Biblia Todo Logo
La Biblia Online

- Anuncios -


ዘሌዋውያን 18 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


የተከለከለ ፍትወታዊ ግንኙነት

1 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው፤

2 “ለእስራኤል ልጆች እንዲህ በላቸው፦ ‘እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ፤

3 በኖራችሁባት በግብጽ ምድር፥ ወይም አሁን እኔ በማስገባችሁ በከነዓን ምድር የሚኖሩ አሕዛብ የሚያደርጉትን አታድርጉ፤ ሥርዓታቸውንም አትከተሉ።

4 ኅጎቼን ፈጽሙ፤ ሥርዓቴን ጠብቁ። እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።

5 እኔ የምሰጣችሁን ኅጎቼንና ሥርዓቴን ጠብቁ፤ ይህን በማድረግ ማናቸውም ሰው ሕይወቱን ያድናል፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።’ ”

6 “ማንም ሰው ፍትወታዊ ግንኙነት ለማድረግ ወደ ሥጋ ዘመዱ አይቅረብ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤

7 ከእናትህ ጋር ፍትወታዊ ግንኙነት በማድረግ የአባትህን ክብር አታዋርድ፤ እናትህ ስለ ሆነች የእርስዋን ኀፍረተ ሥጋ አትግለጥ።

8 ከሌሎቹ ሚስቶቹም ፍትወታዊ ግንኙነት በማድረግ አባትህን አታዋርድ።

9 ከእኅትህ ጋር የፍትወተ ሥጋ ግንኙነት አታድርግ፤ የአባትህ ልጅ ወይም የናትህ ልጅ፥ በቤት ወይም በውጪ የተወለደች ብትሆን ኀፍረተ ሥጋዋን አትግለጥ።

10 ኀፍረተ እንዳይሆንብህ ከልጅ ልጅህ ጋር ፍትወታዊ ግንኙነት አታድርግ።

11 እኅትህ ስለ ሆነች ከአባትህና ከእንጀራ እናትህ ልጅ ጋር ፍትወታዊ ግንኙነት አታድርግ።

12 አክስትህ ስለ ሆነች ከአባትህ እኅት ጋር ፍትወታዊ ግንኙነት አታድርግ።

13 አክስትህ ስለ ሆነች ከእናትህ እኅት ጋር ፍትወታዊ ግንኙነት አታድርግ።

14 እንደ አክስትህ ስለ ሆነች ከአጐትህ ሚስት ጋር ፍትወታዊ ግንኙነት አታድርግ።

15 የልጅህ ሚስት ስለ ሆነች ከምራትህ ጋር ፍትወታዊ ግንኙነት አታድርግ።

16 ዋርሳ ስለ ሆነች ከወንድምህ ሚስት ጋር ፍትወታዊ ግንኙነት አታድርግ።

17 ከእናትና ከሴት ልጅዋ፥ እንዲሁም ከልጅ ልጆችዋ ጋር ፍትወታዊ ግንኙነት አታድርግ፤ እነርሱም የቅርብ ዘመዶችህ ስለ ሆኑ ኃጢአት ይሆንብሃል።

18 ሚስትህ በሕይወት እያለች እኅትዋ ጣውንትዋ እንዳትሆን እኅትዋን አታግባ፤ ከእርስዋም ጋር ፍትወታዊ ግንኙነት አታድርግ።

19 “በወር አበባዋ ምክንያት ካልነጻች ሴት ጋር ፍትወታዊ ግንኙነት አታድርግ።

20 ከሌላ ሰው ሚስት ጋር በመተኛት ራስህን ከእርስዋ ጋር አታርክስ።

21 የእግዚአብሔር አምላክህን ስም እንዳታሰድብ ከልጆችህ ማንኛውንም ሞሌክ ለተባለው ባዕድ አምላክ የሚቃጠል መሥዋዕት ይሆን ዘንድ አሳልፈህ አትስጥ፤ እኔ እግዚአብሔር ነኝ።

22 በእግዚአብሔር ዘንድ የተጠላ ነገር ስለ ሆነ፥ ግብረ ሰዶም አትፈጽም።

23 ወንድ ወይም ሴት ማንም ሰው ከእንስሳ ጋር ተኝቶ ራሱን አያርክስ፤ እንዲህ ያለው ድርጊት የተፈጥሮን ሕግና ሥርዓት የሚያበላሽ ነው።

24 “ወደ ምድራቸው ያስገባህ ዘንድ እግዚአብሔር ከፊትህ የሚያስወግዳቸው ሕዝቦች ራሳቸውን ያረከሱባቸው ስለ ሆኑ፥ ከእነዚህ ድርጊቶች በአንዱ እንኳ ራስህን አታርክስ።

25 ምድሪቱ ረከሰች፤ በበደልዋ ምክንያት ቀጣኋት፤ እርስዋም የሚኖሩባትን ሰዎች አንቅራ ተፋቻቸው።

26 ትእዛዞቼንና ኅጎቼን ጠብቁ፤ ከእነዚህ ርኲሰቶች እናንተም ሆናችሁ በመካከላችሁ የሚኖሩ ባዕዳን አንዳቸውንም አታድርጉ።

27 ከእናንተ በፊት የነበሩት የምድሪቱ ኗሪዎች እነዚህን ርኲሰቶች ሁሉ ስለ ፈጸሙ ምድሪቱን አርክሰዋታል።

28 ምድሪቱን ብታረክስዋት ከእናንተ በፊት የነበሩትን ሕዝቦች እንደ ተፋች እናንተንም አንቅራ ትተፋችኋለች።

29 እነዚህን ርኲሰቶች የሚፈጽም ያ ሰው ከሕዝቡ ይለይ።

30 “እኔ የምሰጣችሁን ትእዛዝ ሁሉ ፈጽሙ፤ ከእናንተ በፊት በምድሪቱ ይፈጽሙት የነበረውን የረከሰ ልማድ አትከተሉ፤ ከእነዚህ አሳፋሪ ተግባሮች አንዱንም በመፈጸም ራሳችሁን አታርክሱ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ።”

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos