ማርቆስ 16 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየኢየሱስ ከሞት መነሣት ( ማቴ. 28፥1-8 ፤ ሉቃ. 24፥1-12 ፤ ዮሐ. 20፥1-10 ) 1 የሰንበት ቀን ካለፈ በኋላ መግደላዊት ማርያም፥ የያዕቆብ እናት ማርያም ሰሎሜም ሆነው፥ የኢየሱስን አስከሬን ለመቀባት ከመልካም ቅመም የተዘጋጀ ሽቶ ገዙ። 2 ከሳምንቱ በመጀመሪያው ቀን እሑድ ጧት በማለዳ፥ ልክ ፀሐይ ስትወጣ፥ ወደ መቃብሩ ሄዱ። 3 እነርሱ “ድንጋዩን ከመቃብሩ ደጃፍ ማን አንከባሎ ይከፍትልናል?” በማለት እየተነጋገሩ ይሄዱ ነበር። 4 ይህንንም ያሉት መቃብሩ የተዘጋበት ድንጋይ እጅግ ትልቅ ስለ ነበረ ነው፤ ቀና ብለውም በተመለከቱ ጊዜ ግን ድንጋዩ ወደ ጐን ተንከባሎ አዩት። 5 ወደ መቃብሩም በገቡ ጊዜ ነጭ ልብስ የለበሰ ጐልማሳ በስተቀኝ በኩል ተቀምጦ በማየታቸው ደነገጡ። 6 እርሱ ግን እንዲህ አላቸው፦ “አይዞአችሁ፥ አትደንግጡ፤ እናንተ የምትፈልጉት ተሰቅሎ የነበረውን የናዝሬቱን ኢየሱስን እንደ ሆነ ዐውቃለሁ፤ እርሱ ተነሥቶአል፤ እዚህ የለም፤ የተቀበረበትም ቦታ ይኸውላችሁ፤ ተመልከቱ። 7 አሁንም ሂዱ፤ ለደቀ መዛሙርቱና ለጴጥሮስ ‘ከዚህ በፊት ኢየሱስ እንደ ነገራችሁ እርሱ ወደ ገሊላ ቀድሞአችሁ ይሄዳል፤ በዚያም ታዩታላችሁ፤’ ብላችሁ ንገሩአቸው።” 8 ሴቶቹም በፍርሃት እየተንቀጠቀጡ ከመቃብሩ ቦታ ወጥተው ሸሹ፤ እጅግ ፈርተው ስለ ነበር ምንም ነገር ለማንም አልተናገሩም። [ ኢየሱስ ለመግደላዊት ማርያም መገለጡ ( ማቴ. 28፥9-10 ፤ ዮሐ. 20፥11-18 ) 9 ኢየሱስ ከሳምንቱ በመጀመሪያው ቀን (እሑድ) በማለዳ ከሞት ከተነሣ በኋላ፥ መጀመሪያ ሰባት አጋንንት ላወጣላት ለመግደላዊት ማርያም ታየ። 10 እርስዋም ሄዳ፥ በሐዘንና በለቅሶ ላይ ለነበሩት ተከታዮቹ ነገረች። 11 እርስዋ “ኢየሱስ ከሞት ተነሥቶ፥ በሕይወት አለ፤ እኔም በዐይኔ አይቸዋለሁ፤” ብላ ነገረቻቸው፤ እነርሱ ግን አላመኑአትም። ኢየሱስ ለሁለት ደቀ መዛሙርት መታየቱ ( ሉቃ. 24፥13-35 ) 12 ከዚያም በኋላ ወደ ገጠር ይሄዱ ለነበሩ ሁለት ደቀ መዛሙርት ኢየሱስ በሌላ መልክ ታያቸው። 13 እነርሱም ተመልሰው ለቀሩት ደቀ መዛሙርት ነገሩአቸው፤ ደቀ መዛሙርቱ ግን እነዚህንም አላመኑአቸውም። ኢየሱስ ለዐሥራ አንዱ ሐዋርያት መገለጡ ( ማቴ. 28፥16-20 ፤ ሉቃ. 24፥36-49 ፤ ዮሐ. 20፥19-23 ፤ ሐ.ሥ. 1፥6-8 ) 14 ከዚያም በኋላ ዐሥራ አንዱ በማእድ ቀርበው ሲበሉ ኢየሱስ ተገለጠላቸው፤ “ኢየሱስ ከሞት ተነሥቶ በሕይወት አለ፤ በዐይናችንም አይተነዋል፤” ብለው የነገሩአቸውን ባለማመናቸውና በግትርነታቸው ነቀፋቸው። 15 እንዲህም አላቸው፦ “ወደ መላው ዓለም ሂዱ፤ ለሰው ሁሉ ወንጌልን አስተምሩ። 16 ያመነና የተጠመቀ ይድናል፤ የማያምን ግን ይፈረድበታል። 17 በእኔ የሚያምኑ ሁሉ እነዚህን ተአምራት ያደርጋሉ፤ በስሜ አጋንንትን ያወጣሉ፤ በአዲስ ቋንቋም ይናገራሉ፤ 18 እባቦችን ቢይዙ፥ ወይም የሚገድል መርዝ እንኳ ቢጠጡ አይጐዳቸውም፤ እጃቸውን በበሽተኞች ላይ ሲጭኑ በሽተኞቹ ይድናሉ።” ኢየሱስ ወደ ሰማይ ማረጉ ( ሉቃ. 24፥50-53 ፤ ሐ.ሥ. 1፥9-11 ) 19 ጌታ ኢየሱስ ይህን ሁሉ ከነገራቸው በኋላ ወደ ሰማይ ዐረገ። በእግዚአብሔርም ቀኝ ተቀመጠ። 20 ደቀ መዛሙርቱም በየስፍራው ሁሉ እየሄዱ አስተማሩ፤ ጌታም ከእነርሱ ጋር ይሠራ ነበር። ተአምራትንም የማድረግ ሥልጣን በመስጠት የትምህርታቸውን እውነተኛነት ያጸና ነበር።] |