ማርቆስ 2 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምኢየሱስ ሽባውን ሰው መፈወሱ ( ማቴ. 9፥1-8 ፤ ሉቃ. 5፥17-26 ) 1 ከጥቂት ቀን በኋላ ኢየሱስ ወደ ቅፍርናሆም ተመልሶ መጣ፤ እዚያ በቤት ውስጥ መሆኑ ተሰማ። 2 ቤቱ የማይበቃ ሆኖ ደጁ እንኳ እስኪጠብ ድረስ ብዙ ሰዎች ተሰበሰቡ፤ ቃሉንም ያስተምራቸው ነበር። 3 በዚያን ጊዜ አራት ሰዎች አንድ ሽባ ሰው ተሸክመው ወደ እርሱ መጡ። 4 ከሕዝቡም ብዛት የተነሣ ሽባውን ወደ ኢየሱስ ማቅረብ ቢያቅታቸው የቤቱን ጣራ ኢየሱስ ባለበት በኩል ከፍተው ሽባውን ከነአልጋው አወረዱት። 5 ኢየሱስም እምነታቸውን አይቶ ሽባውን “ልጄ ኃጢአትህ ይቅር ተብሎልሃል” አለው። 6 በዚያ ተቀምጠው የነበሩ አንዳንድ የሕግ መምህራን በልባቸው እንዲህ አሉ፤ 7 “ይህ ሰው ለምን እንዲህ ያለ ስድብ በእግዚአብሔር ላይ ይናገራል? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ኃጢአትን ይቅር ማለት የሚችል ማን ነው?” 8 ወዲያውኑ ኢየሱስ ይህን የልባቸውን ሐሳብ በመንፈሱ ዐውቆ እንዲህ አላቸው፦ “ስለምን በልባችሁ ይህን ታስባላችሁ? 9 ሽባውን፥ ‘ኃጢአትህ ይቅር ተብሎልሃል፤’ ከማለትና፥ ‘ተነሥተህ አልጋህን ተሸከምና ሂድ!’ ከማለት የትኛው ይቀላል? 10 ነገር ግን የሰው ልጅ በምድር ላይ ኃጢአትን ይቅር ለማለት ሥልጣን ያለው መሆኑን እንድታውቁ” ብሎ ሽባውን፥ 11 “ተነሥ፤ አልጋህን ተሸከምና ወደ ቤትህ ሂድ እልሃለሁ” አለው። 12 ሽባውም ወዲያውኑ ተነሣና አልጋውን ተሸክሞ በሰዎቹ ሁሉ ፊት ወጣ። ስለዚህም ሰዎቹ ሁሉ ተደንቀው እንዲህ ያለ ነገር ከቶ አይተን አናውቅም እያሉ እግዚአብሔርን አመሰገኑ። ኢየሱስ ማቴዎስ የተባለውን ሌዊን መጥራቱ ( ማቴ. 9፥9-13 ፤ ሉቃ. 5፥27-32 ) 13 ኢየሱስም እንደገና ወደ ገሊላ ባሕር አጠገብ ሄደ፤ ሕዝቡም ሁሉ ተሰብስበው ወደ እርሱ መጡና አስተማራቸው። 14 በዚያም ሲያልፍ ሳለ በቀረጥ መቀበያ ስፍራ ተቀምጦ የነበረውን የእልፍዮስን ልጅ ሌዊን አይቶ፥ “ተከተለኝ” አለው፤ እርሱም ተነሥቶ ተከተለው። 15 ከዚህ በኋላ ኢየሱስ በሌዊ ቤት በማእድ ተቀምጦ ነበር፤ ብዙ ሰዎችም ተከትለውት ስለ ነበር ከእነርሱ ብዙ ቀራጮችና ኃጢአተኞች ከኢየሱስና ከደቀ መዛሙርቱ ጋር በገበታ ቀርበው ነበር። 16 ከፈሪሳውያን ወገን የሆኑ የሕግ መምህራን ኢየሱስ ከቀራጮችና ከኃጢአተኞች ጋር ሲበላ አይተው “ከቀራጮችና ከኃጢአተኞች ጋር የሚበላውና የሚጠጣው ስለምንድን ነው?” በማለት ደቀ መዛሙርቱን ጠየቁአቸው። 17 ኢየሱስም ይህን ሰምቶ፦ “በሽተኞች እንጂ ጤነኞች ሐኪም አያስፈልጋቸውም፤ እኔም የመጣሁት ጻድቃንን ሳይሆን ኃጢአተኞችን ወደ ንስሓ ለመጥራት ነው፤” አላቸው። ስለ ጾም የቀረበ ጥያቄ ( ማቴ. 9፥14-17 ፤ ሉቃ. 5፥33-39 ) 18 የዮሐንስ ደቀ መዛሙርትና ፈሪሳውያን ይጾሙ ነበር። አንዳንድ ሰዎች ወደ ኢየሱስ መጥተው፦ “የዮሐንስና የፈሪሳውያን ደቀ መዛሙርት ይጾማሉ፤ የአንተ ደቀ መዛሙርት ግን የማይጾሙት ስለምንድን ነው?” አሉት። 19 ኢየሱስም “ሙሽራው ከእነርሱ ጋር እያለ ሚዜዎች መጾም ይገባቸዋልን? አይደለም! ሙሽራው ከእነርሱ ጋር ሳለ መጾም አይገባቸውም። 20 ነገር ግን ሙሽራው ከእነርሱ የሚወሰድበት ቀን ይመጣል፤ በዚያን ጊዜ ይጾማሉ። 21 “ባረጀ ልብስ ላይ አዲስ ዕራፊ የሚጥፍ የለም፤ ይህ ቢደረግ ግን፥ አዲሱ ዕራፊ አሮጌውን ልብስ በመሸምቀቅ ይቀደዋል፤ ቀዳዳውም ከበፊቱ የባሰ ይሆናል። 22 እንዲሁም በአረጀ የወይን ጠጅ አቁማዳ አዲስ የወይን ጠጅ የሚያኖር የለም፤ ቢደረግ ግን የወይን ጠጁ አቁማዳውን ያፈነዳዋል፤ የወይን ጠጁም ይፈስሳል፤ አቁማዳውም ከንቱ ይሆናል። ስለዚህ ለአዲስ የወይን ጠጅ አዲስ አቁማዳ ያስፈልገዋል፤” አላቸው። ስለ ሰንበት የቀረበ ጥያቄ ( ማቴ. 12፥1-8 ፤ ሉቃ. 6፥1-5 ) 23 በሰንበት ቀን ኢየሱስ በስንዴ እርሻ መካከል ያልፍ ነበር። ደቀ መዛሙርቱ ሲሄዱ የስንዴ እሸት መቅጠፍ ጀመሩ። 24 ፈሪሳውያንም “እነሆ፥ ደቀ መዛሙርትህ በሰንበት ያልተፈቀደውን ስለምን ያደርጋሉ?” ሲሉ ጠየቁት። 25 ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤ “ዳዊት ከተከታዮቹ ጋር በተራበና በተቸገረ ጊዜ ምን እንዳደረገ አላነበባችሁምን? 26 አብያታር የካህናት አለቃ በነበረበት ዘመን እርሱ ወደ እግዚአብሔር ቤት ገብቶ፥ ከካህናት በቀር ለሌሎች መብላት ያልተፈቀደውን፥ የተቀደሰውን የመባ ኅብስት በላ፤ ከእርሱም ጋር ለነበሩት ሰዎች ሰጣቸው።” 27 ደግሞም ኢየሱስ እንዲህ አላቸው፦ “ሰንበት ለሰው ተሠራ እንጂ ሰው ለሰንበት አልተፈጠረም። 28 እንዲሁም የሰው ልጅ ለሰንበትም ጌታዋ ነው።” |