ሉቃስ 19 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምኢየሱስና ዘኬዎስ 1 ኢየሱስ ወደ ኢያሪኮ ከተማ ገብቶ በዚያ በኩል አልፎ እየሄደ ነበር። 2 በዚያም አንድ የቀራጮች አለቃ ዘኬዎስ የሚባል ሀብታም ሰው ነበረ። 3 እርሱ ኢየሱስ የቱ እንደ ሆነ ለማየት ይፈልግ ነበር፤ ነገር ግን ቁመቱ አጭር በመሆኑ ከሕዝቡ ብዛት የተነሣ ሊያየው አልቻለም። 4 ኢየሱስ በዚያ በኩል ያልፍ ስለ ነበር ዘኬዎስ እርሱን ለማየት ብሎ ከሕዝቡ ፊት ቀድሞ ሮጠና በአንድ ሾላ ዛፍ ላይ ወጣ። 5 ኢየሱስም ወደዚያ ስፍራ በደረሰ ጊዜ ቀና ብሎ ተመለከተና ዘኬዎስን፥ “ዘኬዎስ ሆይ! ዛሬ በአንተ ቤት መዋል ይገባኛልና ፈጥነህ ከዛፉ ውረድ” አለው። 6 ዘኬዎስም ቶሎ ብሎ ወረደና፥ በደስታ ኢየሱስን በቤቱ ተቀበለው። 7 ይህን የተመለከቱ ሰዎች ሁሉ “ይህ ሰው ወደ ኃጢአተኛ ቤት ሊጋበዝ ገባ!” ብለው በኢየሱስ ላይ አጒረመረሙ። 8 ዘኬዎስ ግን ቆሞ ጌታ ኢየሱስን እንዲህ አለው፦ “ጌታ ሆይ! እነሆ፥ ካለኝ ሀብት ሁሉ እኩሌታውን ለድኾች እሰጣለሁ፤ በማታለል ከሰው ላይ የወሰድኩትም ገንዘብ ቢኖር፥ አራት እጥፍ አድርጌ እመልሳለሁ።” 9 ኢየሱስም እንዲህ አለ፦ “ይህ ሰው ደግሞ የአብርሃም ዘር ነውና ዛሬ መዳን ለዚህ ቤት ሆኖአል፤ 10 የሰው ልጅ የመጣው የጠፋውን ሊፈልግና ሊያድን ነው።” የዐሥሩ አገልጋዮች ምሳሌ ( ማቴ. 25፥14-30 ) 11 ሰዎቹ ይህን በመስማት ላይ ሳሉ ኢየሱስ አንድ ምሳሌ ደግሞ ነገራቸው፤ እርሱ ወደ ኢየሩሳሌም ስለ ተቃረበ ሰዎቹ የእግዚአብሔር መንግሥት አሁኑኑ የምትገለጥ መስሎአቸው ነበር። 12 ስለዚህ ኢየሱስ እንዲህ አለ፦ “የንጉሥነትን ሥልጣን ተቀብሎ ለመመለስ ወደ ሩቅ አገር የሄደ አንድ መኰንን ነበረ፤ 13 እርሱ ከመሄዱ በፊት ከአገልጋዮቹ ዐሥሩን ጠርቶ ለእያንዳንዱ ዐሥር ምናን ሰጣቸውና ‘ተመልሼ እስክመጣ ድረስ በዚህ ገንዘብ ነግዱ’ አላቸው። 14 የአገሩ ሰዎች ግን ይጠሉት ስለ ነበር፥ ይህ ሰው በእኛ ላይ እንዲነግሥ አንፈልግም ሲሉ እርሱ ከሄደ በኋላ መልእክተኛ ላኩ። 15 “ያ ሰው ንጉሥ ሆኖ በተመለሰ ጊዜ በተሰጣቸው ገንዘብ ነግደው ምን ያኽል እንዳተረፉ ለማወቅ፥ ገንዘብ ሰጥቶአቸው የነበሩትን አገልጋዮቹን አስጠራቸው። 16 የመጀመሪያው አገልጋይ ቀርቦ፦ ‘ጌታ ሆይ! የሰጠኸኝ አንድ ምናን እነሆ፥ ዐሥር ምናን አትርፎአል’ አለው። 17 ጌታውም ‘አንተ መልካም አገልጋይ! ደግ አደረግህ፤ በትንሽ ነገር ስለ ታመንህ እኔ ደግሞ በዐሥር ከተሞች ላይ ሥልጣን ሰጥቼሃለሁ’ አለው። 18 ሁለተኛውም አገልጋይ ቀርቦ ‘ጌታ ሆይ! የሰጠኸኝ ምናን እነሆ! አምስት ምናን አትርፎአል’ አለው። 19 ጌታውም ይህኛውን ‘አንተንም ደግሞ በአምስት ከተሞች ላይ ሾሜሃለሁ’ አለው። 20 “ሌላውም አገልጋይ ቀርቦ እንዲህ አለ፤ ‘ጌታዬ ሆይ! የሰጠኸኝ ገንዘብ ይኸውልህ፤ በጨርቅ ቋጥሬ አስቀምጬው ነበር። 21 ይህንንም ያደረግኹት አንተ ያላስቀመጥከውን የምትወስድ፥ ያልዘራኸውንም የምትሰበስብ፥ ኀይለኛ ሰው መሆንህን ዐውቄ ስለ ፈራሁህ ነው’ አለው። 22 ጌታውም ‘አንተ መጥፎ አገልጋይ! በአነጋገርህ እፈርድብሃለሁ፤ እኔ ያላስቀመጥኩትን የምወስድና ያልዘራሁትን የምሰበስብ ጨካኝ ሰው መሆኔን ዐውቀሃል፤ 23 ታዲያ ገንዘቤን ትርፍ በሚያስገኝልኝ በባንክ ለምን አላስቀመጥከውም ነበር? እኔ ተመልሼ ስመጣ ከነትርፉ እወስደው ነበር’ አለው። 24 ከዚህ በኋላ ጌትዮው፥ በዚያ ቆመው የነበሩትን፦ ‘ምናኑን ከእርሱ ወስዳችሁ ዐሥር ምናን ላለው አገልጋይ ስጡት’ አላቸው። 25 እነርሱም ‘ጌታ ሆይ! እርሱ እኮ ዐሥር ምናን አለው!’ አሉት። 26 ጌትዮውም ‘ላለው ሁሉ ይበልጥ ይሰጠዋል፤ ከሌለው ሰው ግን ያው ያለው እንኳ ይወሰድበታል እላችኋለሁ። 27 በእነርሱ ላይ እንድነግሥ ያልፈለጉትን እነዚያን ጠላቶቼን ግን እዚህ አምጥታችሁ በፊቴ ግደሉአቸው!’ ” አላቸው። 28 ኢየሱስ ይህን ምሳሌ ከተናገረ በኋላ ጒዞውን ወደ ኢየሩሳሌም በመቀጠል፥ ከደቀ መዛሙርቱ ፊት ፊት ይሄድ ነበር። የኢየሱስ በታላቅ ክብር ወደ ኢየሩሳሌም መግባት ( ማቴ. 21፥1-11 ፤ ማር. 11፥1-11 ፤ ዮሐ. 12፥12-19 ) 29 ኢየሱስ በደብረ ዘይት ተራራ አጠገብ ወደሚገኙት ወደ ቤተ ፋጌና ወደ ቢታንያ በቀረበ ጊዜ፥ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለቱን እንዲህ ሲል ላካቸው፤ 30 “በፊታችሁ ወደምትገኘው መንደር ሂዱ፤ እዚያም በደረሳችሁ ጊዜ ገና ማንም ሰው ያልተቀመጠበትን የአህያ ውርንጫ ታስሮ ታገኛላችሁ፤ ፈትታችሁ ወዲህ አምጡት። 31 ማንም ሰው ‘ለምን ትፈቱታላችሁ?’ ብሎ ቢጠይቃችሁ፥ ‘ጌታ ስለሚያስፈልገው ነው’ ብላችሁ መልሱለት።” 32 የተላኩትም ሄደው ሁሉም ነገር ልክ ኢየሱስ እንዳላቸው ሆኖ አገኙት። 33 ውርንጫውን በሚፈቱበት ጊዜ ባለቤቶቹ፦ “ስለምን ትፈቱታላችሁ?” አሉአቸው። 34 እነርሱም “ለጌታ ስለሚያስፈልገው ነው” አሉ። 35 ውርንጫውንም ወደ ኢየሱስ አመጡ፤ ልብሳቸውንም በውርንጫው ጀርባ ላይ አንጥፈው ኢየሱስ እንዲቀመጥበት አደረጉ። 36 ኢየሱስ ሲሄድ ሳለ ሰዎች ልብሳቸውን በመንገዱ ላይ ያነጥፉለት ነበር። 37 ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ከተማ ሊደርስ በተቃረበ ጊዜ የደብረ ዘይትን ተራራ ቊልቊል በመውረድ ላይ ነበር፤ በዚያን ጊዜ ኢየሱስን ይከተሉት የነበሩት ሰዎች ሁሉ ስላዩአቸው ተአምራት በደስታ ተሞልተው ስለ ነበር ድምፃቸውን ከፍ አድርገው እግዚአብሔርን ማመስገን ጀመሩ። 38 እንዲህ ይሉም ነበር፤ “በጌታ ስም የሚመጣ ንጉሥ የተባረከ ነው! ሰላም በሰማይ፥ ክብርም ለእግዚአብሔር በአርያም ይሁን!” 39 በሕዝቡ መካከል የነበሩት አንዳንድ ፈሪሳውያን ግን ኢየሱስን “መምህር ሆይ! ደቀ መዛሙርትህን ዝም አሰኛቸው!” አሉት። 40 ኢየሱስም “እነርሱ እንኳ ዝም ቢሉ ድንጋዮች ይጮኻሉ እላችኋለሁ” ሲል መለሰላቸው። ኢየሱስ ለኢየሩሳሌም ከተማ ማልቀሱ 41 ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ከተማ ቀርቦ፥ ከተማይቱን በተመለከተ ጊዜ፥ አለቀሰላት። 42 እንዲህም አለ፤ “አንቺ ለሰላምሽ የሚያስፈልገውን ነገር ምነው ዛሬ ዐውቀሽ ቢሆን ኖሮ! አሁን ግን ይህ ነገር ከዐይንሽ ተሰውሮብሻል፤ 43 ጠላቶችሽ በዙሪያሽ ዐጥር ዐጥረውና ከበው፥ በዚህም በዚያም አንቺን የሚያስጨንቁበት ቀን ይመጣል። 44 አንቺንና በውስጥሽ ያሉትንም ልጆችሽን በመሬት ላይ ጥለው ያወድማሉ፤ ሳይፈርስ የሚቀር አንድ ድንጋይ እንኳ በቦታው አይተዉልሽም፤ ይህም የሚሆነው፥ እግዚአብሔር አንቺን ሊያድን የመጣበትን ጊዜ ባለማወቅሽ ነው።” ኢየሱስ በቤተ መቅደስ የሚገበያዩትን ማስወጣቱ ( ማቴ. 21፥12-17 ፤ ማር. 11፥15-19 ፤ ዮሐ. 2፥13-22 ) 45 ኢየሱስ ወደ ቤተ መቅደስ ገብቶ፥ በዚያ የሚገበያዩትን ሰዎች ማባረር ጀመረ፤ 46 እንዲህም አላቸው፦ “ ‘ቤቴ የጸሎት ቤት ይሆናል’ ተብሎ ተጽፎአል፤ እናንተ ግን የቀማኞች ዋሻ አደረጋችሁት።” 47 ኢየሱስ በየቀኑ በቤተ መቅደስ ያስተምር ነበር፤ የካህናት አለቆችና የሕግ መምህራን፥ ሌሎችም የሕዝብ መሪዎች ሊገድሉት ይፈልጉ ነበር። 48 ነገር ግን ሰዎች ሁሉ ኢየሱስን ለመስማት በመፈለግ ልባቸው ተማርኮ ስለ ነበረ ሊገድሉት የፈለጉት ወገኖች ምንም ማድረግ አልቻሉም። |