Biblia Todo Logo
La Biblia Online

- Anuncios -


ነህምያ 12 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


የካህናትና የሌዋውያን ስም ዝርዝር

1 ከሰላትያል ልጅ ከዘሩባቤልና ከሊቀ ካህናቱ ከኢያሱ ጋር ከምርኮ የተመለሱት የካህናትና የሌዋውያን ስም ዝርዝር ከዚህ የሚከተለው ነው፤

2-7 ካህናት፦ ሠራያ፥ ኤርምያስ፥ ዕዝራ፥ አማርያ፥ ማሉክ፥ ሐጡሽ፥ ሸካንያ፥ ረሑም፥ መሬሞት፥ ዒዶ፥ ጊነቶን፥ አቢያ፥ ሚያሚን፥ መዓድያ፥ ቢልጋ፥ ሸማዕያ፥ ዮያሪብ፥ ይዳዕያ፥ ሳሉ፥ ዓሞክ፥ ሒልቂያና ይዳዕያ። እነዚህ ሰዎች በሊቀ ካህናቱ በኢያሱ ዘመን የወገኖቻቸው ካህናት መሪዎች የነበሩ ናቸው።

8 ሌዋውያን፦ የምስጋና መዝሙር ኀላፊዎች የነበሩት ሌዋውያን ኢያሱ፥ ቢኑይ፥ ቃድሚኤል፥ ሼሬብያ፥ ይሁዳና ማታንያ ነበሩ።

9 ባቅቡቅያ፥ ዑኖና ሌሎችም ሌዋውያን ወንድሞቻቸው ከእነርሱ ጋር በመቀባበል ይዘምሩ ነበር።


የሊቀ ካህናቱ የኢያሱ ዘሮች

10 ኢያሱ ዮያቂምን ወለደ፤ ዮያቂም ኤልያሺብን ወለደ፤ ኤልያሺብ ዮያዳዕን ወለደ፤

11 ዮያዳዕ ዮናታንን ወለደ፤ ዮናታን ያዱዓን ወለደ።


የካህናት ጐሣ አለቆች

12-21 ዮያቂም ሊቀ ካህናት በነበረበት ዘመን ከዚህ የሚከተሉት ካህናት፥ የካህናት ጐሣዎች አለቆች ነበሩ፦ ካህኑ ጐሣው። መራያ ሠራያ። ሐናንያ ኤርምያስ። መሹላም ዕዝራ። የሆሐናን አማርያ። ዮናታን መሉኪ። ዮሴፍ ሸካንያ። ዓድና ሓሪም። ሔልቃይ መራዮት። ዘካርያስ ዒዶ። መሹላም ጊነቶን። ዚክሪ አቢያ። ሚንያሚን ፒልጣይ ሞዓዲያ። ሻሙዐ ቢልጋ። የሆናታን ሸማዕያ። ማትናይ ዮያሪብ። ዑዚ ይዳዕያ። ቃላይ ሳላይ። ዔቤር ዓሞቅ። ሐሻብያ ሒልቂያ። ናትናኤል ይዳዕያ።


የካህናትንና የሌዋውያንን ቤተሰቦች ስም ዝርዝር የሚገልጥ መዝገብ

22 ኤልያሺብ፥ ዮያዳዕ፥ ዮናታንና ያዱዐ ተብለው የሚጠሩት ሊቃነ ካህናት በኖሩበት ዘመን የሌዋውያንና የካህናት ቤተሰብ አለቆች ተለይተው የሚታወቁበት መዝገብ ተዘጋጅቶ ነበር፤ ይህም መዝገብ የተዘጋጀው ዳርዮስ የፋርስ ንጉሠ ነገሥት በሆነበት ዘመን ነበር።

23 ይሁን እንጂ የሌዋውያን ቤተሰብ አለቆች በግልጽ መዝገብ የታወቁት የኤልያሺብ የልጅ ልጅ የሆነው ዮናታን በሕይወት እስከ ኖረበት ዘመን ብቻ ነበር።


በቤተ መቅደስ የአገልግሎት አመዳደብ

24 ሌዋውያኑ በሐሻብያ፥ በሼሬብያ፥ በኢያሱ፥ በቢኑይና በቃድሚኤል መሪነት በሁለት ቡድኖች ተከፈሉ። ሁለቱም ቡድኖች የእግዚአብሔር ሰው የሆነ ንጉሥ ዳዊት በሰጠው ትእዛዝ መሠረት እየተቀባበሉ የምስጋና መዝሙር በማቅረብ እግዚአብሔርን ያመሰግኑ ነበር።

25 በቤተ መቅደሱ ቅጽር በር አጠገብ የተሠሩትን የዕቃ ግምጃ ቤቶች የሚጠብቁ ዘበኞችም ማታንያ፥ ባቅቡቅያ፥ አብድዩ፥ መሹላም፥ ጣልሞንና ዓቁብ ተብለው የሚጠሩት ነበሩ።

26 እነዚህም የኢዮጼዴቅ የልጅ ልጅ የሆነው የኢያሱ ልጅ ዮያቂም፥ አገረ ገዢው ነህምያ ካህኑና የሕግ ሊቁ ዕዝራ በነበሩበት ዘመን የተመደቡ አገልጋዮች ነበሩ።


ለኢየሩሳሌም ከተማ ቅጽር የምረቃ በዓል መደረጉ

27 የኢየሩሳሌም ከተማ ቅጽር የምረቃ በዓል በተከበረበት ዕለት ሌዋውያኑ በጸናጽል፥ በበገናና በመሰንቆ በዓሉን እንዲያከብሩ ከየሚኖሩበት ስፍራ ተፈልገው መጡ።

28 ይህንንም በዓል ለማክበር የሌዋውያኑ ቤተሰቦች መዘምራን ሁሉ ሰፍረው ከነበሩበት ከኢየሩሳሌም አካባቢና በነጦፋ ከሚገኙት ታናናሽ ከተሞች፥

29 ከቤትጊልጋል፥ ከጌባዕና ከዓዝማዌት ተሰብስበው መጡ፤

30 ካህናቱና ሌዋውያኑም ስለ ሕዝቡ ራሳቸው ስለ ከተማይቱ በሮችና ስለ ቅጽሩ የማንጻትን ሥርየት ፈጸሙ።

31 እኔም ነህምያ የይሁዳን መሪዎች በቅጽሩ ላይ እንዲወጡ ካደረግሁ በኋላ ሁለት ታላላቅ የመዘምራን ቡድን የምስጋና መዝሙር እንዲዘምሩ አደረግሁ፤ የመጀመሪያው ቡድን በቅጽሩ ግንብ አናት ላይ በስተቀኝ በኩል ወደሚገኘው ወደ ጒድፍ መጣያው የቅጽር በር በኩል አለፈ፤

32 ሆሻዕያና የይሁዳ መሪዎች ተከተሉአቸው።

33-35 ዐዛርያ፥ ዕዝራ፥ መሹላም፥ ይሁዳ፥ ብንያም፥ ሸማዕያና ኤርምያስ ተብለው የሚጠሩት ካህናትም በሰልፍ አለፉ፤ ቀጥሎም እምቢልታ የሚነፉ ጥቂት ካህናትና እንዲሁም ዘካርያስ የዮናታን ልጅ የሸማዕያ ልጅ፥ የማታንያ ልጅ፥ የሚክያን ልጅ፥ የዛኩር ልጅ የአሳፍ ልጅ አለፉ።

36 የራሱ ጐሣ አባላት የነበሩት ሸማዕያ፥ ዐዛርኤል፥ ሚለላይ፥ ጊለላይ፥ ማዓይ፥ ናትናኤል፥ ይሁዳና ሐናኒ የእግዚአብሔር ሰው ዳዊት ይዘምርበት የነበረውን የሙዚቃ መሣሪያ ሁሉ ተሸክመው ተከተሉት፤ የዚህንም ቡድን ሰልፍ የሚመራው የሕግ ሊቁ ዕዝራ ነበር።

37 ወደ ውሃው ምንጭ በር እንደ ደረሱም ወደ ዳዊት ከተማ አቅንተው በቅጽሩ ላይ ያሉትን ደረጃዎች በመውጣትና የዳዊትን ቤተ መንግሥት በማለፍ ከከተማይቱ በስተምሥራቅ ወደሚገኘው ወደ ውሃ ቅጽር በር ተመለሱ።

38 ሌላው የመዘምራን ቡድን ሰልፍ የቅጽሩን ግንብ ጫፍ በመከተል ወደ ግራ በኩል አለፈ፤ እኔም ከሕዝቡ እኩሌታ ጋር ይህንኑ የቡድን ሰልፍ እከተል ነበር፤ የእቶኑንም ግንብ አልፈን ወደ ሰፊው ቅጽር ግንብ ደረስን።

39 ከዚያም አልፈን የኤፍሬም ቅጽር በር፥ የይሻና ቅጽር በር፥ የዓሣ ቅጽር በር ተብለው ወደተሰየሙትና የሐናንኤል ግንብ የመቶዎቹ ግንብና የበጎች ቅጽር በር ተብለው ወደሚጠሩት ስፍራዎች መጣን፤ ሰልፋችንንም ያበቃነው ለቤተ መቅደሱ ቅርብ ወደ ሆነው የዘበኞች ቅጽር በር ወደሚባለው ቦታ ስንደርስ ነበር።

40 በዚህም ሁኔታ የሁለቱም ቡድኖች ሰልፍ እግዚአብሔርን በመዝሙር በማመስገን ወደ ቤተ መቅደሱ ክልል ደረሰ፤ አብረውኝም ከነበሩት መሪዎች ጋር በተጨማሪ፥

41 የእኔ ቡድን ሰልፍ ከዚህ የሚከተሉትን እምቢልታ የሚነፉ ካህናትን የሚጨምር ነበር፤ እነርሱም ኤልያቄም፥ መዕሤያ፥ ሚንያሚን፥ ማካያ፥ ኤልዮዔናይ፥ ዘካርያስና ሐናንያ ሲሆኑ፥

42 እነርሱንም ደግሞ መዕሤያ፥ ሸማዕያ፥ አልዓዛር፥ ዑዚ፥ የሆሐናን፥ ማልኪያ፥ ኤላምና ኤዜር ተከትለዋቸው ይጓዙ ነበር፤ እንደ ቆምንም መዘምራኑ በይዝራሕያ እየተመሩ ድምፃቸውን ከፍ በማድረግ ዘመሩ።

43 በዚያም ዕለት ብዙ መሥዋዕት ቀረበ፤ ሕዝቡም እግዚአብሔር ደስ ስላሰኛቸው ታላቅ ሐሴት አደረጉ፤ ሴቶችም፥ ልጆችም አብረው ተደስተዋል፤ በኢየሩሳሌም የነበረው የእልልታቸው ድምፅ እስከ ሩቅ ድረስ ይሰማ ነበር።


ለቤተ መቅደስ መገልገያ የሚቀርብ አስተዋጽዖ

44 በዚያም ጊዜ ለቤተ መቅደስ መገልገያ የሚደረገውን አስተዋጽዖ እንዲሁም ከዐሥር አንዱን፥ በየዓመቱ በመጀመሪያ የሚደርሰውን እህልና ፍራፍሬ በማከማቸት የዕቃ ቤት ክፍሎችን የሚጠብቁ ኀላፊዎች ተሾሙ፤ እነዚህም ሰዎች በልዩ ልዩ ከተሞች አቅራቢያ ከሚገኙ የእርሻ ቦታዎች ሕጉ በሚያዝዘው መሠረት ለካህናቱና ለሌዋውያኑ የተመደበውን አስተዋጽዖ የመሰብሰብ ኀላፊነት ነበራቸው፤ የይሁዳም ሕዝብ በሙሉ በካህናቱና በሌዋውያኑ እጅግ ደስ ብሎአቸው ነበር።

45 የይሁዳም ሕዝብ ተደስቶ የነበረው እነርሱ እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት መፈጸም የሚገባውን ደንብና የማንጻት ሥርዓት በማከናወናቸው ነበር፥ የቤተ መቅደሱ መዘምራንና የቤተ መቅደሱ ዘብ ጠባቂዎችም ዳዊትና ልጁ ሰሎሞን በመደቡት ሥርዓት መሠረት የሚጠበቅባቸውን አገልግሎት ፈጸሙ።

46 ከንጉሥ ዳዊትና የመዘምራን አለቃ ከነበረው አሳፍ ዘመንም ጀምሮ ለመዘምራንና ለማኅሌታዊ ዜማ መሪዎች ነበሩአቸው።

47 በዘሩባቤልና በነህምያ ዘመን መላው እስራኤላውያን ለቤተ መቅደሱ መዘምራንና ለዘብ ጠባቂዎቹ የየዕለት ድርሻቸውን ይሰጡ ነበር፤ ሌዋውያኑም የአሮን ተወላጁን ድርሻ ይሰጡ ነበር።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos