ኢያሱ 14 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምከዮርዳኖስ ወንዝ በስተምዕራብ ያለው ምድር አከፋፈል 1 ካህኑ አልዓዛር፥ የነዌ ልጅ ኢያሱና የእስራኤል ነገድ የቤተሰብ አለቆች በከነዓን ምድር ለእስራኤላውያን አከፋፍለዋቸው የተቀበሉት ርስት ይህ ነው። 2 እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት ከዮርዳኖስ ወንዝ በስተምዕራብ ያለው ግዛት በሙሉ ለዘጠኙ ነገድ ተኩል በዕጣ ተከፈለ። 3 ሙሴ ከዮርዳኖስ በስተ ምሥራቅ ያለውን ምድር ለሁለት ተኩል ነገዶች ርስት አድርጎ ሰጥቶአቸው ነበር፤ ለሌዋውያን ግን በእነርሱ መካከል ርስት አልሰጣቸውም። 4 የዮሴፍ ልጆች ምናሴና ኤፍሬም ሁለት ነገዶች ነበሩ፤ ለሌዋውያንም በምድሪቱ ለመኖሪያቸው የሚሆኑ ከተሞችና ለከብቶቻቸው ማሰማሪያ የሚሆን መሬት በቀር የርስት ድርሻ አልተሰጣቸውም፤ 5 እግዚአብሔር ሙሴን ባዘዘው መሠረት እስራኤላውያን ምድሪቱን ተካፈሉ። ኬብሮን ለካሌብ መሰጠቱ 6 አንድ ቀን ከይሁዳ ነገድ የሆኑ ሰዎች በጌልገላ ወደ ኢያሱ ቀረቡ፤ ከእነርሱ አንዱ የቀኒዛዊው የይፉኔ ልጅ ካሌብ እንዲህ አለው፦ “በቃዴስ በርኔ በነበርንበት ጊዜ እግዚአብሔር በአገልጋዩ በሙሴ አማካይነት ስለ አንተና ስለ እኔ የተናገረውን ታውቃለህ፤ 7 የእግዚአብሔር አገልጋይ ሙሴ የዚህችን ምድር ሁኔታ ለማጥናት ከቃዴስ በርኔ በላከኝ ጊዜ የአርባ ዓመት ጐልማሳ ነበርኩ፤ ለእርሱም አስተማማኝ የሆነ ማስረጃ አቅርቤአለሁ፤ 8 ከእኔ ጋር ሄደው የነበሩ ሰዎች ግን የሕዝቡ ልብ በፍርሃት እንዲቀልጥ አደረጉ፤ እኔ ግን ለአምላኬ ለእግዚአብሔር በታማኝነት ታዛዥ ሆኛለሁ፤ 9 ሙሴ፦ ‘አምላኬን እግዚአብሔርን በሙሉ ልብህ ስለ ተከተልከው የረገጥከው ምድር ለአንተና ለልጆችህ የዘለዓለም ርስት ይሆናል’ ” ብሎ በዚያን ቀን በመሐላ ቃል ገብቶልኝ ነበር። 10 እስራኤል በምድረ በዳ በጉዞ ላይ ሆኖ ሳለ እግዚአብሔር ሙሴን ይህን ቃል ከተናገረበት ቀን ጀምሮ አሁን እንደምታየኝ እግዚአብሔር እንዳለው ይህን አርባ አምስት ዓመት ጠብቆ አኑሮኛል፤ እነሆ አሁን እኔ ሰማኒያ አምስት ዓመት ሆነኝ። 11 ሙሴ በላከኝ ጊዜ እንደ ነበርኩት አሁንም እንደዚያው ብርቱ ነኝ፤ በዚያን ጊዜ ለመዋጋት ለመውጣትና ለመግባት የነበረኝ ጒልበት አሁንም እንደዚያው ነው። 12 አሁን እንግዲህ እግዚአብሔር በዚያን ቀን በሰጠኝ ተስፋ መሠረት ይህን ኮረብታማ አገር ስጠኝ፤ ዐናቃውያን ከታላላቅ የተመሸጉ ከተሞች ጋር እንደ ነበሩ በዚያን ቀን ሰምተሃል፤ እግዚአብሔር እንዳለ እርሱ ከእኔ ጋር ሆኖ አሳድዳቸዋለሁ። 13 ኢያሱም የይፉኔን ልጅ ካሌብን ባረከው፤ ኬብሮንንም ርስት አድርጎ ሰጠው፤ 14 ስለዚህም እርሱ የእስራኤላውያን አምላክ እግዚአብሔርን በሙሉ ልቡ ስለ ተከተለ ኬብሮን እስከ አሁን ድረስ የቀኒዛዊው የይፉኔ ልጅ የካሌብ ዘሮች ይዞታ ናት፤ 15 የኬብሮንም ስም አስቀድሞ ቂርያት አርባዕ ነበር፤ ይህም አርባዕ ከዐናቃውያን መካከል ታላቅ ሰው ነበር። ምድሪቱም ከጦርነት ዐረፈች። |