Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ነህምያ 6 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


በነህምያ ላይ የተደረገው ሤራ መቀጠሉ

1 ሰንባላጥ፥ ጦቢያ፥ ዐረባዊው ጌሼምና ሌሎችም ጠላቶቻችን የቅጽሩን ግንብ ሠርቼ መፈጸሜንና ያልተሠራ ክፍት ቦታ አለመኖሩን ሰሙ፤ ይሁን እንጂ በቅጽር በሮቹ ላይ መዝጊያዎችን አላቆምኩም ነበር።

2 ከዚህም የተነሣ ሰንባላጥና ጌሼም በተለይ ኦኖ ተብሎ በሚጠራው ሜዳ ከሚገኙት መንደሮች በአንዲቱ እንድንገናኛቸው መልእክት ላኩብኝ፤ ይህም እኔን ለመጒዳት በተንኰል የተዶለተ ዘዴ ነበር።

3 እኔም “አስቸኳይ ሥራ ስላለብኝ ተግባሬን አቁሜ እናንተ ወዳላችሁበት ስፍራ መውረድ አልችልም፤ ወደ እናንተ ለመምጣት ተብሎ ለምን ሥራው ይቆማል?” አልኳቸው።

4 ያንኑም ዐይነት መልእክት በማከታተል አራት ጊዜ ሲልኩብኝ እኔም ተመሳሳዩን መልስ ሰጠኋቸው።

5 ከዚህም በኋላ ሰንባላጥ ከአገልጋዮቹ አንዱን ለአምስተኛ ጊዜ መልእክት አስይዞ ወደ እኔ ላከ፤ የተላከውም ግልጥ ደብዳቤ እንዲህ የሚል ነበር፦

6 “አንተና ወገኖችህ የሆኑት አይሁድ ዐመፅ ለማስነሣት ማቀዳችሁንና የቅጽር ግንቦችንም የምትሠሩት በዚሁ ምክንያት መሆኑን ጐረቤቶቻችን በሆኑ ሕዝቦች ዘንድ እንደሚወራ ጌሼም ነግሮኛል፤ ከዚህም ሌላ አንተ ራስህን ለማንገሥ ማሰብህንና፥

7 የይሁዳ ንጉሥ መሆንህንም በኢየሩሳሌም አንዲያውጁ፥ ነቢያት መሾምህን ጌሼም ጨምሮ ነግሮኛል፤ ይህንንም ወሬ ንጉሠ ነገሥቱ እንደሚሰማ የተረጋገጠ ነው፤ ስለዚህ አንተና እኔ ተገናኝተን በጒዳዩ ላይ ብንወያይበት ይሻላል።”

8 እኔም “ይህ የምትለው ነገር ሁሉ ምንም እውነትነት የሌለውና አንተ ራስህ የፈለሰፍከው ሐሰት ነው” ብዬ መለስኩለት።

9 በዚህም ዐይነት ሥራውን እንድናቆም ለማድረግ ያስፈራሩን ነበር፤ ስለዚህም “እግዚአብሔር አምላክ ሆይ! እባክህ አበርታኝ!” ስል ጸለይኩ።

10 በዚህም ጊዜ ከቤቱ እንዳይወጣ ተዘግቶበት ወደነበረው የመሄጣብኤል የልጅ ልጅ ወደ ሆነው ወደ ደላያ ልጅ ሸማዕያ ዘንድ ሄድኩ፤ እርሱም “በሌሊት ሊገድሉህ ስለሚመጡ አንተና እኔ ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ ገብተን በሮቹን በመዝጋት እንደበቅ” አለኝ።

11 እኔ ግን “እንደ እኔ ያለ ሰው ሸሽቶ አይደበቅም፤ እንደ እኔ ያለ ሰው ሕይወቱን ለማዳን ወደ ቤተ መቅደስ መግባት አለበትን? ይህን ከቶ አላደርገውም” ስል መለስኩለት።

12 በነገሩ ሳሰላስል፥ እርሱ እንዲህ ዐይነቱን የሐሰት ማስጠንቀቂያ እንዲሰጠኝ ጦቢያና ሰንባላጥ በገንዘብ የደለሉት እንጂ ሸማዕያ ከእግዚአብሔር የተላከ ነቢይ አለመሆኑን ተገነዘብኩ።

13 ይህን ነገር በማድረግ በደል እንድሠራና በእኔም ላይ ክፉ ወሬ በማውራት እያስፈራራ ስሜን በማጥፋት ያዋርደኝ ዘንድ ጉቦ ተቀብሎ ነበር።

14 እኔም “አምላክ ሆይ፥ ጦቢያና ሰንባላጥ ያደረጉትን ሁሉ ተመልከት፤ ፍረድባቸውም፤ ኖዓድያ የተባለችው ሴት ነቢይትና ሌሎቹም ነቢያት እኔን ለማስፈራራት ያደረጉትን ሁሉ አስብ” በማለት ጸለይኩ።


የቅጽር ግንቡ ሥራ ከፍጻሜ መድረስ

15 ሥራው ከተጀመረ ከኀምሳ ሁለት ቀኖች በኋላ ኤሉል ተብሎ የሚጠራው ወር በገባ በሃያ አምስተኛው ቀን የቅጽሩ ሥራ በሙሉ ተጠናቀቀ፤

16 በዙሪያችን የሚኖሩ አሕዛብ ጠላቶቻችን ይህን በሰሙ ጊዜ ሥራው አስደናቂ ሥራ መሆኑን ስለ ተገነዘቡና፤ ሥራውም በእግዚአብሔር ርዳታ የተከናወነ መሆኑን ስለ ተረዱ እጅግ ፈርተው ተደናገጡ።

17-18 የኢራሕ ልጅ ሴኬን የጦብያ አማች ስለ ነበርና ልጁ ዮሐናንም የቤሬክያን ልጅ የሜሱላንን ሴት ልጅ አግብቶ ስለ ነበረ ከይሁዳ ብዙዎቹ ከእርሱ ጋር ተማምለው ነበር፤ እንዲሁም የይሁዳ ባለ ሥልጣኖች በዚያው ወቅት ከጦብያ ጋር ብዙ የደብዳቤዎች መለዋወጥ ያደርጉ ነበር።

19 ጦቢያ ያደረገውን መልካም ነገር በማጋነን በፊቴ እንኳ ሳይቀር ይናገሩለት ነበር፤ እኔም የምለውን ሁሉ ለእርሱ ይነግሩት ነበር፤ ከዚህም የተነሣ እርሱ እኔን ለማስፈራራት ደብዳቤዎችን ከመላክ አልተቈጠበም።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos