Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ዘሌዋውያን 9 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


አሮን ለእግዚአብሔር ያቀረበው መሥዋዕት

1 ሰባት ቀን የቈየው የክህነት አሰጣጥ ሹመት በተፈጸመ ማግስት ሙሴ አሮንንና ልጆቹን፥ እንዲሁም የእስራኤልን መሪዎች ጠራ፤

2 አሮንንም እንዲህ አለው፤ “ምንም ነውር የሌለባቸውን አንድ ወይፈንና አንድ የበግ አውራ ወስደህ ወይፈኑን ስለ ኃጢአት ስርየት የሚቀርብ መሥዋዕት፥ የበግ አውራውንም የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገህ ለእግዚአብሔር አቅርብ።

3 ከዚህ በኋላ የእስራኤል ሕዝብ ስለ ኃጢአት ስርየት መሥዋዕት የሚሆን አንድ ተባዕት ፍየል፥ ምንም ነውር የሌለባቸውን የአንድ ዓመት ጥጃና የአንድ ዓመት የበግ ጠቦት ለሚቃጠል መሥዋዕት እንዲያመጡ ንገራቸው።

4 እንዲሁም አንድ ወይፈንና አንድ የበግ ጠቦት ለአንድነት መሥዋዕት ያምጡ፤ እነዚህንም በዘይት ከታሸ የእህል መባ ጋር ለእግዚአብሔር መሥዋዕት አድርገው ያቅርቡ፤ ዛሬ እግዚአብሔር ስለሚገለጥላቸው ይህን ሁሉ ያድርጉ።”

5 እነርሱም ሙሴ ያዘዛቸውን ሁሉ ወደ ድንኳኑ ፊት ለፊት አመጡ፤ ማኅበሩም ሁሉ ለእግዚአብሔር ለመስገድ ወደዚያ ተጠግተው ቆሙ።

6 ሙሴም “የእግዚአብሔር ክብር ስለሚገለጥላችሁ ይህን ሁሉ እንድታደርጉ እግዚአብሔር አዞአል።” አላቸው።

7 ከዚህም በኋላ ሙሴ አሮንን እንዲህ አለው፤ “ወደ መሠዊያው ቀርበህ የራስህን ኃጢአትና የሕዝቡን ኃጢአት ለማስተስረይ ስለ ኃጢአት ስርየት የሚቀርበውን መሥዋዕትና የሚቃጠለውን መሥዋዕት አቅርብ፤ ይህንንም ሁሉ መሥዋዕት የሕዝቡን ኃጢአት ለማስተስረይ እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት አቅርብ።”

8 አሮንም ወደ መሠዊያው ሄዶ መጀመሪያ ስለ ራሱ ኃጢአት ስርየት መሥዋዕት ሆኖ የሚቀርበውን ጥጃ ዐረደ፤

9 ልጆቹም ደሙን ወደ እርሱ አመጡለት፤ እርሱም ደሙን በጣቱ እያጠቀሰ በመሠዊያው ላይ ያሉትን ጒጦች ቀባ፤ የተረፈውንም ደም በመሠዊያው ሥር አፈሰሰ፤

10 ከዚህም በኋላ ስቡን፥ ኲላሊቶቹን እንደ መረብ ሆኖ ጒበቱን ከሚሸፍነው ስብ ምርጥ የሆነውን ወስዶ እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት በመሠዊያው ላይ አቃጠለው፤

11 ሥጋውንና ቆዳውን ግን ከሰፈር ውጪ አውጥቶ አቃጠለው።

12 የሚቃጠል መሥዋዕት ሆኖ የሚቀርበውንም እንስሳ ዐረደ፤ ልጆቹም ደሙን ወደ እርሱ አመጡለት፤ እርሱም ደሙን በመሠዊያው ጐን በአራቱም ማእዘን ረጨ፤

13 ጭንቅላቱንና ሌላውንም ሥጋ በየብልቱ ከፋፍለው አመጡለት፤ አሮንም ያን ሁሉ በመሠዊያው ላይ አቃጠለው።

14 ከዚህ በኋላ ሆድ ዕቃውንና የኋላ እግሮቹን በውሃ አጥቦ በመሠዊያው ላይ ባለው የሚቃጠል መሥዋዕት መሠዊያ ላይ በማኖር አቃጠለው።

15 ከዚያም በኋላ ካህኑ የሕዝቡን መባ አቀረበ፤ ስለ ሕዝቡ ኃጢአት ስርየት መሥዋዕት ሆኖ የሚቀርበውን ተባዕት ፍየል ወስዶ ዐረደው፤ እርሱንም ስለ ራሱ ኃጢአት ባቀረበው ዐይነት መሥዋዕት አድርጎ አቀረበው።

16 ለሚቃጠል መሥዋዕት የሚቀርበውንም እንስሳ አምጥቶ በሥርዓቱ መመሪያ ሕግ መሠረት ሠዋው።

17 የእህሉንም መባ አቀረበ፤ ከዱቄቱም በእፍኙ ሙሉ ወስዶ በመሠዊያው ላይ አቃጠለው፤ ይህም ለሚቃጠል መሥዋዕት ጧት ከሚቀርበው ጋር ተጨማሪ መሆኑ ነው።

18 በሬውንና የበግ አውራውን ዐርዶ ስለ ሕዝቡ የአንድነት መሥዋዕት በማድረግ አቀረበ፤ ልጆቹም ደሙን አመጡለት፤ እርሱም ተቀብሎ ደሙን በመሠዊያው ጐን በአራቱም ማእዘን ረጨው፤

19 አሮንም የወይፈኑንና የበግ አውራውን ስብ ሁሉ ማለትም ላቱን፥ ሆድ ዕቃውን የሚሸፍነውን ስብ፥ እንደ መረብ ሆኖ ጒበቱን የሚሸፍነውን ስብ ምርጥ የሆነውን ክፍል፥ ኲላሊቶቹንና በእነርሱ ላይ ያለውን ስብ ወስዶ፥

20 በእንስሶቹ ፍርምባ ጫፍ ላይ በመደረብ ያን ሁሉ ወስደው በመሠዊያው ላይ አኖሩት፤ አሮንም ስቡን በመሠዊያው ላይ አቃጠለው፤

21 ፍርምባዎቹንና በስተቀኝ በኩል ያሉትን የኋላ እግሮች ሙሴ ባዘዘው መሠረት በመወዝወዝ ለእግዚአብሔር ልዩ መባ አድርጎ አቀረበው።

22 አሮንም ይህን ሁሉ መሥዋዕት አቅርቦ እንደ ጨረሰ እጆቹን በሕዝቡ ላይ ዘርግቶ ከባረካቸው በኋላ ወረደ፤

23 ሙሴና አሮን ወደ መገናኛው ድንኳን ገቡ፤ በሚወጡበትም ጊዜ ሕዝቡን ባረኩ፤ የእግዚአብሔርም ክብር ለሕዝቡ ሁሉ ተገለጠ፤

24 እሳትም በድንገት ከእግዚአብሔር ዘንድ ተልኮ፥ በመሠዊያው ላይ የነበረውን መሥዋዕትና ስብ ሁሉ በላ፤ ሕዝቡ ሁሉ ይህን ባዩ ጊዜ እልል አሉ፤ በምድር ላይም በግንባራቸው ተደፍተው ሰገዱ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos