ዘኍል 1 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየመጀመሪያው የእስራኤል የሕዝብ ቈጠራ 1 እስራኤላውያን ከግብጽ በወጡ በሁለተኛው ዓመት፥ ሁለተኛው ወር በገባ በመጀመሪያው ቀን በሲና በረሓ ሳሉ፥ እግዚአብሔር በመገናኛው ድንኳን ውስጥ ሙሴን እንዲህ ሲል አነጋገረው፦ 2-3 “አንተና አሮን፥ የእስራኤልን ሕዝብ ሁሉ በየነገዱና በየቤተሰቡ ኻያ ዓመትና ከዚያ በላይ የሆነውን እያንዳንዱን ወንድ አንድ በአንድ እየቈጠራችሁ መዝግቡ። 4 ከእያንዳንዱ ነገድ አንዳንድ የቤተሰብ አለቃ ከእናንተ ጋር ይሁን። 5 የሚረዱአችሁ ሰዎች ስም የሚከተሉት ናቸው፦ ከሮቤል የሸዴኡር ልጅ ኤሊጹር 6 ከስምዖን የጹሪሻዳይ ልጅ ሸሉሚኤል 7 ከይሁዳ የዓሚናዳብ ልጅ ነአሶን 8 ከይሳኮር የጹዓር ልጅ ናትናኤል 9 ከዛብሎን የሔሎን ልጅ ኤሊአብ 10 ከዮሴፍ ልጆች፦ ከኤፍሬም የዓሚሁድ ልጅ ኤሊሻማዕ ከምናሴ የጴዳጹር ልጅ ገማልኤል 11 ከብንያም የጊድዖኒ ልጅ አቢዳን 12 ከዳን የዓሚሻዳይ ልጅ አሒዔዜር 13 ከአሴር የዖክራን ልጅ ፋግዒኤል 14 ከጋድ የደዑኤል ልጅ ኤልያሳፍ 15 ከንፍታሌም የዔናን ልጅ አሒራዕ።” 16 ከማኅበሩ መካከል፥ ከየነገዶቻቸው የእስራኤል ቤተሰብ መሪዎች ሆነው የተመረጡት እነዚህ ነበሩ። 17 ሙሴና አሮን እነዚህን ስሞቻቸው የተጠቀሱትን ሰዎች ወሰዱ፤ 18 ሁለተኛው ወር በገባ በመጀመሪያው ቀን፥ ማኅበሩን ሁሉ በአንድነት ሰብስበው በየነገዱና በየቤተሰቡ ከመደቡ በኋላ የሕዝብ ቈጠራ አደረጉ፤ ዕድሜአቸው ኻያ ዓመትና ከዚያም በላይ የሆኑ ወንዶች ሁሉ እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት ስማቸው እየተመዘገበ ተቈጠሩ። 19 በዚህም ዐይነት ሙሴ እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት በሲና በረሓ ሕዝቡን ቈጠረ። 20 ወታደር ሆነው ለማገልገል ችሎታ ያላቸው፥ ዕድሜአቸው ኻያ ዓመትና ከዚያም በላይ የሆነ ወንዶች ከያዕቆብ ልጆች በኲር ከሆነው ከሮቤል ነገድ 21 ከሮቤል ነገድ የተቈጠሩት አርባ ስድስት ሺህ አምስት መቶ ነበሩ። 22 ከስምዖን ነገድ በየትውልዳቸው በየወገናቸውና በየቤተሰባቸው፥ እንደየስማቸው ቊጥር ኻያ ዓመትና ከዚያም በላይ የሆነው ወደ ጦርነት ለመውጣት የሚችል ወንድ ሁሉ በየራሳቸው የተቈጠሩት፥ 23 ኀምሳ ዘጠኝ ሺህ ሦስት መቶ ነበሩ። 24 ከጋድ ነገድ በየትውልዳቸው፥ በየወገናቸውና በየቤተሰባቸው እንደየስማቸው ቊጥር ኻያ ዓመትና ከዚያም በላይ የሆኑ ወንዶች ሁሉ የተቈጠሩት፤ 25 አርባ አምስት ሺህ ስድስት ሞቶ ኀምሳ ነበሩ። 26-27 ከይሁዳ ነገድ በየትውልዳቸው፥ በየወገናቸውና በየቤተሰባቸው፥ እንደየስማቸው ቊጥር፥ ኻያ ዓመትና ከዚያም በላይ የሆኑ ወንዶች ሁሉ ተቈጠሩ፤ ከይሁዳ ነገድ የተቈጠሩት ሰባ አራት ሺህ ስድስት መቶ ነበሩ። 28 የይሳኮር ልጆች፥ በየትውልዳቸው፥ በየወገናቸውና በየአባቶቻቸው ቤቶች እንደየስማቸው ቊጥር ኻያ ዓመትና ከዚያም በላይ የሆኑ ወንዶች ሁሉ ተቈጠሩ፤ 29 ከይሳኮር ነገድ የተቈጠሩት ኀምሳ አራት ሺህ አራት መቶ ነበሩ። 30 የዛብሎን ልጆች፥ በየትውልዳቸው፥ በየወገናቸውና በየአባቶቻቸው ቤቶች እንደየስማቸው ቊጥር ኻያ ዓመትና ከዚያም በላይ የሆኑ ወንዶች ሁሉ ተቈጠሩ፤ 31 ከዛብሎን ነገድ የተቈጠሩት ኀምሳ ሰባት ሺህ አራት መቶ ነበሩ። 32 ከዮሴፍ ልጆች፥ የኤፍሬም ልጆች በየትውልዳቸው፥ በየወገናቸውና በየአባቶቻቸው ቤቶች እንደየስማቸው ቊጥር ኻያ ዓመትና ከዚያም በላይ የሆኑ ወንዶች ሁሉ ተቈጠሩ፤ 33 ከኤፍሬም ነገድ የተቈጠሩት አርባ ሺህ አምስት መቶ ነበሩ፤ 34 የምናሴ ልጆች፥ በየትውልዳቸው፥ በየወገናቸውና በየአባቶቻቸው ቤቶች እንደየስማቸው ቊጥር ኻያ ዓመትና ከዚያም በላይ የሆኑ ወንዶች ሁሉ ተቈጠሩ፤ 35 ከምናሴ ነገድ የተቈጠሩት ሠላሳ ሁለት ሺህ ሁለት መቶ ነበሩ። 36 የብንያም ልጆች፥ በየትውልዳቸው፥ በየወገናቸውና በየአባቶቻቸው ቤቶች እንደየስማቸው ቊጥር ኻያ ዓመትና ከዚያም በላይ የሆኑት ወንዶች ሁሉ ተቈጠሩ፤ 37 ከብንያም ነገድ የተቈጠሩት ሠላሳ አምስት ሺህ አራት መቶ ነበሩ። 38 የዳን ልጆች፥ በየትውልዳቸው፥ በየወገናቸውና በየአባቶቻቸው ቤቶች እንደየስማቸው ቊጥር ኻያ ዓመትና ከዚያም በላይ የሆኑ ወንዶች ሁሉ ተቈጠሩ፤ 39 ከዳን ነገድ የተቈጠሩ ሥልሳ ሁለት ሺህ ሰባት መቶ ነበሩ። 40 የአሴር ልጆች፥ በየትውልዳቸው፥ በየወገናቸው በየአባቶቻቸው ቤቶች፥ እንደየስማቸው ቊጥር ኻያ ዓመትና ከዚያም በላይ የሆኑ ወንዶች ሁሉ ተቈጠሩ፤ 41 ከአሴር ነገድ የተቈጠሩት አርባ አንድ ሺህ አምስት መቶ ነበሩ። 42 የንፍታሌም ልጆች፥ በየትውልዳቸው በየወገናቸውና በየአባቶቻቸው ቤቶች እንደየስማቸው ኻያ ዓመትና ከዚያም በላይ የሆኑ ወንዶች ሁሉ ተቈጠሩ፤ 43 ከንፍታሌም ነገድ የተቈጠሩት ኀምሳ ሦስት ሺህ አራት መቶ ነበሩ። 44 እያንዳንዱ የራሱን ወገን ወክሎ በመምጣት በዐሥራ ሁለቱ የነገድ መሪዎች ርዳታ ሙሴና አሮን የቈጠሩአቸው እነዚህ ናቸው፤ 45 በዚህም መሠረት መላው እስራኤላውያን በየነገዳቸው፥ ኻያ ዓመትና ከዚያም በላይ የሆኑት ወደ ጦርነት ለመሄድ የሚችሉ ሁሉ፥ 46 በጠቅላላ የተቈጠሩት ስድስት መቶ ሦስት ሺህ አምስት መቶ ኀምሳ ነበሩ። 47 ሌዋውያን ግን ከሌሎች ነገዶች ጋር አብረው አልተቈጠሩም። 48 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ ብሎት ነበር፤ 49 “እስራኤላውያን ወንዶችን ስትቈጥር፥ የሌዊን ነገድ አትጨምር። 50 በዚህ ፈንታ ሌዋውያንን በመገናኛው ድንኳንና በውስጡም ባሉት የመገልገያ ዕቃዎች ላይ ኀላፊዎች አድርገህ መድባቸው፤ እነርሱ ድንኳኑንና በውስጡ ያሉትን የመገልገያ ዕቃዎች ሁሉ ይሸከማሉ፤ በድንኳኑም ውስጥ ያገለግላሉ፤ በዙሪያውም ይሰፍራሉ። 51 ሰፈራችሁን ለቃችሁ በምትሄዱበት ጊዜ ሌዋውያን ብቻ ድንኳኑን ነቅለው በሚሰፍሩበት አዲስ ቦታ ይተክሉታል፤ ከእነርሱ በቀር ወደ ድንኳኑ የሚቀርብ ማንኛውም ሰው በሞት ይቀጣል። 52 ሌሎቹ እስራኤላውያን በየቡድናቸውና በየሰፈራቸው ድንኳኖቻቸውን ይተክላሉ። 53 ነገር ግን ማንም ሰው ወደ ድንኳኑ በመቅረብ ቊጣዬን አነሣሥቶ የእስራኤልን ማኅበር እንዳያስፈጅ ሌዋውያን በድንኳኑ ዙሪያ ሰፍረው ይጠብቁት።” 54 ስለዚህ የእስራኤል ሕዝብ እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት ሁሉን ነገር አደረጉ። |