Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ዘኍል 19 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ኃጢአትን ለማስተስረይ የሚፈጸም ሥርዓት

1 እግዚአብሔር ሙሴንና አሮንን እንዲህ አላቸው፤

2 “ይህ እኔ ያዘዝኩት የሕጉ ሥርዓት ነው፦ ነውር የሌለባትና በጫንቃዋ ላይ ቀንበር ተጭኖባት የማታውቅ አንዲት ቀይ ጊደር እንዲያመጡ ለእስራኤላውያን ንገሩአቸው።

3 ጊደርዋንም ለካህኑ ለአልዓዛር ስጡት፤ ከሰፈርም ወጥታ በእርሱ ፊት ትታረድ፤

4 ካህኑ አልዓዛርም ከደሙ ጥቂቱን ወስዶ በጣቱ እያጠቀሰ ወደ መገናኛው ድንኳን ፊት ሰባት ጊዜ ይርጨው፤

5 እንስሳዪቱ በሙሉ ማለትም ቆዳዋ፥ ሥጋዋ፥ ደምዋና የሆድ ዕቃዋ ሁሉ በካህኑ ፊት ይቃጠል፤

6 ካህኑ የሊባኖስ ዛፍ እንጨት፥ የሂሶጵ ቅርንጫፍና ቀይ ክር ወስዶ ጊደርዋ በምትቃጠልበት በእሳት ውስጥ ይጣለው፤

7 ከዚህ በኋላ ልብሱን ይጠብ፤ ገላውንም በውሃ ይታጠብና ወደ ሰፈሩ ይመለስ፤ ነገር ግን ያልነጻ ሆኖ እስከ ማታ ድረስ ይቈይ፤

8 ጊደርዋን ያቃጠለውም ሰው ልብሱን አጥቦ ገላውንም በውሃ ይታጠብ፤ እርሱም እስከ ማታ ያልነጻ ሆኖ ይቈያል።

9 ከዚህ በኋላ ንጹሕ የሆነ ሌላ ሰው የጊደርዋን ዐመድ ሰብስቦ በመውሰድ ከሰፈሩ ውጪ ንጹሕ በሆነ ቦታ ያስቀምጠዋል፤ እዚያም ለእስራኤላውያን ጉባኤ ርኲሰትን ለማንጻት የሚያገለግለውን ውሃ ለማዘጋጀት የሚጠቅም ይሆናል፤ ይህም ሥርዓት የሚፈጸመው ኃጢአትን ለማስወገድ ነው።

10 ዐመዱን የሰበሰበው ሰው ልብሱን ይጠብ፤ ነገር ግን እስከ ማታ ያልነጻ ሆኖ ይቈያል፤ ይህ የሥርዓት መመሪያ ለእስራኤላውያንና በመካከላቸው ለሚኖሩ መጻተኞች ለሚመጡት ዘመናት ሁሉ የጸና ሕግ ሆኖ ይኖራል።


በድን ስለ መንካት

11 “የማንኛውንም ሰው አስከሬን የሚነካ ለሰባት ቀን ያልነጻ ሆኖ ይቈያል፤

12 በሦስተኛውና በሰባተኛው ቀን ለማንጻት በተመደበው ውሃ ራሱን ያነጻል፤ ከዚያም በኋላ ንጹሕ ይሆናል፤ በሦስተኛውና በሰባተኛው ቀን ራሱን የማያነጻ ከሆነ ሊነጻ አይችልም።

13 ለማንጻት የተመደበው ውሃ በእርሱ ላይ ስላልፈሰሰ በድን ነክቶ ራሱን የማያነጻ፥ እንደ ረከሰ ይቈያል፤ እንዲህ ያለው ሰው ድንኳኑን ያረክሳል፤ ስለዚህም ከእስራኤል ሕዝብ ይለይ።

14 “አንድ ሰው በድንኳኑ ውስጥ በሚሞትበት ጊዜ ተፈጻሚ የሚሆነው ሕግ ይህ ነው። እርሱ በሞተበት ጊዜ በዚያ ድንኳን ውስጥ ያለ ሰው ወይም ወደዚያ የሚገባ ሰው ለሰባት ቀን ያልነጻ ሆኖ ይቈያል።

15 በድንኳኑ ውስጥ የሚገኝ ክዳን የሌለው ማንኛውም እንስራም ሆነ ማሰሮ የረከሰ ይሆናል።

16 ሰው የገደለውን ወይም በሕመም የሞተውን ሰው በውጭ ወድቆ ሳለ ሬሳውን የሚነካ ሰው፥ ወይም የሰው ዐፅም፥ ወይም መቃብር የሚነካ ሰው ለሰባት ቀን የረከሰ ይሆናል።

17 “ርኲሰቱንም ለማስወገድ፥ ለኃጢአት ማስተስረያ ከተቃጠለችው ጊደር ዐመድ ጥቂት ተወስዶ በማሰሮ ውስጥ ይከተት፤ ንጹሕ የምንጭ ውሃም ይጨመርበት፤

18 ቀጥሎም ንጹሕ የሆነ ሰው የሂሶጵ ቅርንጫፍ ወስዶ በውሃው ውስጥ እየነከረ በድንኳኑና በውስጡ በሚገኙት ዕቃዎች ሁሉ ላይ እንዲሁም በድንኳኑ ውስጥ በሚገኙ ሰዎች ላይ ይርጨው፤ ከዚያም በኋላ ንጹሕ የሆነ ሰው ዐፅም ወይም ሬሳ ወይም መቃብር በነካው ሰው ላይ ውሃ ይርጭበት፤

19 በሦስተኛውና በሰባተኛው ቀን የነጻው ሰው ባልነጻው ሰው ላይ ውሃ ይርጭበት፤ በሰባተኛው ቀን ሰውየውን ያነጻዋል፤ ያም ሰው ልብሱንና ገላውን ካጠበ በኋላ ፀሐይ ስትጠልቅ የነጻ ይሆናል።

20 “ያልነጻና ራሱንም ያላነጻ ሰው ለማንጻት የተመደበው ውሃ በላዩ ስላልፈሰሰ የረከሰ ሆኖ ይቈያል፤ እንደዚህ ያለው ሰው የእግዚአብሔርን ድንኳን ስለሚያረክስ ከማኅበሩ ይለይ።

21 ይህን ሕግ ለሚመጡት ዘመናት ሁሉ መጠበቅ ይኖርባችኋል፤ ለማንጻት የሚያገለግለውን ውሃ በላዩ የሚረጨው ሰው ልብሱን ማጠብ ይኖርበታል፤ ውሃውን የሚነካ ሁሉ እስከ ማታ ድረስ ያልነጻ ሆኖ ይቈያል፤

22 ያልነጻ ሰው የሚነካው ነገር ሁሉ የረከሰ ይሆናል፤ ያንንም ዕቃ የሚነካ ሌላ ሰው እስከ ማታ እንደ ረከሰ ይቈያል።”

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos