ዘኍል 26 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምሁለተኛው የሕዝብ ቈጠራ 1 መቅሠፍቱ ከቆመ በኋላ እግዚአብሔር ሙሴንና የካህኑን የአሮንን ልጅ አልዓዛርን እንዲህ አላቸው፤ 2 “በመላው የእስራኤል ማኅበር በየቤተሰቡ ዕድሜአቸው ኻያ ዓመት የሞላቸውንና ከዚያም በላይ የሆኑትን፥ ወታደር ሆነው ለማገልገል ብቃት ያላቸውን ወንዶች ልጆች ሁሉ ቊጠሩ።” 3 ሙሴና ካህኑ አልዓዛር በዮርዳኖስ አጠገብ ከኢያሪኮ ትይዩ ባለው የሞአብ ሜዳ ሕዝቡን ሰብስበው እንዲህ አሉአቸው፦ 4 “እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት ኻያና ከኻያ ዓመት በላይ ዕድሜ ያላቸውን ሰዎች ሁሉ ቈጠሩ።” ከግብጽ ምድር የወጡትም እስራኤላውያን እነዚህ ነበሩ፦ 5 የያዕቆብ የበኲር ልጅ የሮቤል ነገድ ተወላጆች ሐኖክ፥ ፋሉስ፥ 6 ሔጽሮን፥ ከርሚና የእነርሱ ተወላጆች ናቸው። 7 ከሮቤል ነገድ የጐሣ መሪዎች የተቈጠሩት ጠቅላላ ቊጥር አርባ ሦስት ሺህ ሰባት መቶ ሠላሳ ነበር፤ 8 የፋሉ ዘሮችም ኤሊአብና 9 የኤሊአብ ልጆች ነሙኤል፥ ዳታንና አቤሮን ነበሩ፤ ዳታንና አቤሮንም በማኅበሩ ተመርጠው የነበሩት ሲሆኑ እነርሱም ከቆሬና ከተከታዮቹ ጋር ተባብረው በእግዚአብሔር ላይ ባመፁ ጊዜ ሙሴንና አሮንን የተፈታተኑአቸው ናቸው። 10 እነርሱንም ምድር ተከፍታ ከቆሬ ጋር ዋጠቻቸው፤ እነርሱም በሞቱ ጊዜ እሳት ወርዶ ሁለት መቶ ኀምሳውን ሰዎች አቃጠላቸው፤ ለሕዝቡም መቀጣጫ ሆኑ። 11 የቆሬ ልጆች ግን አልሞቱም። 12 የስምዖን ነገድ ተወላጆች፦ ነሙኤል፥ ያሚንና፥ ያኪን፥ 13 ዛራ፥ ሳኡልና የእነርሱ ተወላጆች ናቸው። 14 ከስምዖን ነገድ የጐሣ መሪዎች የተቈጠሩት ኻያ ሁለት ሺህ ሁለት መቶ ነበሩ። 15 የጋድ ነገድ ተወላጆች ጽፎን፥ ሐጊ፥ ሹኒ፥ 16 ኤስናን፥ ዔሪ፥ 17 አሮድ አርኤሊና ተወላጆቻቸው ናቸው። 18 ከጋድ ወገኖች የተቈጠሩት ጠቅላላ ቊጥር አርባ ሺህ አምስት መቶ ነበር። 19 የይሁዳ ነገድ ተወላጆች፥ ኤርና አውናን በከነዓን ምድር ሞቱ። 20 የቀሩት የይሁዳ ልጆች ሴሎም ፋሬስ ዛራና ተወላጆቻቸው ናቸው። 21 የፋሬስም ልጆች፥ ኤስሮም፥ ሐሙልና ተወላጆቻቸው ናቸው። 22 ከይሁዳ ነገድ የጐሣ መሪዎች የተቈጠሩት ሰባ ስድስት ሺህ አምስት መቶ ነበሩ። 23 የይሳኮር ነገድ ተወላጆች ቶላ፥ ፉዋ፥ 24 ያሱብ፥ ሺምሮንና ተወላጆቻቸው ናቸው። 25 ከይሳኮር ነገድ የጐሣ መሪዎች የተቈጠሩት ሥልሳ አራት ሺህ ሦስት መቶ ነበሩ። 26 የዛብሎን ነገድ ተወላጆች ሴሬድ፥ ኤሎን ያሕይኤልና ተወላጆቻቸው ናቸው፥ 27 ከዛብሎን ነገድ የጐሣ መሪዎች የተቈጠሩት ሥልሳ ሺህ አምስት መቶ ነበር። 28 የዮሴፍ ልጆች በየወገናቸው፥ ምናሴና ኤፍሬም፥ 29 የምናሴ ነገድ ተወላጆች ማኪር ገለዓድን ወለደ፤ 30 የገለዓድ ልጆች እነዚህ ናቸው፤ ኢኤዝር፥ ሔሌቅ፥ 31 አስሪኤል፥ ሴኬም። 32 ሸሚዳ፥ ኦፌር፥ 33 የሔፌር ልጅ ጸሎፍሐድ ከሴቶች በቀር ወንዶች ልጆች አልነበሩትም፤ እነርሱም ማሕላ፥ ኖዓ፥ ሖግላ፥ ሚልካ እና ቲርጻ ተብለው የሚጠሩ ነበሩ፤ 34 ከምናሴ ነገድ የጐሣ መሪዎች የተቈጠሩ ኀምሳ ሁለት ሺህ ሰባት መቶ ነበሩ። 35 የኤፍሬም ነገድ ተወላጆች ሱቱላ፥ ቤኬር፥ ታሖን፥ 36 የሱቱላ ልጅ፦ ዔራንና የእነርሱ ተወላጆች ናቸው። 37 እነዚህ የኤፍሬም ወገኖች ናቸው፤ ከእነርሱም የተቈጠሩት ሠላሳ ሁለት ሺህ አምስት መቶ ነበሩ። በየወገናቸው የዮሴፍ ተወላጆች እነዚህ ናቸው። 38 የብንያም ነገድ በየትውልዳቸው ቤላ፥ አሽቤል፥ አሒራም። 39 ሹፋም፥ ሑፋም፥ 40 የቤላም ልጆች አርድና ናዕማን ናቸው። ከናዕማናውያን ወገን ናዕማን፥ 41 የብንያም ነገድ ተወላጆች እነዚህ ናቸው። ከእነርሱም የተቈጠሩት አርባ አምስት ሺህ ስድስት መቶ ነበሩ። 42 የዳን ነገድ ተወላጆች ሰሜዔና፤ ተወላጆቹ፥ 43 የሰምዔያውያን ወገኖች ሁሉ ከእነርሱ እንደ ተቈጠሩ ሥልሳ አራት ሺህ አራት መቶ ነበሩ። 44 የአሴር ነገድ ተወላጆች ዪምና፥ የሱዋ፥ በሪዓ። 45 ከበሪዓ ልጆች፦ ሔቤር፥ መልኪኤል፥ 46 አሴርም ሤራሕ የምትባል ሴት ልጅ ነበረችው፤ 47 እነዚህ የአሴር ተወላጆች ናቸው፤ ከእነርሱም የተቈጠሩት ኀምሳ ሦስት ሺህ አራት መቶ ነበር። 48 የንፍታሌም ነገድ ተወላጆች ያሕጼል፥ ጉኒ 49 ዬጽር፥ ሺሌምና የእነርሱ ተወላጆች ናቸው። 50 የንፍታሌም ነገድ በየወገናቸው እነዚህ ናቸው፤ ከእነርሱም የተቈጠሩት አርባ አምስት ሺህ አራት መቶ ነበሩ። 51 በዚህም ዐይነት ከእስራኤላውያን የተቈጠሩት ስድስት መቶ አንድ ሺህ ሰባት መቶ ሠላሳ ነበሩ። 52 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 53 “ምድሪቱን በስማቸው ምዝገባ መሠረት ለየነገዱ በርስትነት አከፋፍል፤ 54 ብዛት ላለው ነገድ ሰፊ መሬት፥ አነስተኛ ቊጥር ለሆነ ነገድ ጠበብ ያለ መሬት ስጥ፤ የርስቱም ክፍፍል በቈጠራ በተገኘው የሕዝብ ብዛት መሠረት ነው። 55 ሆኖም ክፍፍሉ የሚደረገው በዕጣ ነው፤ ዕጣውም የሚጣለው በየነገዱ መሠረት ነው። 56 ዕጣ የሚጣለውም ከፍተኛ ቊጥርና አነስተኛ ቊጥር ባላቸው ቤተሰቦች መካከል ነው።” 57 ከሌዋውያን ነገድ ተወላጆች፦ ጌርሾን፥ ቀዓት፥ ሜራሪና የእነርሱ ተወላጆች ናቸው። የእነርሱም ዘሮች ሊብኒ፥ ኬብሮን፥ ማሕሊ፥ ሙሴ፥ ቆሬና የእነርሱ ተወላጆች ናቸው። ቀዓትም አሞራምን ወለደ። 58 የእነርሱ ዘሮች የሊብናውያን ወገን፥ የኬብሮናውያን ወገን፥ የሞላውያን ወገን፥ የሙሳውያን ወገን፥ የቆሬያውያን ወገን ቀዓትም አምራምን ወለደ። 59 ዓሞራም በግብጽ የተወለደችውን የሌዊን ሴት ልጅ ዮኬቤድን አግብቶ ነበር፤ እርስዋም አሮንና ሙሴ የተባሉትን ሁለት ወንዶች ልጆችንና ማርያም የተባለችውን አንዲት ሴት ልጅ ወለደችለት። 60 አሮንም ናዳብ፥ አቢሁ፥ አልዓዛርና ኢታማር የተባሉ አራት ወንዶች ልጆች ነበሩት። 61 ናዳብና አቢሁ ያልተቀደሰ እሳት ለእግዚአብሔር ከማቅረባቸው የተነሣ ተቀሥፈው ሞቱ። 62 ዕድሜአቸው አንድ ወርና ከዚያም በላይ የሆነ የወንዶች ሌዋውያን ጠቅላላ ቊጥር ኻያ ሦስት ሺህ ሆነ፤ እነርሱም ከሌሎቹ እስራኤላውያን ተለይተው ተመዘገቡ፤ ይህም የሆነበት ምክንያት በእስራኤል ምድር ምንም ዐይነት የርስት ድርሻ ስላልተሰጣቸው ነበር። 63 ሙሴና አልዓዛር በኢያሪኮ ትይዩ ከዮርዳኖስ ወንዝ አጠገብ ባለው በሞአብ ሜዳ እስራኤላውያንን በቈጠሩበት ጊዜ የመዘገቡአቸው የጐሣ መሪዎች እነዚህ ነበሩ። 64 በሲና በረሓ በመጀመሪያው የሕዝብ ቈጠራ ጊዜ ሙሴና አሮን ከመዘገቡአቸው ወንዶች አንድም ተርፎ የቀረ አልነበረም። 65 ይህም የሆነው “ሁሉም በምድረ በዳ ይሞታሉ!” ብሎ እግዚአብሔር ተናግሮ ስለ ነበር ነው፤ ስለዚህም ከየፉኔ ልጅ ከካሌብና ከነዌ ልጅ ከኢያሱ በቀር ሁሉም ሞተዋል። |