Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ሉቃስ 13 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ንስሓ የማይገባ ሁሉ እንደሚጠፋ

1 በዚያን ጊዜ ሰዎች ወደ ኢየሱስ መጥተው፥ “የገሊላ ሰዎች መሥዋዕት በሚያቀርቡበት ጊዜ ጲላጦስ ገደላቸው፤ ደማቸውም ከመሥዋዕታቸው ጋር አደባለቀ” ሲሉ ነገሩት።

2 ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰላቸው፦ “ታዲያ፥ እነዚህ የገሊላ ሰዎች ይህ ጥፋት የደረሰባቸው ከሌሎቹ የገሊላ ሰዎች ሁሉ ይበልጥ ኃጢአተኞች ስለ ነበሩ ይመስላችኋልን?

3 ‘አይደለም፤ ንስሓ ባትገቡ እናንተም እንደእነርሱ ትጠፋላችሁ’ እላችኋለሁ።

4 በሰሊሆም ግንብ ተደርምሶባቸው ስለሞቱት ዐሥራ ስምንት ሰዎች ምን ታስባላችሁ? እነርሱ በኢየሩሳሌም ከሚኖሩት ሰዎች ሁሉ የባሱ ኃጢአተኞች የነበሩ ይመስሉአችኋልን?

5 አይደለም! ንስሓ ባትገቡ እናንተም እንደእነርሱ ትጠፋላችሁ እላችኋለሁ።”


የማታፈራ የበለስ ዛፍ ምሳሌ

6 ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ይህን ምሳሌ ነገራቸው፦ “አንድ ሰው በወይን ተክሉ ቦታ ውስጥ የተተከለች አንዲት የበለስ ዛፍ ነበረችው፤ ከዚያች የበለስ ዛፍ ፍሬ አገኛለሁ ብሎ ቢሄድ ምንም ሳያገኝ ቀረ።

7 ስለዚህ አትክልተኛውን ‘እነሆ፥ ከዚህች የበለስ ዛፍ ፍሬ ለማግኘት ሦስት ዓመት ሙሉ ተመላለስኩ፤ ግን ምንም ፍሬ አላገኘሁባትም፤ አሁንስ ቊረጣት! ስለምንስ መሬቱን ታበላሻለች?’ አለው።

8 አትክልተኛው ግን እንዲህ ሲል መለሰለት፤ ‘ጌታዬ ሆይ! እስቲ ለዚህ ዓመት ደግሞ ተዋት፤ ዙሪያዋን ኰትኲቼ ማዳበሪያ አደርግላታለሁ፤

9 ለመጪው ዓመት ፍሬ ብትሰጥ መልካም ነው፤ አለበለዚያ ግን ትቈረጣለች።’ ”


ኢየሱስ አንዲት ጀርባዋ የጐበጠ ሴት በሰንበት ቀን መፈወሱ

10 ኢየሱስ በሰንበት ቀን ከምኲራቦቹ በአንዱ ያስተምር ነበር፤

11 ከዚያም ከዐሥራ ስምንት ዓመት ጀምሮ ርኩስ መንፈስ ጀርባዋን ያጐበጣት አንዲት ሴት ነበረች፤ እርስዋ ወገብዋ በመጒበጡ ቀና ለማለት በፍጹም አትችልም ነበር።

12 ኢየሱስ ባያት ጊዜ ጠራትና “አንቺ ሴት ከበሽታሽ ተፈውሰሻል!” አላት።

13 እጆቹን ጫነባት፤ ወዲያውም ቀጥ ብላ ቆመች፤ እግዚአብሔርንም አመሰገነች።

14 ኢየሱስ በሰንበት ቀን ስለ ፈወሰ የምኲራቡ አለቃ ተቈጣና ለሕዝቡ፦ “በሳምንት ውስጥ ሥራ የሚሠራባቸው ስድስት ቀኖች አሉ፤ በእነዚህ ቀኖች እየመጣችሁ ተፈወሱ፤ በሰንበት ቀን ግን አይሆንም” ብሎ ተናገረ።

15 ጌታ ኢየሱስም እንዲህ ሲል መለሰለት፦ “እናንተ ግብዞች፥ ከእናንተስ እያንዳንዱ በሰንበት ቀን በሬውን ከተዘጋበት አውጥቶ፥ ወይም አህያውን ከታሰረበት ፈቶ ውሃ ወደሚያጠጣበት ቦታ ይወስደው የለምን?

16 እነሆ፥ የአብርሃም ዘር የሆነች ይህች ሴት ዐሥራ ስምንት ዓመት ሙሉ በሰይጣን ታስራ ስትሠቃይ ኖራለች፤ ታዲያ፥ እርስዋ ታስራ ከምትሠቃይበት በሽታ በሰንበት ቀን መፈታት አይገባትምን?”

17 በዚህም ንግግሩ ኢየሱስ ተቃዋሚዎቹን ሁሉ አሳፈራቸው፤ ሕዝቡ ግን ኢየሱስ ባደረገው ድንቅ ነገር ሁሉ ተደሰተ።


የሰናፍጭ ዘር ምሳሌ
( ማቴ. 13፥31-32 ፤ ማር. 4፥30-32 )

18 ኢየሱስ እንዲህ አለ፤ “የእግዚአብሔር መንግሥት በምን ትመሰላለች? ወይስ ከምን ጋር አነጻጽራታለሁ?

19 አንድ ሰው በአትክልቱ ውስጥ የዘራትን የሰናፍጭ ዘር ትመስላለች፤ እርስዋ አድጋ ዛፍ ሆነች፤ ወፎችም በቅርንጫፎችዋ ላይ ጎጆአቸውን ሠሩ።”


የእርሾው ምሳሌ
( ማቴ. 13፥33 )

20 ኢየሱስ እንደገና እንዲህ አለ፤ “የእግዚአብሔርን መንግሥት ከምን ጋር አነጻጽራታለሁ?

21 የእግዚአብሔር መንግሥት፥ አንዲት ሴት ሊጡ በሙሉ እንዲቦካ በሦስት መስፈሪያ ዱቄት ውስጥ የለወሰችውን እርሾ ትመስላለች።”


ስለ ጠባብዋ በር
( ማቴ. 7፥13-14 ፤ 21-23 )

22 ከዚህ በኋላ ኢየሱስ ወደ ኢየሩሳሌም ሲሄድ ሳለ በየከተማውና በየገጠሩ እያስተማረ ያልፍ ነበር።

23 በዚያን ጊዜ አንድ ሰው፥ “ጌታ ሆይ፥ የሚድኑ ጥቂቶች ሰዎች ናቸውን?” ሲል ጠየቀው፤ ኢየሱስ እንዲህ ሲል መለሰላቸው፤

24 “በጠባብዋ በር ለመግባት ተጣጣሩ፤ በዚህች በር መግባት የሚፈልጉ ብዙዎች ናቸው፤ ነገር ግን መግባት አይችሉም እላችኋለሁ።

25 የቤቱ ጌታ ተነሥቶ በሩን ይዘጋዋል፤ እናንተም በደጅ ቆማችሁ በሩን በማንኳኳት፥ ‘ጌታ ሆይ! እባክህ ክፈትልን!’ ማለት ትጀምራላችሁ፤ እርሱም ‘ከየት እንደ መጣችሁ አላውቅም!’ ሲል ይመልስላችኋል።

26 በዚያን ጊዜ እናንተ፥ ‘ከአንተ ጋር አብረን በልተናል፤ አብረን ጠጥተናል፤ በአደባባያችንም አስተምረሃል’ ትሉታላችሁ።

27 እርሱም እንደገና ‘ከየት እንደ መጣችሁ አላውቅም፤ እናንተ ክፉ አድራጊዎች ሁሉ ከእኔ ራቁ!’ ይላችኋል።

28 አብርሃምን፥ ይስሐቅን፥ ያዕቆብን ነቢያትንም ሁሉ በእግዚአብሔር መንግሥት ታዩአቸዋላችሁ፤ እናንተ ግን በውጪ ተጥላችሁ ስትቀሩ ለቅሶና ጥርስ ማፋጨት ይደርስባችኋል።

29 ብዙ ሰዎች ከምሥራቅና ከምዕራብ፥ ከሰሜንና ከደቡብ ይመጣሉ፤ በእግዚአብሔር መንግሥትም በማእድ ይቀመጣሉ።

30 ስለዚህ ኋለኞች ፊተኞች ይሆናሉ፤ ፊተኞችም ኋለኞች ይሆናሉ።”


ኢየሱስ ለኢየሩሳሌም ማልቀሱ
( ማቴ. 23፥37-39 )

31 በዚያን ጊዜ አንዳንድ ፈሪሳውያን ወደ ኢየሱስ ቀርበው፥ “ሄሮድስ ሊገድልህ ይፈልጋልና ከዚህ ወጥተህ ሂድ” አሉት።

32 ኢየሱስ ግን እንዲህ አላቸው፦ “ሄዳችሁ ለዚያ ቀበሮ፦ ‘ዛሬና ነገ አጋንንትን አስወጣለሁ፤ በሽተኞችን እፈውሳለሁ፤ በሦስተኛው ቀንም ሥራዬን እጨርሳለሁ’ ይላል በሉት።

33 ይሁን እንጂ ዛሬና ነገ ከነገ ወዲያም መንገዴን ወደ ኢየሩሳሌም መቀጠል አለብኝ፤ ነቢይ ከኢየሩሳሌም በቀር በሌላ ቦታ መሞት አይገባውም።

34 “ኢየሩሳሌም! ኢየሩሳሌም ሆይ! አንቺ ነቢያትን የምትገድዪ፥ ወደ አንቺ የተላኩትንም መልእክተኞች በድንጋይ የምትወግሪ፥ ዶሮ ጫጩቶችዋን በክንፎችዋ ሥር እንደምትሰበስብ፥ እኔም ስንት ጊዜ ልጆችሽን መሰብሰብ ፈለግኹ! አንቺና ሕዝብሽ ግን እምቢ አላችሁ።

35 ስለዚህ ቤታችሁ ወና ሆኖ ይቀራል፤ በእውነት እላችኋለሁ፤ ‘በጌታ ስም የሚመጣ የተባረከ ነው’ እስክትሉ ድረስ ከቶ አታዩኝም።”

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos