ነህምያ 11 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምበኢየሩሳሌም የሚኖሩ ሕዝቦች 1 መሪዎቹ መኖሪያቸውን በኢየሩሳሌም አደረጉ፤ ከሌላውም ሕዝብ መካከል ከየዐሥር ቤተሰብ አንዱ እጅ ቅድስት በሆነችው በኢየሩሳሌም ከተማ እንዲኖር በዕጣ ተመረጠ፤ የቀሩት ሰዎች ግን በሌሎች መንደሮችና ከተሞች ሁሉ ኑሮአቸውን መሠረቱ፤ 2 ሕዝቡም በኢየሩሳሌም ውስጥ ለመኖር የበጎ ፈቃድ ዝንባሌ ያለውን ሰው ሁሉ አመሰገነ። 3 በሌሎች መንደሮችና ከተሞች የሚኖሩ የእስራኤል ልጆች ካህናቱና ሌዋውያኑ የቤተ መቅደሱ አገልጋዮችና የሰሎሞን አገልጋዮች ዘሮች በየመንደሮቻቸው ባላቸው ይዞታ ኖሩ። በኢየሩሳሌም የሚኖሩ የይሁዳ ምድር መሪዎችም ስም ዝርዝር የሚከተለው ነበር፦ 4 የይሁዳ ነገድ አባላት፦ የዘካርያስ የልጅ ልጅ የሆነው የዑዚያ ልጅ ዐታያ፤ ሌሎች የቀድሞ አያቶቹ የይሁዳ ልጅ የሆነው የፋሬስ ዘሮች የሆኑትን አማርያን፥ ሸፋጥያንና ማሀላልኤልን ይጨምራሉ። 5 የኮልሖዜ የልጅ ልጅ የሆነው የባሩክ ልጅ ማዕሤያ ሌሎች የቀድሞ አባቶቹ የይሁዳ ልጅ የነበረው የሼላ ዘሮች የሆኑትን ሐዛያን፥ ዓዳያን፥ የዮያሪብንና ዘካርያስን ይጨምራል። 6 ከፋሬስ ዘሮች መካከል በጀግንነታቸው ታዋቂዎች የሆኑ 468 ሰዎች በኢየሩሳሌም ነዋሪዎች ሆኑ። 7 የብንያም ነገድ አባላት፦ ሳሉ፥ የመሹላም ልጅ፥ የዮዔድ ልጅ፥ የፐዳያ ልጅ፥ የቆላያን ልጅ፥ የማዕሤያን ልጅ፥ የኢቲኤልን ልጅ፥ የሻዕያን ልጅ፥ 8 የሳሉ የቅርብ ዘመዶች የሆኑ፦ ጋባይና ሳላይ፥ በድምሩ 928 ብንያማውያን በኢየሩሳሌም ይኖሩ ነበር። 9 የዚክሪ ልጅ ኢዩኤል መሪያቸው ሲሆን፥ የሀስኑአ ልጅ ይሁዳ በማዕርግ ሁለተኛ የሆነ የከተማይቱ ባለሥልጣን ነበር። 10 ካህናት፦ ይዳዕያ የዩያሪብ ልጅ፥ የያኪን ልጁ፥ 11 ሠራያ፥ የሒልቅያ ልጅ፥ የመሹላም ልጅ፥ የጻዶቅ ልጅ፥ የመራዮት ልጅ፥ የእግዚአብሔር ቤት አለቃ የነበረው የአሒጡብ ልጅ፥ 12 ከዚህም ጐሣ ውስጥ በአጠቃላይ 822 አባላት በቤተ መቅደስ ውስጥ አገልጋዮች ነበሩ። ዓደያ የየሮሖም ልጅ፥ የፐላልያ ልጅ፥ የአምጺን ልጅ፥ የዘካርያስ ልጅ፥ የፓሽሑር ልጅ፥ የማልኪያን ልጅ፥ 13 ከዚህም ጐሣ ውስጥ ባጠቃላይ 242 የቤተሰብ መሪዎች ነበሩ። አማሽሳይ የዐዛርኤል ልጅ፥ የአሕዛይ ልጅ፥ የመሺሌሞት ልጅ፥ የኢሜር ልጅ፥ 14 የእርሱም ወንድሞች ስመጥር ወታደሮች የሆኑት አባላት ብዛት 128 ነበር፤ መሪያቸውም ዛብድኤል ተብሎ የሚጠራ የሐጌዶሊም ልጅ ነበር። 15 ሌዋውያን፦ ሸማዕያ የሐሹብ ልጅ፥ የዓዝሪቃም ልጅ፥ የሐሻብያን ልጅ፥ የቡኒን ልጅ፥ 16 ሻበታይና ዮዛባድ ተብለው የሚጠሩ የሌዋውያን መሪዎች ከቤተ መቅደስ በስተውጭ ለሚሠራው ነገር ሁሉ ኀላፊዎች ነበሩ። 17 ማታንያ የሚካ ልጅ፥ የዘብዲ ልጅ፥ የመዘምራን አለቃ የነበረው የአሳፍ ልጅ፥ የእርሱ ምክትል የነበረው የባቅቡቅያ ልጅና፥ የሻሙዐ ልጅ የነበረው ዐብዳ፥ የጋላል ልጅ፥ የዩዱቱን ልጅ፥ 18 ከሌዋውያኑም ወገን በአጠቃላይ 284 ሰዎች በቅድስቲቱ በኢየሩሳሌም ከተማ ይኖሩ ነበር። 19 የቤተ መቅደስ ዘበኞች፦ ዓቁብ፥ ጣልሞንና ዘመዶቻቸው በአጠቃላይ 172 ነበሩ። 20 በተረፈ ሌሎቹ እስራኤላውያን፥ ካህናትና ሌዋውያን በየርስታቸው በሌሎቹ የይሁዳ ከተሞችና መንደሮች ይኖሩ ነበር። 21 የቤተ መቅደሱ አገልጋዮች የኢየሩሳሌም ከተማ አንዱ ክፍል በሆነው ዖፌል ተብሎ በሚጠራው ኮረብታ ላይ ይኖሩ ነበር፤ ጺሐና ጊሽፓ ተብለው የሚጠሩም ሰዎች የእነርሱ አለቆች ነበሩ። 22 በኢየሩሳሌም የሌዋውያን አለቃ ዑዚ የባሂ ልጅ፥ የሖሻብያ ልጅ፥ የማታንያ ልጅ፥ የሚካ ልጅ ነበር። ዑዚ የቤተ መቅደስ መዘምራን ኀላፊ የነበረው የአሳፍ ዘር ነበር። 23 በየዕለቱ የሚቀርበውንም መዝሙር ቅደም ተከተል ተራ በማስያዝ ረገድ ከንጉሡ የተሰጠ ትእዛዝ ነበር። 24 ከይሁዳ ነገድ የዛራ ጐሣ ተወላጅ የሆነው የመሼዛቤል ልጅ ፐታሕያ የእስራኤልን ሕዝብ በሚመለከት ጉዳይ የፋርስ ንጉሥ እንደ ራሴ ነበር። በሌሎች መንደሮችና ከተሞች የሚኖር ሕዝብ 25 መንደሮቹንና እርሻዎቹን በተመለከተ ከይሁዳ ነገድ መካከል አንዳንዶቹ በቂርያት አርባዕና በመንደሮችዋ፥ በጊቦንና በመንደሮችዋ በይቀብጽኤልና በመንደሮችዋ፥ 26 እንዲሁም ኢያሱ፥ ሞላዳ፥ ቤትጳሌጥና፥ 27 ሐጻርሹዓል ተብለው በሚጠሩ ከተሞች ይኖሩ ነበር፤ ቤርሳቤህና በዙሪያዋ የሚገኙ መንደሮችም የእነርሱ መኖሪያዎች ነበሩ፤ 28 በጺቅላግ ከተማም በተለይ በመኮናና በአካባቢዋ በሚገኙት መንደሮች፥ 29 በዔንሪሞን፥ በጸርዓ፥ በያርሙት፥ 30 በዛኖሐ፥ በዐዱላምና በእነዚህም ከተሞች አጠገብ በሚገኙት መንደሮች ሁሉ ይኖሩ ነበር፤ ላኪሽና በአቅራቢያዋ የሚገኙ የእርሻ ቦታዎች፥ ዐዜቃና የአካባቢዋ መንደሮች ሁሉ የእነርሱ መኖሪያዎች ነበሩ፤ በዚህ ዐይነት የይሁዳ ሕዝብ መኖሪያ በደቡብ ከቤርሳቤህ፥ በሰሜን ከሂኖም ሸለቆ በመለስ ባለው ክልል ውስጥ ነበር። 31 የብንያም ነገድ ተወላጆች መኖሪያዎች ደግሞ በጌባዕ፥ በሚክማስ፥ በዐይ፥ በቤትኤልና በአካባቢዋ በሚገኙ መንደሮች ነበር፤ 32 ዐናቶት፥ ኖብ፥ ዓናንያ፥ 33 ሐጾር፥ ራማ፥ ጊታይም፥ 34 ሐዲድ፥ ጸቦዒም፥ ነባላጥ፥ 35 ሎድና፥ ኦኖ፥ እንዲሁም “የእጅ ጥበብ ሠራተኞች ሸለቆ” ተብሎ የሚጠራው ስፍራ ሁሉ የእነርሱ መኖሪያዎች ነበሩ። 36 በይሁዳ ክፍለ ግዛት ከሚኖሩት የሌዋውያን ቡድኖች መካከል አንዳንዶቹ ከብንያም ሕዝብ ጋር እንዲኖሩ ተደረገ። |