ኢያሱ 19 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምለስምዖን ርስት ሆኖ የተመደበ ምድር 1 ሁለተኛው ዕጣ ለስምዖን ነገድ በየወገኖቻቸው ወጣ፤ ርስቱም ለይሁዳ ነገድ እስከ ተመደበው ምድር ድረስ ገባ ያለ ነበር፤ 2 እነርሱም ቤርሳቤህ፥ ሼባዕ፥ ሞላዳ፥ 3 ሐጻርሹዓል፥ ባላ፥ ዔጼም፥ 4 ኤልቶላድ፥ በቱል፥ ሖርማ፥ 5 ጺቅላግ፥ ቤትማርካቦት፥ ሐጻርሱሳ፥ 6 ቤትለባኦትና ሻሩሔን የተባሉትን ዐሥራ ሦስት ከተሞችና በዙሪያቸው ያሉትን ትንንሽ ከተሞችንም ይጨምር ነበር። 7 ከዚህም ሁሉ ጋር በተጨማሪ ዓይን፥ ሪሞን፥ ዔቴርና ዐሻን ተብለው የሚጠሩትን አራት ከተሞች በዙሪያቸው የሚገኙ ታናናሽ ከተሞችን ያጠቃልል ነበር፤ 8 በደቡብ በኩል እስከምትገኘው እስከ ባዕላትበኤር (ራማ) ድረስ በእነዚህ ከተሞች ዙሪያ ያሉትን ትንንሽ ከተሞችን ሁሉ ያጠቃልል ነበር፤ የስምዖን ነገድ ርስት በየወገኖቻቸው ይዞ ነበር፤ 9 የይሁዳ ነገድ ድርሻ በጣም ብዙ ስለ ነበር ለስምዖን ነገድ በይሁዳ ርስት ውስጥ ድርሻ ተሰጠው። ለዛብሎን ርስት ሆኖ የተመደበ ምድር 10 ሦስተኛው ዕጣ ለዛብሎን ነገድ በየወገናቸው ወጣ፤ እነርሱም የተቀበሉት ርስት እስከ ሣሪድ ይደርሳል፤ 11 ድንበሩም ከዚያ በመነሣት ከዳባሼትና በዮቅነዓም ምዕራብ ከሚገኘው ወንዝ እየተዋሰነ በምሥራቅ በኩል እስከ ማርዕላ ይደርሳል። 12 ከሣሪድም ባሻገር በምሥራቅ በኩል ወደ ኪስሎት ታቦር አልፎ እስከ ዳብራትና እስከ ያፊዓ ይደርሳል፤ 13 እንደገናም በዚሁ በምሥራቅ በኩል ወደ ሪሞን በሚወስደው መንገድ ወደ ኔዓ አቅጣጫ ይታጠፍና ወደ ጋትሔፌርና ወደ ዒትቃጺን ይዘልቃል፤ 14 የሰሜኑም ድንበር መመለሻው የይፍታሕኤል ሸለቆ ሆኖ ወደ ሐናቶን አቅጣጫ ይታጠፋል፤ 15 እርሱም ቃጣት፥ ናህላል፥ ሺምሮን፥ ይዳላና ቤተልሔም ተብለው የሚጠሩትን ዐሥራ ሁለት ከተሞችና በዙሪያቸው ያሉትን ታናናሽ ከተሞች ያጠቃልላል፤ 16 ስለዚህም እነዚህ ታላላቅና ታናናሽ ከተሞች ለዛብሎን ነገድ በየወገናቸው የተሰጡ ርስቶች ናቸው። ለይሳኮር ርስት ሆኖ የተመደበ ምድር 17 አራተኛው ዕጣ ለይሳኮር ነገድ በየወገኖቻቸው ወጣ፤ 18 የምድሩም ክልል ኢይዝራኤልን፥ ከሱሎትን፥ ሹኔምን፥ 19 ሐፋራይምን፥ ሺኦንን፥ አናሐራትን፥ 20 ራቢትን፥ ቂሽዮንን፥ አቤጽን፥ 21 ሬሜትን፥ ዔንጋኒምን፥ ዔንሐዳንና ቤትጳጼጽን ይጨምራል፤ 22 ድንበሩም መመለሻው የዮርዳኖስ ወንዝ ሆኖ፥ ከታቦር፥ ከሻሐጹማና ከቤትሼሜሽ ጋር ይዋሰናል፤ እርሱም ዐሥራ ስድስት ከተሞችንና በዙሪያቸው ያሉትን ታናናሽ ከተሞች ሁሉ ያጠቃልላል፤ 23 ስለዚህም እነዚህ ታላላቅና ታናናሽ ከተሞችና ለይሳኮር ነገድ በየወገኖቻቸው ርስት ሆኖ በተሰጠው ምድር ክልል ውስጥ የሚገኙ ናቸው። ለአሴር ርስት ሆኖ የተመደበ ምድር 24 አምስተኛው ዕጣ ለአሴር ነገድ በየወገኖቻቸው ወጣ፤ 25 የምድሩም ክልል ሔልቃትን፥ ሐሊን፥ ቤጤንን፥ አክሻፍን፥ 26 ኣላሜሌክን፥ ዓምዓድንና ሚሽአልን ይጨምራል፤ በምዕራብም ከቀርሜሎስና ከሺሖርሊብናት ይዋሰናል፤ 27 ወደ ምሥራቅም ይታጠፍና ድንበሩ ወደ ቤትዔሜቅና ወደ ነዒኤል በሚወስደው መንገድ ከዛብሎንና ከይፍታሕኤል ሸለቆ እየተዋሰነ ወደ ቤትዳጎን ይዘልቃል። በሰሜንም ወደ ካቡል፥ 28 ወደ ዔብሮን፥ ረሖብ፥ ሐሞንና ቃና አልፎ እስከ ታላቁ ሲዶና ይደርሳል። 29 ድንበሩ እስከ ተመሸገችው እስከ ጢሮስ ከተማ ይደርስና ወደ ራማ ይታጠፋል፤ ከዚያም መመለሻው የሜድትራኒያን ባሕር ሆኖ ወደ ሖሳ ይታጠፋል፤ እርሱም ማሐላብ፥ አክዚብ፥ 30 ዑማ፥ አፌቅና ረሖብ ተብለው የሚጠሩትን ኻያ ሁለት ከተሞችና በዙሪያቸው የሚገኙ ታናናሽ ከተሞችን ይጨምራል፤ 31 ስለዚህ እነዚህ ታላላቅና ታናናሽ ከተሞች ለአሴር ነገድ በየወገኖቻቸው ርስት ሆነው የተሰጡ ድርሻዎች ናቸው። ለንፍታሌም ርስት ሆኖ የተመደበ ምድር 32 ስድስተኛው ዕጣ ለንፍታሌም ነገድ በየወገኖቻቸው ወጣ፤ 33 ድንበሩም ከሔሌፍ በመነሣት በአዳሚኔቄብና በያሚኒያ በኩል መመለሻው የዮርዳኖስ ወንዝ ሆኖ እስከ ላቁም ድረስ እስከ ዳዕናኒም ወርካ ይዘልቃል። 34 ከዚህ በኋላ ድንበሩ በምዕራብ በኩል ወደ አዝኖትታቦር ይታጠፋል፤ ከዚያም ወደ ሁቆቅ ይሄዳል፤ በደቡብ በኩል ዛብሎን፥ በምዕራብ በኩል አሴርን፥ በስተምሥራቅ ዮርዳኖስ የሚያዋስነው ይሁዳን ነው። 35 እንዲሁም የተመሸጉት ከተሞች ጺዲም፥ ጼር፥ ሐማት፥ ራቃት፥ የገሊላ ባሕር፥ 36 አዳማ፥ ራማ፥ ሐጾር፥ 37 ቄዴሽ፥ ኤድረዒ፥ ዔንሐጾር፥ 38 ይርኦን፥ ሚግዳልኤል፥ ሖሬም፥ ቤትዐናትና ቤትሼሜሽ ተብለው የሚጠሩ ዐሥራ ዘጠኝ ከተሞች በዙሪያቸው ታናናሽ ከተሞች ጋር በዚህ ክልል ውስጥ ይገኛሉ፤ 39 ስለዚህ እነዚህ ታላላቅና ታናናሽ ከተሞች ለንፍታሌም ነገድ በየወገናቸው ርስት ሆኖ በተሰጠው ምድር ክልል ውስጥ የሚገኙ ናቸው። ለዳን ርስት ሆኖ የተመደበ ምድር 40 ሰባተኛው ዕጣ ለዳን ነገድ በየወገኖቻቸው የተሰጠው የርስት ድርሻ ነበር፤ 41 የምድሩም ክልል ጾርዓን፥ ኤሽታኦልን፥ ዒርሼሜሽን፥ 42 ሻዓልቢምን፥ አያሎንን፥ ይታላን፥ 43 ኤሎንን፥ ቲምናን፥ ዔቅሮንን፥ 44 ኤልተቄን፥ ጊበቶንን፥ ባዕላትን፥ 45 አይሁድን፥ በኔበራቅን፥ ጋትሪሞንን፥ 46 ሜያርቆን፥ ራቆንና እንዲሁም በኢዮጴ ዙሪያ ያለውን ግዛት ጭምር ያጠቃልላል። 47 የዳንም ሕዝብ ይህን ምድር ለመውረስ የማይቻል ሆኖ ባገኙት ጊዜ ወደ ላዪሽ ሄደው አደጋ በመጣል ከተማይቱን ያዙ፤ ሕዝብዋንም ፈጅተው የራሳቸው ይዞታ አደረጉአት፤ በዚያም ሰፈሩ፤ ላዪሽ ትባል የነበረችውን ከተማ ስሟን ለውጠው በቀድሞ አባታቸው ስም ዳን ብለው ጠሩአት፤ 48 ስለዚህ እነዚህ ትላልቅና ትናንሽ ከተሞች የዳን ልጆች በየወገናቸው ርስት ናቸው። ለኢያሱ ርስት ሆኖ የተመደበ የመጨረሻው ምድር 49 እስራኤላውያን ምድሪቱን ተከፋፍለው በጨረሱ ጊዜ ለነዌ ልጅ ኢያሱ ከምድሪቱ ከፍለው ርስት ሰጡት፤ 50 እግዚአብሔርም ባዘዘው መሠረት በኮረብታማው በኤፍሬም አገር እንዲሰጡት የጠየቃቸውን ቲምናትሴራሕ ተብላ የምትጠራውን ከተማ ሰጡት፤ ያቺንም ከተማ እንደገና ሠርቶ መኖሪያው አደረጋት። 51 ካህኑ አልዓዛር፥ የነዌ ልጅ ኢያሱና የእስራኤል ሕዝብ የነገድ አለቆች በሴሎ በመገናኛው ድንኳን ደጃፍ በእግዚአብሔር ፊት ለእስራኤል ሕዝብ በዕጣ ያከፋፈሉት ርስት ይህ ነው። በዚህም ዐይነት ምድሪቱን አከፋፍለው ጨረሱ። |