Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ኢያሱ 17 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


በዮርዳኖስ ምዕራብ የሰፈረው የምናሴ ነገድ እኩሌታ

1 ይህ የዮሴፍ በኲር ልጅ የነበረው የምናሴ ነገድ ድርሻ የሚከተለው ነው። የምናሴ በኲር ልጅ የገለዓድ አባት ማኪር የጦር ጀግና ስለ ነበረ ገለዓድና ባሳን በርስትነት ተሰጠው።

2 ከዮርዳኖስ በስተ ምዕራብ ያለው ምድር ለቀሩት ለምናሴ ልጆች በየወገናቸው ተሰጠ፤ እነርሱም አቢዔዜር፥ ሔሌቅ፥ አሥሪኤል፥ ሼኬም፥ ሔፌርና ሸሚዳዕ የተባሉት ናቸው፤ የዮሴፍ ልጅ የምናሴ ዘሮች በየወገናቸው የሚከተሉት ናቸው።

3 ጸለጰሐድ የሔፌር ልጅ፥ ሔፌር የገለዓድ ልጅ፥ ገለዓድ የማኪር ልጅ፥ ማኪርም የምናሴ ልጅ ነው፤ ታዲያ ይህ ጸለጰሐድ ሴቶች እንጂ ወንዶች ልጆች አልነበሩትም፤ አምስቱ ሴቶች ልጆቹም ማሕላ፥ ኖዓ፥ ሖግላ፥ ሚልካ እና ቲርጻ ተብለው ይጠሩ ነበር።

4 እነርሱም ወደ ካህኑ አልዓዛር፥ ወደ ነዌ ልጅ ኢያሱና ወደ መሪዎቹ ቀርበው “እንደ ወንዶች ዘመዶቻችን የርስት ድርሻ እንዲሰጠን እግዚአብሔር ሙሴን አዞታል” አሉአቸው። ስለዚህም እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት ለእነርሱ ከወንዶች ዘመዶቻቸው ጋር የርስት ድርሻ ተሰጣቸው፤

5 ምናሴ በዮርዳኖስ ወንዝ በስተምሥራቅ ከሚገኙት ከገለዓድና ከባሳን ጋር በተጨማሪ ዐሥር ዕጣ እንዲደርሰው ተደርጎአል።

6 ሴቶች ዘሮቹ እንደ ወንዶች ዘሮቹ የርስት ድርሻ ስለ ተቀበሉ የገለዓድም ምድር ለቀሩት ለምናሴ ዘሮች ተሰጠ።

7 የምናሴ የርስት ይዞታ ከአሴር ተነሥቶ በሴኬም በስተ ምሥራቅ እስከምትገኘው እስከ ሚክመታት ይደርስ ነበር፤ ድንበሩም ወደ ደቡብ በማለፍ የዔንታፑዓሕን ሕዝብ ይጨምራል፤

8 በታፑሐ ዙሪያ የሚገኘውም ምድር ለምናሴ ተሰጠ፤ በድንበር ላይ የምትገኘው ትንሽዋ የታፑሐ ከተማ ግን የኤፍሬም ዘሮች ይዞታ ነበረች።

9 ድንበሩም ከዚያ ተነሥቶ እስከ ቃና ወንዝ ይደርሳል፤ ከወንዙ በስተ ደቡብ የሚገኙት ከተሞች ምንም እንኳ በምናሴ ግዛት ክልል ውስጥ ቢሆኑ የኤፍሬም ይዞታዎች ነበሩ፤ የምናሴ ድንበር በሰሜን በኩል ከወንዙ እየተዋሰነ መጨረሻው የሜድትራኒያን ባሕር ነበር፤

10 ከዚህም የተነሣ የሁለቱም ምዕራባዊ ወሰን የሜድትራኒያን ባሕር ሆኖ ኤፍሬም በደቡብ፥ ምናሴ በሰሜን እንዲሰፍሩ ተደረገ፤ አሴር በሰሜን ይሳኮር ደግሞ በምሥራቅ ሰፈሩ።

11 በይሳኮርና በአሴር ግዛት ውስጥ ምናሴ ቤትሼንና መንደሮችዋ፥ ይብልዓምና መንደሮችዋ፥ የዶር ኑዋሪዎችና መንደሮችዋ የዕንዶር ኑዋሪዎችና መንደሮችዋ፥ የታዕናክ ኑዋሪዎችና መንደሮችዋ፥ የመጊዶና ኑዋሪዎችና መንደሮችዋ፥ (በሦስተኛው ተራ ዶር የተባለው ናፋት ዶርም ይባላል)። እነዚህም ሁሉ የምናሴ ይዞታዎች ሆኑ።

12 ይሁን እንጂ የምናሴ ልጆች ሕዝቡን አባረው እነዚያን ከተሞች ለመያዝ አልቻሉም፤ ስለዚህም ከነዓናውያን በዚያ መኖርን ቀጠሉ፤

13 እስራኤላውያን በኀይል እየበረቱ ቢሄዱም እንኳ ከነዓናውያንን ሁሉ አላባረሩአቸውም፤ ነገር ግን የጒልበት ሥራ እንዲሠሩላቸው ያስገድዱአቸው ነበር።


ኤፍሬምና የምናሴ ነገድ እኩሌታ ተጨማሪ መሬት መጠየቃቸው

14 የዮሴፍ ነገድ ወደ ኢያሱ ቀርበው “እግዚአብሔር ባርኮን ለበዛነው ለእኛ እንዴት አንድ ዕጣ ብቻ ሰጠኸን?” ብለው ጠየቁት።

15 ኢያሱም መልሶ “ብዙዎች ከሆናችሁና ኮረብታማይቱ የኤፍሬም ምድር ትንሽ ከሆነችባችሁ፥ ፈሪዛውያንና ረፋያውያን ወደሚኖሩበት ምድር ሄዳችሁ ጫካውን መንጥሩ” አላቸው።

16 እነርሱም “ኮረብታማይቱ አገር ለእኛ በቂ አይደለችም፤ ከዚህም ሁሉ ጋር በኢይዝራኤል ሸለቆ በቤትሻንና በዙሪያዋ ባሉት ታናናሽ ከተሞችና በሜዳማው አገር የሚኖሩ ከነዓናውያን ብዙ የብረት ሠረገሎች አሉአቸው” ሲሉ መለሱ።

17 ኢያሱም ለኤፍሬምና በዮርዳኖስ ምዕራብ ለሰፈረው ለምናሴ ነገዶች እንዲህ አላቸው፤ “እናንተ በእውነት ብዙዎች ናችሁ፤ በኀይልም ብርቱዎች ናችሁ፤ አንድ ዕጣ ብቻ ሊኖራችሁ አይገባም፤

18 ስለዚህ ኮረብታማው አገር የእናንተ ይሆናል፤ ጫካም ቢሆን መንጥራችሁ ዳር እስከ ዳር የራሳችሁ ርስት አድርጉት፤ ስለ ከነዓናውያን ጉዳይ የሆነ እንደሆን ምንም የብረት ሠረገሎች ቢኖራቸውና ምንም ብርቱዎች ቢሆኑ ነቃቅላችሁ ልታባርሩአቸው ትችላላችሁ።”

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos