርብ አድርጉ፤

5 ከእያንዳንዱም ጠቦት ጋር ምርጥ በሆነ፥ በአንድ ሊትር የወይራ ዘይት የተለወሰ፥ አንድ ኪሎ ዱቄት የእህል ቊርባን ሆኖ ይቅረብ፤

6 ይህም በፍጹም የሚቃጠለው የዘወትር መሥዋዕት ነው፤ የዚህ ዐይነቱ መሥዋዕት መዓዛው እኔን እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ የምግብ ቊርባን ሆኖ በመጀመሪያ የቀረበው በሲና ተራራ ላይ ነበር።

7 ከመጀመሪያው ጠቦት ጋር የመጠጥ መባ ሆኖ እንዲቀርብ አንድ ሊትር ጠንካራ መጠጥ በመሠዊያው ላይ አፍስሱበት።

8 ሲመሽም ሁለተኛውን ጠቦት ልክ የመጀመሪያው በቀረበበት ሁኔታ የመጠጡንም መባ ጨምራችሁ አቅርቡ፤ እርሱም መዓዛው እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ የምግብ ቊርባን ይሆናል።


የሰንበት መሥዋዕት

9 “በሰንበት ቀን አንድ ዓመት የሞላቸውና ምንም ነውር የሌለባቸው ሁለት የበግ ጠቦቶች አቅርቡ፤ በወይራ ዘይት የተለወሰ ሁለት ኪሎ ምርጥ ዱቄት ለእህል ቊርባን አቅርቡ፤ እንዲሁም የመጠጡንም መባ አቅርቡ፤

10 ከመጠጡ መባና ከሚቀርበው ከዘወትር መሥዋዕት ጋር ይህ የሚቃጠል መሥዋዕት በየሰንበቱ ይቅረብ።


ወር በገባ በመጀመሪያው ቀን የሚቀርብ መሥዋዕት

11 “በእያንዳንዱ ወር መጀመሪያ ቀን የሚቃጠል መሥዋዕት ለእግዚአብሔር አቅርቡ፤ ይኸውም ነውር የሌለባቸውን ሁለት ወይፈኖች፥ አንድ አውራ በግ፥ አንድ ዓመት የሞላቸው ሰባት ተባዕት የበግ ጠቦቶች ታቀርባላችሁ።

12 ለእህልም ቊርባን በወይራ ዘይት የተለወሰ ምርጥ ዱቄት አቅርቡ፤ ይኸውም ከእያንዳንዱ ኰርማ ጋር ሦስት ኪሎ ዱቄት፥ ከአውራው በግ ጋር ሁለት ኪሎ ዱቄት፥

13 ከእያንዳንዱም የበግ ጠቦት ጋር በዘይት የተለወሰ የእህል ቊርባን አንድ ኪሎ ዱቄት ታቀርባላችሁ፤ ይህም የሚቃጠል መሥዋዕት ሁሉ መዓዛው እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ የምግብ መባ ሆኖ ይቀርባል።

14 ተገቢ ለሆነው የመጠጥ መባ ከእያንዳንዱ ኰርማ ጋር ሁለት ሊትር መጠጥ፥ ከአውራው በግ ጋር አንድ ተኩል ሊትር መጠጥ፥ ከእያንዳንዱም ጠቦት ጋር አንድ ሊትር የወይን ጠጅ አቅርቡ፤ በዓመቱ ሙሉ፥ ወር በገባ በመጀመሪያው ቀን ስለሚቀርበው የሚቃጠል መሥዋዕት የተሰጠው የሥርዓት መመሪያ ይኸው ነው።

15 በየቀኑ ከሚቀርበው የሚቃጠል መሥዋዕት ጋር የመጠጥ መባ በመጨመር አንድ ተባዕት ፍየል ስለ ኃጢአት ስርየት መሥዋዕት አድርጋችሁ አቅርቡ።


በፋሲካና በቂጣ በዓል የሚቀርብ መሥዋዕት
( ዘሌ. 23፥5-14 )

16 “የጌታ የፋሲካ በዓል የሚከበረው የመጀመሪያው ወር በገባ በዐሥራ አራተኛው ቀን ይሁን።

17 በዐሥራ አምስተኛው ቀን በዓል ነው፤ ለሰባት ቀኖች መበላት ያለበት እርሾ ያልነካው ቂጣ ብቻ ነው፤

18 በበዓሉ መጀመሪያ ቀን ለአምልኮ ትሰበሰባላችሁ፤ በእርሱ ምንም ሥራ አትሠሩበትም።

19 የምግብ ቊርባን አድርጋችሁ የሚቃጠል መሥዋዕት አቅርቡ፤ ይኸውም ነውር የሌለባቸው ሁለት ወይፈኖች፥ አንድ አውራ በግ፥ አንድ ዓመት የሞላቸው ሰባት ተባዕት የበግ ጠቦቶች ታቀርባላችሁ፤

20 ተገቢ የሆነውንም የእህል ቊርባን በወይራ ዘይት የተለወሰ ምርጥ ዱቄት አቅርቡ፤ ይኸውም ከእያንዳንዱ ኰርማ ጋር ሦስት ኪሎ ዱቄት፥ ከአውራው በግ ጋር ሁለት ኪሎ ዱቄት፥

21 ከእያንዳንዱም ጠቦት ጋር አንድ ኪሎ ዱቄት ታቀርባላችሁ።

22 ስለ ኃጢአት ስርየትም የሚሆን አንድ ተባዕት ፍየል ታቀርባላችሁ፤ ይህም የኃጢአት ማስተስረያ መሥዋዕት ነው።

23 እነዚህም ሁሉ የሚቀርቡት በየቀኑ ጠዋት ከሚቀርበው የሚቃጠል መሥዋዕት ጋር ተጨማሪ ሆነው ነው።

24 መዓዛው እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኘውንም የምግብ ቊርባን በተመሳሳይ ሁኔታ በሰባቱም ቀኖች ውስጥ ታቀርባላችሁ፤ ይህንንም የምታቀርቡት በቀኑ ከሚቀርበው የሚቃጠል መሥዋዕትና የመጠጥ መባ ጋር ተጨማሪ በማድረግ ነው።

25 በሰባተኛው ቀን ለአምልኮ ትሰበሰባላችሁ፤ በእርሱ ምንም ሥራ አትሠሩም።


በመከር በዓል ጊዜ የሚቀርብ መሥዋዕት
( ዘሌ. 23፥15-22 )

26 “በመከር በዓል መጀመሪያ ቀን አዲስ እህል ለእግዚአብሔር መባ አድርጋችሁ በምታቀርቡበት ጊዜ ለአምልኮ ትሰበሰባላችሁ፤ ሥራም አትሠሩም፤

27 ሁለት ወይፈኖች፥ አንድ አውራ በግ፥ አንድ ዓመት የሞላቸው ሰባት ተባዕት የበግ ጠቦቶች፥ መዓዛው እግዚአብሔርን ደስ የሚያሰኝ የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጋችሁ ታቀርባላችሁ።

28 ተገቢ የሆነውንም የእህል ቊርባን በወይራ ዘይት የተለወሰ ምርጥ ዱቄት ታቀርባላችሁ፤ ይኸውም ከእያንዳንዱ ኰርማ ጋር ሦስት ኪሎ ዱቄት፥ ከአውራው በግ ጋር ሁለት ኪሎ ዱቄት፥

29 ከእያንዳንዱም የበግ ጠቦት ጋር አንድ ኪሎ ዱቄት ታቀርባላችሁ፤

30 ስለ ኃጢአት ስርየትም የሚሆን አንድ ተባዕት ፍየል ታቀርባላችሁ፤ በዚህም ዐይነት ለሕዝቡ የኃጢአት ስርየት ሥርዓት ትፈጽማላችሁ።

31 ይህን ሁሉ መሥዋዕትና የመጠጥ መባ በቀኑ ከሚቀርበው የሚቃጠል መሥዋዕትና የእህል ቊርባን ጋር ተጨማሪ በማድረግ ታቀርባላችሁ፤ እንስሶቹም ነውር የሌለባቸው መሆናቸውን አረጋግጡ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos