Biblia Todo Logo
La Biblia Online

- Anuncios -


ዘሌዋውያን 16 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


የኃጢአት ስርየት ቀን

1 ሁለቱ የአሮን ልጆች ያልተፈቀደ እሳት ይዘው ወደ እግዚአብሔር ፊት በመቅረባቸው ከሞቱ በኋላ እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ ሲል ተናገረው፦

2 “እኔ በታቦቱ ስርየት መክደኛ በደመና የምገለጥበት ስለ ሆነ፥ መጋረጃውን አልፎ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን መግባት ያለበት ሁልጊዜ ሳይሆን፥ በአንድ በተወሰነ ቀን ብቻ መሆኑን፥ ለወንድምህ ለአሮን ንገረው፤ ይህን ትእዛዝ የማይፈጽም ከሆነ ይሞታል፤

3 ወደ ቅድስተ ቅዱሳን መግባት የሚችለውም ስለ ኃጢአት ስርየት መሥዋዕት አንድ ወይፈን፥ ለሚቃጠል መሥዋዕትም አንድ አውራ በግ ካቀረበ በኋላ መሆን አለበት።”

4 “አሮን ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ከመግባቱ በፊት ሰውነቱን ታጥቦ የክህነት ልብሱን ይልበስ፤ ይኸውም ከበፍታ የተሠራውን ቀሚስና ሱሪ ይልበስ፤ እንዲሁም ከበፍታ የተሠራውን ቀበቶ ይታጠቅ፤ ከበፍታ የተሠራውንም መጠምጠሚያ ራሱ ላይ ያድርግ።

5 “የእስራኤልም ማኅበር ስለ ኃጢአት ማስተስረያ መሥዋዕት ሁለት ተባዕት ፍየሎች፥ ለሚቃጠልም መሥዋዕት አንድ አውራ በግ ለአሮን ያምጡለት።

6 የራሱንና የቤተሰቡንም ኃጢአት ለማስተስረይ አንድ ኰርማ መሥዋዕት አድርጎ ያቅርብ።

7 ከዚህም በኋላ ሁለቱን ፍየሎች ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ በእግዚአብሔር ፊት ይውሰድ፤

8 በዚያም አንዱ ‘ለእግዚአብሔር’ ሁለተኛው ‘ለዐዛዜል’ የሚል ምልክት ያለባቸው ሁለት ድንጋዮች ወስዶ ዕጣ ያውጣ፤

9 አሮንም በዕጣ ለእግዚአብሔር የተመረጠውን ፍየል ስለ ኃጢአት ማስተስረያ መሥዋዕት አድርጎ ያቀርባል።

10 ለዐዛዜል የተመረጠውም ፍየል የሕዝቡን ኃጢአት ተሸክሞ ወደ በረሓ እንዲላክ ከነሕይወቱ ወደ እግዚአብሔር ፊት ይቀርባል።”

11 አሮንም ኰርማውን ስለ ራሱና ስለ ቤተሰቡ የኃጢአት ማስተስረያ መሥዋዕት በማድረግ ይረደው፤

12 ከመሠዊያው የሚቃጠል የእሳት ፍም በጥናው ሞልቶም ሁለት እፍኝ ጣፋጭ ሽታ ያለውን የተወቀጠ ደቃቅ ዕጣን በመውሰድ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ያግባ፤

13 እዚያም በእግዚአብሔር ፊት በእሳቱ ላይ ዕጣን ይጨምርበት፤ እርሱም አይቶ እንዳይሞት የዕጣኑ ጢስ የስርየት መክደኛውን ይሸፍነው።

14 ከኰርማውም ደም ጥቂት ወስዶ በጣቱ እየነከረ በስርየት መክደኛው ላይ ከፊት ለፊት በኩል ይርጭ፤ እንዲሁም ከእርሱ ጥቂቱን በኪዳኑ ታቦት ፊት ሰባት ጊዜ ይርጨው።

15 ከዚህም በኋላ ለሕዝቡ የኃጢአት ማስተስረያ የሆነውን ፍየል ይረድ፤ ደሙንም ወደ ቅድስተ ቅዱሳን አስገብቶ በኰርማው ደም ባደረገው ዐይነት፥ በስርየት መክደኛው ላይ፥ እንዲሁም በኪዳኑ ታቦት ፊት ይርጨው።

16 በዚህም ዐይነት ቅድስተ ቅዱሳኑን ከእስራኤል ሕዝብ ርኲሰትና ከኃጢአታቸውም ሁሉ ለማጥራት የማንጻትን ሥርዓት ይፈጽማል፤ ንጹሕ ባልሆነ ሰፈር መካከል ስለሚገኝ ድንኳኑንም ለማንጻት እንዲሁ ያደርጋል።

17 አሮን ለማስተሰረይ ወደ መቅደሱ በሚገባበት ጊዜ ለራሱ፥ ለቤተሰቡ፥ ለእስራኤል ጉባኤ ሁሉ አስተስርዮ እስኪወጣ ድረስ ድንኳን ውስጥ ማንም አይኑር፤

18 ከዚያም በእግዚአብሔር ፊት ወዳለው መሠዊያ ወጥቶ መሠዊያውን ያንጻው፤ ከኰርማውና ከፍየሉ ጥቂት ደም ወስዶ በመሠዊያው ዙሪያ ያሉትን ጒጦች ይቀባ፤

19 ከደሙም ጥቂቱን ወስዶ በጣቱ እየነከረ በመሠዊያው ላይ ሰባት ጊዜ ይርጭ፤ በዚህም ዐይነት ከእስራኤል ሕዝብ ርኲሰትን በማንጻት መሠዊያውን የተቀደሰ ያደርገዋል።


የሕዝብን በደል ተሸክሞ ወደ በረሓ የሚለቀቅ ፍየል

20 አሮን ቅድስተ ቅዱሳኑን፥ የመገናኛውን ድንኳን የቀረውን ክፍልና መሠዊያውንም የማንጻት ሥርዓት ከፈጸመ በኋላ ለዐዛዜል የተመረጠውን ፍየል ወስዶ ለእግዚአብሔር ያቀርባል።

21 ሁለት እጆቹን በፍየሉ ራስ ላይ ይጭናል፤ የሕዝቡን ክፋት፥ ኃጢአትና ዐመፅ ሁሉ በመናዘዝ አዛውሮ በፍየሉ ራስ ላይ ያሸክመዋል፤ ከዚህ በኋላ ለዚህ ሥራ የተመደበ ሰው ፍየሉን ነድቶ ወደ በረሓ ይወስደዋል።

22 ፍየሉንም ኃጢአታቸውን ሁሉ ተሸክሞ ምንም ሰው ወደማይኖርበት ምድረ በዳ ወስዶ ይለቀዋል።

23 “አሮንም ወደ ድንኳኑ ይግባ፤ ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ከመግባቱ በፊት ለብሶት የነበረውን የክህነት ልብስ አውልቆ፥ በዚያ ይተወው፤

24 በተቀደሰውም ቦታ ሰውነቱን ታጥቦ የዘወትር ልብሱን ይልበስ፤ ከዚያም ወጥቶ የራሱንና የሕዝቡን ኃጢአት ለማስተስረይ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ያቅርብ።

25 ኃጢአትን ለማስተስረይ መሥዋዕት ሆኖ የቀረበውንም የእንስሳ ስብ፥ በመሠዊያው ላይ ያቃጥለው፤

26 የተመረጠውን ፍየል እየነዳ ወደ በረሓ ይዞት ሄዶ የነበረውም ሰው ወደ ሰፈር ከመግባቱ በፊት ልብሱን ይጠብ፤ ሰውነቱንም ይታጠብ።

27 ስለ ኃጢአት ስርየት መሥዋዕት ሆነው የቀረቡትና ኃጢአትን ለማስተስረይ ደማቸው ወደ ቅድስተ ቅዱሳን ገብቶ የነበረው ኰርማና ፍየልም ከሰፈር ወደ ውጪ ተወስደው በእሳት ይቃጠሉ፤ እንዲሁም ቆዳቸው፥ ሥጋቸውና የሆድ ዕቃቸው በሙሉ ይቃጠል።

28 እነርሱንም የሚያቃጥለው ሰው ወደ ሰፈር ከመመለሱ በፊት ልብሱን ይጠብ፤ ሰውነቱንም ይታጠብ።


የኃጢአት ማስተስረያን ቀን ስለ መጠበቅ

29 “ከዚህ የሚከተሉትን መመሪያዎች በሚመጡት ዘመናት ሁሉ ቋሚ ሥርዓት አድርጋችሁ ትጠብቁአቸዋላችሁ፦ ሰባተኛው ወር በገባ በዐሥረኛው ቀን እስራኤላውያንና በእነርሱ መካከል የሚኖሩ መጻተኞች ራሳቸውን ማዋረድ አለባቸው፤ በዚያን ቀን ምንም ሥራ አይሥሩበት።

30 በዚያን ዕለት ንጹሖች እንድትሆኑ የኃጢአት ማስተስረይ ይደረግላችኋል፤ ከዚያም ከኃጢአታችሁ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት የነጻችሁ ትሆናላችሁ፤

31 ያም ዕለት እንደ ሰንበት የዕረፍት ቀን ይሁንላችሁ፤ በዚያን ቀን ራሳችሁን አዋርዱ ይህም የዘለዓለም ሥርዓት ነው።

32 በአባቱ ምትክ ሊቀ ካህናት እንዲሆን ተለይቶ የሚሾመው ካህን የተቀደሰ የክህነት በፍታ ልብሱን ለብሶ ያስተሰርያል።

33 እርሱም ለቅድስተ ቅዱሳኑ፥ ለመገናኛው ድንኳን፥ ለመሠዊያው፥ ለካህናቱና ለጉባኤው ያስተሰርያል።

34 በዓመት አንድ ጊዜ የእስራኤላውያንን ኃጢአት ሁሉ ማስተስረይ የዘለዓለም ሥርዓት ይሆናል።” በዚህም ዐይነት ሙሴ እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos