ማቴዎስ 17 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየኢየሱስ መልክ መለወጥ ( ማር. 9፥2-13 ፤ ሉቃ. 9፥28-36 ) 1 ከስድስት ቀን በኋላ ኢየሱስ ጴጥሮስን፥ ያዕቆብንና የያዕቆብን ወንድም ዮሐንስን ብቻ አስከትሎ፥ ለብቻው ወደ አንድ ከፍተኛ ተራራ ላይ ወጣ። 2 እዚያ በፊታቸው መልኩ ተለወጠ፤ ፊቱም እንደ ፀሐይ አበራ፤ ልብሱም ነጭ ሆኖ እንደ ብርሃን አንጸባረቀ። 3 እነሆ፥ ሙሴና ኤልያስ ከኢየሱስ ጋር ሲነጋገሩ ታዩአቸው። 4 በዚያን ጊዜ ጴጥሮስ ኢየሱስን “ጌታ ሆይ! እዚህ ብንኖር ለእኛ መልካም ነው፤ ስለዚህ ብትፈቅድስ አንድ ለአንተ፥ አንድ ለሙሴ፥ አንድ ለኤልያስ የሚሆኑ ሦስት ዳሶች ልሥራ” አለው። 5 ጴጥሮስ ገና ይህን ሲናገር ሳለ ብሩህ ደመና ጋረዳቸው፤ ከደመናውም ውስጥ “በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው፤ እርሱን ስሙት!” የሚል ድምፅ መጣ። 6 ደቀ መዛሙርቱም ይህን ድምፅ በሰሙ ጊዜ እጅግ ስለ ደነገጡ በግንባራቸው በመሬት ላይ ተደፉ። 7 ኢየሱስ ግን ወደ እነርሱ ቀርቦ በእጁ ዳሰሳቸውና “ተነሡ፤ አትፍሩ!” አላቸው። 8 እነርሱም ቀና ብለው ሲመለከቱ ከኢየሱስ በቀር ማንንም አላዩም። 9 ከተራራው ሲወርዱ ሳሉ ኢየሱስ፦ “የሰው ልጅ ከሞት እስኪነሣ ድረስ ይህን ያያችሁትን ለማንም አትንገሩ” ሲል ደቀ መዛሙርቱን አዘዛቸው። 10 ደቀ መዛሙርቱም “ታዲያ፥ የሕግ መምህራን አስቀድሞ መምጣት ያለበት ኤልያስ ነው ለምን ይላሉ?” ሲሉ ኢየሱስን ጠየቁት። 11 ኢየሱስ እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “እርግጥ ነው፤ ኤልያስማ አስቀድሞ ይመጣል፤ እርሱ ሁሉንም ያስተካክላል። 12 ነገር ግን ኤልያስ ገና ዱሮ መጥቶአል እላችኋለሁ፤ ሰዎች ግን አላወቁትም፤ ስለዚህ የፈለጉትን ሁሉ አደረጉበት። እንዲሁም ደግሞ የሰው ልጅ በእነርሱ እጅ መከራን መቀበል አለበት።” 13 በዚያን ጊዜ ደቀ መዛሙርቱ ኢየሱስ የተናገረው ስለ መጥምቁ ዮሐንስ መሆኑ ገባቸው። ኢየሱስ ጋኔን ያደረበትን ልጅ መፈወሱ ( ማር. 9፥14-29 ፤ ሉቃ. 9፥37-43 ) 14 ኢየሱስና ሦስቱ ደቀ መዛሙርት ወደ ሕዝቡ በተመለሱ ጊዜ አንድ ሰው ወደ ኢየሱስ መጥቶ በእግሩ ሥር ተንበረከከና እንዲህ አለ፦ 15 “ጌታ ሆይ! እባክህ ለልጄ ራራለት፤ የሚጥል የጋኔን በሽታ ክፉኛ ያሠቃየዋል፤ በእሳት ላይና በውሃ ውስጥ ብዙ ጊዜ ይወድቃል። 16 ወደ ደቀ መዛሙርትህም አምጥቼው ነበር፤ ነገር ግን ሊፈውሱት አልቻሉም።” 17 ኢየሱስም “እናንተ የማታምኑ ጠማማ ትውልድ! እስከ መቼ ከእናንተ ጋር እኖራለሁ? እስከ መቼስ እታገሣችኋለሁ? እስቲ ልጁን ወደ እኔ አምጡት!” አላቸው። 18 ኢየሱስ ጋኔኑን ገሠጸው፤ ጋኔኑም ከልጁ ወጣ፤ ልጁም በዚያኑ ሰዓት ተፈወሰ። 19 ከዚህ በኋላ ደቀ መዛሙርቱ ብቻቸውን ወደ ኢየሱስ ቀርበው፦ “እኛ ጋኔኑን ለማውጣት ያልቻልነው ስለምንድን ነው?” ሲሉ ጠየቁት። 20 ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፦ “እምነታችሁ ጐደሎ ስለ ሆነ ነው፤ በእውነት እላችኋለሁ፤ የሰናፍጭ ቅንጣት የሚያኽል እምነት ቢኖራችሁ ይህን ተራራ ‘ከዚህ ተነሥተህ ወዲያ ሂድ!’ ብትሉት ይሄዳል፤ የሚሳናችሁም ምንም ነገር አይኖርም። 21 እንዲህ ዐይነቱ ጋኔን ግን በጸሎትና በጾም ካልሆነ በቀር ከቶ አይወጣም።” ኢየሱስ ስለ ሞቱና ከሞት ስለ መነሣቱ ሁለተኛ ጊዜ እንደ ተናገረ ( ማር. 9፥30-32 ፤ ሉቃ. 9፥43-45 ) 22 ደቀ መዛሙርቱ በገሊላ በተሰበሰቡ ጊዜ ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ “የሰው ልጅ በሰዎች እጅ ተላልፎ ይሰጣል፤ 23 እነርሱ ይገድሉታል፤ ነገር ግን በሦስተኛው ቀን ከሞት ይነሣል።” ደቀ መዛሙርቱም በዚህ ነገር እጅግ አዘኑ። የቤተ መቅደስ ግብር ስለ መክፈል 24 ኢየሱስና ደቀ መዛሙርቱ ወደ ቅፍርናሆም በደረሱ ጊዜ የቤተ መቅደስ ግብር ተቀባዮች ወደ ጴጥሮስ ቀረቡና፥ “መምህራችሁ የቤተ መቅደስ ግብር አይከፍልምን?” ሲሉ ጠየቁት። 25 ጴጥሮስም “ኧረ ይከፍላል” አላቸው። ጴጥሮስ ወደ ቤት በገባ ጊዜ ኢየሱስ አስቀድሞ “ስምዖን ጴጥሮስ ሆይ! ምን ይመስልሃል? የዚህ ዓለም መንግሥታት ቀረጥና ግብር የሚቀበሉት ከማን ነው? ከልጆቻቸው ነውን ወይስ ከውጪ አገር ሰዎች?” ሲል ጠየቀው። 26 ጴጥሮስም “ከውጪ አገር ሰዎች ነው” ሲል መለሰ። ኢየሱስም እንዲህ አለ፦ “እንግዲያውስ ልጆቻቸው ግብር ከመክፈል ነጻ ናቸው ማለት ነዋ? 27 ነገር ግን ለእነርሱ እንቅፋት እንዳንሆንባቸው ወደ ባሕር ሂድና መንጠቆ ጣል፤ በመጀመሪያ የሚወጣውን ዓሣ ያዝ፤ አፉንም ስትከፍት በውስጡ ገንዘብ ታገኛለህ፤ ያንንም ወስደህ ስለ እኔና ስለ አንተ ክፈል።” |