ዘኍል 17 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየአሮን በትር መለምለም 1 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ 2 “የእስራኤል ሕዝብ ከያንዳንዱ የነገድ መሪ አንዳንድ በትር ተቀብለው ዐሥራ ሁለት በትሮች እንዲሰጡህ ጠይቃቸው፤ የእያንዳንዱንም ስም በበትሩ ላይ ጻፍ። 3 በሌዊ ነገድ ስም በቀረበውም በትር ላይ የአሮንን ስም ጻፍበት፤ ስለያንዳንዱ ነገድ መሪ አንድ በትር ይቅረብ። 4 እነርሱንም ወደ መገናኛው ድንኳን ወስደህ አንተን በማነጋግርበት ስፍራ በታቦቱ ፊት ለፊት አኑራቸው፤ 5 ከዚያም በኋላ እኔ ለክህነት የምመርጠው ሰው በትሩ በማቈጥቈጥ ትለመልማለች፤ በዚህም ዐይነት እነዚህ እስራኤላውያን በየጊዜው በአንተ ላይ ማጒረምረማቸውን እንዲያቆሙ አደርጋለሁ።” 6 ስለዚህ ሙሴ ይህንኑ ለእስራኤላውያን ነገራቸው፤ እያንዳንዱም መሪ በትሩን አምጥቶ ሰጠው፤ ስለያንዳንዱ የነገድ መሪ የሚሰጠው አንዳንድ በትር ሆኖ በአጠቃላይ ዐሥራ ሁለት በትሮች ቀረቡ፤ ከእነዚያም በትሮች መካከል የአሮን በትር ነበረች፤ 7 ሙሴ በትሮቹን ሁሉ ወስዶ በድንኳኑ ውስጥ በእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ታቦት ፊት ለፊት አኖራቸው። 8 በማግስቱ ሙሴ ወደ ድንኳኑ በገባ ጊዜ በሌዊ ነገድ ስም የቀረበችው የአሮን በትር ለምልማ አገኛት፤ ይኸውም እንቡጥ አውጥታ በማበብ የበሰለ የለውዝ ፍሬ አፍርታ ነበር። 9 ሙሴም በትሮቹን ሁሉ አምጥቶ ለእስራኤላውያን አሳያቸው፤ የሆነውን ሁሉ ከተመለከቱ በኋላ እያንዳንዱ መሪ የራሱን በትር ወሰደ። 10 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፦ “የአሮንን በትር በቃል ኪዳኑ ታቦት ፊት መልሰህ አኑረው፤ ዐመፀኞች የሆኑ እስራኤላውያን በእኔ ላይ ማጒረምረማቸውን ካልተዉ እንደሚሞቱ ማስጠንቀቂያ ሆኖ ይቀመጥ።” 11 ሙሴም እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገ። 12 እስራኤላውያን ሙሴን እንዲህ አሉት፤ “እንዲህ ከሆነማ እኛ ሁላችንም ማለቃችን ነው! 13 ወደ ድንኳኑ የሚቀርብ ሁሉ የሚሞት ከሆነ ሁላችንም እንጠፋለን ማለት ነውን?” |