ዘሌዋውያን 12 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምሴቶች ከወለዱ በኋላ የሚጠብቁት የመንጻት ሥርዓት 1 እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ አለው፤ 2 “ሴት ፀንሳ ወንድ ልጅ ብትወልድ፥ በወር አበባዋ እንደሚሆነው ዐይነት እስከ ሰባት ቀን ድረስ የረከሰች ትሆናለች፤ 3 በስምንተኛው ቀን ሕፃኑ መገረዝ አለበት፤ 4 ከዚያም በኋላ በተጨማሪ ደምዋ እስከሚጠራ እስከ ሠላሳ ሦስት ቀን ድረስ የተቀደሰውን ማናቸውንም ነገር መንካት የለባትም፤ ይህ የመንጻትዋም ጊዜ እስከሚፈጸም ድረስ ወደ ተቀደሰው ድንኳን አትግባ። 5 “እንዲሁም አንድ ሴት፥ ሴት ልጅ ብትወልድ፥ በወር አበባዋ ጊዜ በሚደረገው ዐይነት፥ እስከ ዐሥራ አራት ቀን ድረስ የረከሰች ትሆናለች፤ ከዚህም በኋላ ደምዋ እስኪደርቅና የመንጻትዋ ወራት እስኪፈጸም ድረስ ስድሳ ስድስት ቀኖች ትቈይ። 6 “የመንጻትዋም ወራት በተፈጸመ ጊዜ ስለ ወንድ ልጅም ሆነ ስለ ሴት ልጅ የሚቃጠል መሥዋዕት ሆኖ የሚቀርብ የአንድ ዓመት የበግ ጠቦትና ስለ ኃጢአት ስርየት መሥዋዕት የሚሆን ርግብ ወይም ዋኖስ ወደ መገናኛው ድንኳን ደጃፍ አምጥታ በዚያ ለሚያገለግለው ካህን ትስጠው። 7 ካህኑም ስጦታዋን ተቀብሎ ለእግዚአብሔር ያቀርባል፤ የደም መፍሰስ ርኵሰትዋ ተወግዶ የምትነጻበትንም ሥርዓት ይፈጽማል፤ ከዚያም በኋላ የነጻች ትሆናለች፤ ይህም እንግዲህ ወንድ ወይም ሴት ከወለደች በኋላ የምትፈጽመው ሕግ ሆኖ ይኖራል። 8 “ሴትዮዋ የበግ ጠቦት ማምጣት ካልቻለች፥ ሁለት ርግቦች ወይም ሁለት ዋኖሶች ታምጣ፤ እነርሱም አንዱ ለሚቃጠል መሥዋዕት ሌላውም ስለ ኃጢአት ስርየት መሥዋዕት ይቀርባሉ፤ ካህኑም ያስተሰርይላትና ትነጻለች፤ ከዚያም በኋላ የነጻች ትሆናለች።” |