ዘሌዋውያን 11 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየሚበሉ እንስሶች ዐይነት ( ዘዳ. 14፥3-21 ) 1 እግዚአብሔር ለሙሴና ለአሮን እንዲህ አላቸው፤ 2 “ይህን ለእስራኤል ሕዝብ ንገሩ፤ በምድሪቱ ከሚገኙት እንስሶች መብላት የምትችሉት እነዚህን ነው፦ 3 ሰኮናው ስንጥቅ የሆነውንና የሚያመሰኳውን እንስሳ ትበላላችሁ፤ 4 ነገር ግን ከሚያመሰኩት ወይም ሰኮናቸው ስንጥቅ ከሆነው የሚከተሉትን አትበሉም፤ ግመል ያመሰኳል፤ ነገር ግን ሰኰናው ስላልተሰነጠቀ በእናንተ ዘንድ ርኩስ ይሁን። 5 ሽኮኮ ያመሰኳል፤ ነገር ግን ሰኰናው ስላልተሰነጠቀ በእናንተ ዘንድ ርኩስ ይሁን። 6 ጥንቸልም ያመሰኳል፤ ንገር ግን ሰኰናው ስላልተሰነጠቀ በእናንተ ዘንድ ርኩስ ይሁን። 7 ዐሳማዎችንም አትብሉ፤ እነርሱ ሰኰናቸው የተሰነጠቀ ቢሆንም ስለማያመሰኩ በእናንተ ዘንድ እንደ ርኩስ የሚቈጠሩ ይሁኑ። 8 ለእናንተ የረከሱ ስለ ሆኑ እነዚህን እንስሶች አትብሉ፤ በድናቸውንም እንኳ አትንኩ። 9 “በባሕሮችና በወንዞች ውስጥ ካሉት ክንፍና ቅርፊት ያላቸውን ሁሉ ብሉ፤ 10 ነገር ግን በውሃ ውስጥ የሚገኘው ክንፍና ቅርፊት የሌለው ፍጥረት ሁሉ መበላት የለበትም። 11 እንደነዚህ ያሉት እንስሶች በእናንተ ዘንድ የረከሱ ሆነው መቈጠር አለባቸው፤ እነርሱን መብላት ቀርቶ በድናቸውን መንካት እንኳ የለባችሁም። 12 ስለዚህ በውሃ ውስጥ የሚኖሩ ክንፍና ቅርፊት የሌላቸው ፍጥረቶች ሁሉ በእናንተ ዘንድ የተጠሉ ይሁኑ። 13 “ከወፎች ወገን ልትጸየፏቸው የሚገባና የማይበሉ እነዚህ ናቸው፤ ንስር፥ ገዲ፥ ዓሣ አውጪ፥ 14 ጭላት፥ ጭልፊት በየዐይነቱ 15 ቊራ ሁሉ በየወገኑ፥ 16 ሰጐን፥ ጠላቋ፥ ዝይ፥ በቋል፥ በየዐይነቱ፥ 17 ጒጒት፥ እርኩም፥ ጋጋኖ፥ 18 የውሃ ዶሮ፥ ይብራ፥ ጥንብ አንሣ አሞራ፥ 19 ሽመላ፥ ሳቢሳ በየዐይነቱ፥ ጅንጁላቴ ወፍ፥ የሌሊት ወፍ። 20 “ክንፍ ያላቸው በአራት እግር የሚንቀሳቀሱ ፍጥረቶች ሁሉ የረከሱ ናቸው፤ 21 ነገር ግን ከእነርሱ መካከል ከእግሮቻቸው በላይ በምድር ላይ የሚዘሉባቸው ቅልጥሞች ካሉአቸው ተንቀሳቃሾች እነዚህን ትበላላችሁ፤ 22 ይኸውም አንበጣዎችን፥ በዐይነታቸው ፌንጣዎችን በየዐይነታቸው፥ ኲብኲባዎችን በየዐይነታቸው 23 ነገር ግን ሌሎች ክንፎችና አራት እግሮች ያሉአቸው ፍጥረቶች እንደ ርኩስ ይቈጠሩ። 24 “በሚከተሉት እንስሶች ርኩሳን ትሆናላችሁ፤ የእነርሱን በድን የሚነካ እስከ ማታ ርኩስ ይሆናል፤ 25 ከእነርሱም በድን የሚያነሣ ልብሱን ይጠብ፤ እስከ ማታም ርኩስ ይሁን፤ 26 ሰኰና ያለው፥ ነገር ግን ሰኰናው በሙሉ ያልተሰነጠቀና የማያመሰኩ እንስሳ ሁሉ በእናንተ ዘንድ ርኩስ ይሆናል፤ እርሱን የሚነካ ሁሉ ይረክሳል፤ 27 በአራት እግሮቹ ከሚሄድ እንስሳ በመዳፎቹ ላይ የሚሄድ በእናንተ ዘንድ የረከሰ ይሆናል፤ የእርሱንም በድን የሚነካ ሁሉ እስከ ማታ ርኩስ ይሆናል፤ 28 በድናቸውንም የሚያነሣ ልብሱን ይጠብ፤ እስከ ማታም ርኩስ ይሆናል፤ እነርሱም በእናንተ ዘንድ ርኩሳን ናቸው። 29 “በምድር ላይ ከሚንቀሳቀሱ ፍጥረቶች እነዚህ በእናንተ ዘንድ ርኩሳን ናቸው፦ ፍልፈል፥ አይጥ፥ እንሽላሊት፥ 30 ገበሎ፥ አዞ፥ ኤሊ፥ አርጃኖ፥ እስስት፥ 31 ከሚንቀሳቀሱት ሁሉ ርኩሳን የሚሆኑት እነዚህ ናቸው፤ እነርሱንም ሆነ በድናቸውን የሚነካ ሁሉ እስከ ምሽት ድረስ ርኩስ ይሁን። 32 በድናቸው የሚወድቅበት ነገር ሁሉ ይረክሳል፤ ይኸውም ከእንጨት የተሠሩ ዕቃዎችን፥ ልብስን፥ ቆዳን ወይም ከረጢት የመሳሰሉትንና ሌላውንም ነገር ሁሉ ይጨምራል፤ የእነርሱ በድን የነካው ይህን የመሰለ ዕቃ ሁሉ በውሃ ውስጥ ተነክሮ ይቈይ፤ እስከ ምሽትም ድረስ ርኩስ ሆኖ ከዚያ በኋላ ንጹሕ ይሆናል። 33 ከነርሱ የአንዳቸው በድን በሸክላ ዕቃ ውስጥ ቢወድቅ፥ በዕቃው ውስጥ ያለው ነገር ሁሉ ስለሚረክስ፥ ሸክላውን ስበሩት። 34 የሚበላ ምግብ ሁሉ ከሸክላው ዕቃ የውሃ ነጠብጣብ ቢያርፍበት፥ ርኩስ ይሆናል፤ የሚጠጣም ነገር ቢሆን በዚያ ሸክላ ዕቃ ውስጥ ካለ ርኩስ ነው። 35 ማንኛውም በድን የሚወድቅበት ነገር ሁሉ ርኩስ ስለ ሆነ፥ ተጸየፉት፤ ክፍት ምድጃም ሆነ ዝግ ምድጃ ይሰበር። 36 ሌላው ነገር ሁሉ የእነዚህ እንስሶች በድን ሲነካው የሚረክስ ቢሆንም ምንጭ ወይም የውሃ ጒድጓድ አይረክስም። 37 ለዘር በተቀመጠ እህል ላይ ከእነዚህ በድኖች አንዱ ቢያርፍበት ዘሩ ንጹሕ ነው፤ 38 ነገር ግን በዘሩ ላይ ውሃ ከፈሰሰበት በኋላ አንዳች በድን ቢነካው ዘሩ በእናንተ ዘንድ ርኩስ ይሆናል። 39 “ከሚበሉትም ቢሆን ማናቸውም እንስሳ ቢሞት የሚነካው ሁሉ እስከ ምሽት ርኩስ ነው። 40 ማንም ከዚህ እንስሳ ማንኛውንም ክፍል ቢበላ ልብሱን ይጠብ፤ እስከ ምሽት ድረስ ርኩስ ይሁን፤ ማንም ሰው የዚያን እንስሳ በድን ቢሸከም ልብሱን ይጠብ፤ እርሱም እስከ ምሽት ድረስ ርኩስ ይሁን። 41 “በምድር ላይ በደረታቸው እየተሳቡ የሚንቀሳቀሱ ትናንሽ ነፍሳት ሁሉ የማይበሉና በእናንተ ዘንድ የተጠሉ ይሁኑ፤ 42 በደረት የሚሳቡ፥ በአራት እግር የሚሄዱ ወይም ብዙ እግር ያሉአቸው ሁሉ የማይበሉና የተጠሉ ይሁኑ። 43 ከነዚህ ውስጥ ማንኛውንም በመብላት ራሳችሁን አታርክሱ፤ 44 እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ፤ እኔ ቅዱስ ስለ ሆንኩ እናንተም ራሳችሁን የተቀደሰ አድርጉ፤ በደረታቸው እየተሳቡ የሚንቀሳቀሱትን ነፍሳት በመብላት ራሳችሁን አታርክሱ። 45 አምላካችሁ እሆን ዘንድ ከግብጽ ምድር መርቼ ያወጣኋችሁ እኔ እግዚአብሔር ነኝ፤ ስለዚህም እኔ ቅዱስ ስለ ሆንኩ እናንተም ቅዱሳን ሁኑ። 46 “ይህ እንግዲህ በውሃ ውስጥ ስለሚኖሩና በምድር ላይ ስለሚንቀሳቀሱ ስለ እንስሶችና ወፎች ሁሉ የተሰጠ ሕግ ነው፤ 47 ንጹሕ በሆነውና ንጹሕ ባልሆነው መካከል ያለውን ልዩነት ለማወቅ፥ ይኸውም በሚበሉትና በማይበሉት እንስሶች መካከል ያለውን ልዩነት ለመረዳት ብርቱ ጥንቃቄ አድርጉ።” |