ማቴዎስ 28 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየኢየሱስ ከሞት መነሣት ( ማር. 16፥1-10 ፤ ሉቃ. 24፥1-12 ፤ ዮሐ. 20፥1-10 ) 1 ሰንበት ካለፈ በኋላ ከሳምንቱ በመጀመሪያው ቀን (እሑድ) ጠዋት፥ በማለዳ መግደላዊት ማርያምና ሌላይቱ ማርያም መቃብሩን ለማየት ሄዱ። 2 እነሆ፥ በድንገት ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ፤ የጌታ መልአክ ከሰማይ ወርዶ መቃብሩ የተዘጋበትን ድንጋይ አንከባለለና በላዩ ተቀመጠ። 3 የመልአኩ ፊት እንደ መብረቅ ያበራ ነበር፤ ልብሱም እንደ በረዶ ነጭ ነበረ። 4 ጠባቂዎቹ መልአኩን ከመፍራት የተነሣ በመንቀጥቀጥ እንደ በድን ሆኑ፤ 5 መልአኩ ግን ሴቶቹን እንዲህ አላቸው፤ “እናንተስ አትፍሩ፤ የተሰቀለውን ኢየሱስን እንደምትፈልጉ ዐውቃለሁ፤ 6 እርሱ እዚህ የለም ቀደም ብሎ እንደ ተናገረው ተነሥቶአል። እዚህ የለም፤ ተቀብሮበት የነበረበትን ስፍራ ኑና እዩ። 7 እንግዲህ በፍጥነት ሄዳችሁ ለደቀ መዛሙርቱ ‘ከሞት ተነሥቶአል! እነሆ፥ ወደ ገሊላ ቀድሞአችሁ ይሄዳል፤ በዚያ ታገኙታላችሁ!’ ብላችሁ ንገሩአቸው፤ እነሆ፥ ነግሬአችኋለሁ።” 8 ከዚህ በኋላ ሴቶቹ በፍርሃትና በታላቅ ደስታ ከመቃብሩ በፍጥነት ሄዱ፤ ለደቀ መዛሙርቱም ሊነግሩ ሮጡ። 9 ኢየሱስ በመንገድ አገኛቸውና “ሰላም ለእናንተ ይሁን!” አላቸው። እነርሱም ወደ እርሱ ቀረቡና እግሮቹን ይዘው ሰገዱለት። 10 በዚያን ጊዜ ኢየሱስ፦ “አትፍሩ! ሂዱና ወደ ገሊላ እንዲሄዱ ለወንድሞቼ ንገሩአቸው፤ የሚያዩኝም በዚያ ነው” አላቸው። 11 ሴቶቹም ሲሄዱ ሳሉ ከወታደሮቹ አንዳንዶቹ ወደ ከተማ ሄደው የሆነውን ነገር ሁሉ ለካህናት አለቆች ነገሩ። 12 የካህናት አለቆች ከሽማግሌዎች ጋር ተሰብስበው ከተማከሩ በኋላ ለወታደሮቹ ብዙ ገንዘብ ሰጡአቸውና እንዲህ አሉአቸው፤ 13 “ ‘እኛ ተኝተን ሳለ ደቀ መዛሙርቱ በሌሊት መጥተው ሰርቀው ይዘውት ሄዱ’ ብላችሁ ለሕዝቡ ንገሩ። 14 ይህን አገር ገዢው የሰማ እንደ ሆነ እኛ ጉዳዩን ለእርሱ አስረድተን በማሳመን በእናንተ ላይ ችግር እንዳይደርስባችሁ እናደርጋለን። ” 15 ስለዚህ ወታደሮቹ ገንዘቡን ተቀብለው ልክ እንደ ተነገራቸው አደረጉ፤ ይህም ነገር እስከ ዛሬ ድረስ በአይሁድ ዘንድ ተስፋፍቶ ይነገራል። ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንደ ተገለጠ ( ማር. 16፥14-18 ፤ ሉቃ. 24፥36-49 ፤ ዮሐ. 20፥19-23 ፤ ሐ.ሥ. 1፥6-8 ፤ 1ቆሮ. 15፥3-8 ) 16 ዐሥራ አንዱ ደቀ መዛሙርት ኢየሱስ እንዲሄዱ ወደ አመለከታቸው፥ በገሊላ ወደሚገኘው ተራራ ሄዱ። 17 ባዩትም ጊዜ ሰገዱለት፤ አንዳዶቹ ግን ተጠራጠሩ፤ 18 ኢየሱስ ወደ እነርሱ ቀረበና እንዲህ አላቸው፤ “ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጥቶኛል፤ 19 እንግዲህ ወደ ዓለም ሕዝብ ሁሉ ሂዱ፤ በአብ፥ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው የእኔ ደቀ መዛሙርት አድርጉአቸው። 20 ያዘዝኳችሁንም ሁሉ እንዲፈጽሙ አስተምሩአቸው! እነሆ፥ እኔም እስከ ዓለም መጨረሻ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።” |