ኢያሱ 10 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየፀሐይ መቆም 1 ኢያሱ የዐይን ከተማ በጦርነት ከያዘ በኋላ በኢያሪኮና በንጉሥዋ ላይ ባደረገው ዐይነት በፍጹም የደመሰሳት መሆኑንና ንጉሥዋንም መግደሉን የኢየሩሳሌም ንጉሥ አዶኒጼዴቅ ሰማ፤ እንዲሁም የገባዖን ሰዎች ከእስራኤላውያን ጋር ስምምነት አድርገው በሰላም መኖራቸውን ተረዳ። 2 ገባዖን በነገሥታት እንደሚተዳደሩት ከተሞች ትልቅና ከዐይ ትበልጥ የነበረች ከተማ ከመሆንዋም በላይ ሰዎችዋም ብርቱ ጦረኞች ስለ ነበሩ፥ አዶኒጼዴቅ በጣም ፈራ። 3 ስለዚህ የኢየሩሳሌሙ ንጉሥ አዶኒጼዴቅ ሆሃም ተብሎ ለሚጠራው ለኬብሮን ንጉሥ፥ ፒራም ለተባለው ለያርሙት ንጉሥ፥ ያፊዓ ለተባለው ለላኪሽ ንጉሥና ደቢር ለተባለው ለዔግሎን ንጉሥ እንዲህ የሚል መልእክት ላከ፦ 4 “ገባዖን ከኢያሱና ከእስራኤላውያን ጋር በሰላም አብሮ የመኖር ስምምነት ስላደረገች እርስዋን ለመውጋት መጥታችሁ እርዱኝ፤” 5 እነዚህ የኢየሩሳሌም፥ የኬብሮን፥ የያርሙት፥ የላኪሽና የዔግሎን ገዢዎች አምስቱ አሞራውያን ነገሥታት ሠራዊታቸውን አስተባብረው፥ የጦር ግንባር በመፍጠር፥ ገባዖንን ከበው አደጋ ጣሉባት። 6 የገባዖን ሰዎችም ሰፈሩን በጌልገላ አድርጎ ወደነበረው ወደ ኢያሱ እንዲህ ሲሉ መልእክት ላኩበት፦ “በተራራማው አገር የሚኖሩት የአሞራውያን ነገሥታት ሁሉ እኛን ሊወጉን ስለ ተባበሩብን እኛ አገልጋዮችህን ችላ አትበል! በቶሎ ወደ እኛ ወጥተህ እርዳንና አድነን!” 7 ስለዚህም ኢያሱና መላው ሠራዊት፥ ምርጥ የሆኑት ወታደሮች ጭምር ከጌልጌላ ወጥተው ሄዱ፤ 8 እግዚአብሔርም ኢያሱን “እነርሱን አትፍራቸው፤ እኔ አንተን በእነርሱ ላይ ድልን አቀዳጅሃለሁ፤ ከእነርሱ አንድም የሚቋቋምህ አይኖርም” አለው። 9 ኢያሱም ሌሊቱን ሙሉ ከጌልጌላ ወደ ገባዖን ሲገሠግሥ ዐድሮ በአሞራውያን ላይ ድንገተኛ አደጋ ጣለባቸው። 10 እግዚአብሔርም በእስራኤል ሠራዊት ፊት አሞራውያን በድንጋጤ እንዲሸበሩ አደረገ፤ እስራኤላውያንም እነርሱን በገባዖን ዐረዱአቸው፤ የቀሩትንም በቤትሖሮን በኩል እስከ ተራራው መተላለፊያ ቊልቊለት እስከ ዐዜቃና እስከ ማቄዳ ድረስ አሳደዱአቸው። 11 አሞራውያን በመተላለፊያው ቊልቊለት ከእስራኤላውያን ሠራዊት በሚሸሹበት ጊዜ፥ እግዚአብሔር እስከ ዐዜቃ ድረስ ከሰማይ ታላላቅ የበረዶ ድንጋይ አወረደባቸው፤ ስለዚህም እስራኤላውያን ከገደሉአቸው ይልቅ በበረዶው ድንጋይ የሞቱት እጅግ ብዙዎች ነበሩ። 12 እግዚአብሔር አሞራውያንን ለእስራኤላውያን አሳልፎ በሰጠበት ቀን ኢያሱ ከእግዚአብሔር ጋር ተነጋገረ፤ እርሱም በእስራኤል ፊት እንዲህ አለ፦ “ፀሐይ በገባዖን፥ ጨረቃም በኤሎን ሸለቆ ላይ ይቁሙ” አለ። 13 ስለዚህም የእስራኤል ሕዝብ ጠላቶቻቸውን እስኪበቀሉ ድረስ ፀሐይ ቆመ፤ ጨረቃም ካለችበት ሳትንቀሳቀስ ቈየች፤ ይህም በያሻር መጽሐፍ ተጽፎ ይገኛል። ሳይንቀሳቀስ በሰማይ መካከል ቆመ፤ ቀኑንም ሙሉ ሳይጠልቅ ቈየ፤ 14 እግዚአብሔር የሰውን ቃል የሰማበት፥ እንደዚያ ያለ ቀን፥ ከዚያም በፊት ሆነ ከዚያ ወዲህ ታይቶ አይታወቅም፤ በእርግጥም እግዚአብሔር ከእስራኤል ጐን ተሰልፎ ይዋጋላቸው ነበር። 15 ከዚህ በኋላ ኢያሱና ሠራዊቱ በጌልገላ ወደ ነበረው ሰፈር ተመለሱ። ኢያሱ አምስቱን አሞራውያን ነገሥታት መግደሉ 16 አምስቱ አሞራውያን ነገሥታትም አምልጠው በማቄዳ ዋሻ ተደብቀው ነበር፤ 17 እነዚህም አምስቱ ነገሥታት በማቄዳ ዋሻ ውስጥ ተደብቀው መገኘታቸው ለኢያሱ ተነገረው። 18 ኢያሱም እንዲህ ሲል ትእዛዝ ሰጠ፤ “ታላላቅ ድንጋዮች አንከባላችሁ የዋሻውን በር ዝጉ፤ በዚያም ዘብ ጠባቂ አቁሙበት፤ 19 እናንተ ግን በዚያ አትቈዩ፤ ጠላትን እያሳደዳችሁ ከኋላ በኩል አደጋ መጣላችሁን ቀጥሉ፤ ሸሽተው ወደ ከተሞቻቸው እንዲገቡ መንገድ አትስጡአቸው! አምላካችሁ እግዚአብሔር በእነርሱ ላይ ድልን ያቀዳጃችኋልና።” 20 ጥቂቶች ብቻ አምልጠው ወደ የከተሞቻቸው ምሽጎች ገብተው ከሞት ለመትረፍ ቢችሉም እንኳ ኢያሱና የእስራኤል ሰዎች ሁሉንም ዐረዱአቸው። 21 ከዚህ በኋላ የኢያሱ ሰዎች ሁሉ በሰላም ተመልሰው እርሱ ወደ ሰፈረበት ወደ ማቄዳ መጡ። ከዚህም የተነሣ በምድሪቱ በእስራኤላውያን ላይ ደፍሮ ቃል የሚናገር እንኳ አልነበረም። 22 ከዚህም በኋላ ኢያሱ፦ “የዋሻውን በር ከፍታችሁ በማውጣት እነዚያን አምስት ነገሥታት ወደ እኔ አምጡ” ሲል ትእዛዝ ሰጠ፤ 23 ስለዚህም ዋሻው ተከፍቶ እነዚያ አምስቱ የኢየሩሳሌም፥ የኬብሮን፥ የያርሙት፥ የላኪሽና የዔግሎን ነገሥታት እንዲወጡ ተደረገ፤ 24 ወደ ኢያሱም አመጡአቸው፤ ኢያሱም የእስራኤልን ሰዎች ሁሉ ወደ እርሱ ጠራ፤ ከእርሱ ጋር የዘመቱት የጦር መኰንኖችም መጥተው እግራቸውን በነገሥታቱ አንገት ላይ እንዲያደርጉ ትእዛዝ ሰጠ፤ እነርሱም እንደ ታዘዙት አደረጉ። 25 ኢያሱም ለጦር መኰንኖቹ እንዲህ አለ፤ እግዚአብሔር ጦርነት በምትገጥሙአቸው በጠላቶቻችሁ ሁሉ ላይ ልክ እንደዚህ ስለሚያደርግ አትፍሩ አይዞአችሁ፤ ቆራጥነትና ድፍረት ይኑራችሁ። 26 ከዚህም በኋላ ኢያሱ አምስቱን ነገሥታት ገድሎ በአምስት ዕንጨት ላይ ሰቀላቸው፤ ሬሳቸውም እስከ ምሽት ድረስ በዚያው ዋለ። 27 ፀሐይም ስትጠልቅ የነዚያ ነገሥታት ሬሳ ከየተሰቀለበት እንጨት እንዲወርድና ቀድሞ ተደብቀው ወደነበሩበት ዋሻ ውስጥ እንዲጣል ኢያሱ ትእዛዝ ሰጠ፤ ታላላቅ ድንጋዮችንም አንከባለው የዋሻውን ደጃፍ ገጠሙት፤ እስከ አሁን በዚያ ይገኛል። ኢያሱ ጦርነቱን መቀጠሉ 28 በዚያን ቀን ኢያሱ ማቄዳን ያዘ፤ ንጉሥዋንም በሰይፍ ገደለ፤ በከተማይቱ የነበሩትን ሰዎች ሁሉ አንድም ሳያስቀር ፈጀ፤ በማቄዳም ንጉሥ ላይ ያደረገው ቀድሞ በኢያሪኮ ንጉሥ ላይ ባደረገው ዐይነት ነው። 29 ከዚህም በኋላ ኢያሱና ሠራዊቱ ከማቄዳ ሄደው በሊብና ላይ አደጋ ጣሉባት፤ 30 እግዚአብሔርም በርስዋና በንጉሥዋ በእስራኤል ላይ ለእስራኤላውያን ድልን ሰጣቸው፤ ኢያሱም ከተማይቱንና በእርስዋ ያሉትን ሰዎች አጠፋ፤ በንጉሥዋም ላይ በኢያሪኮ ንጉሥ ላይ እንዳደረገው አደረገበት። 31 ከዚህ በኋላ ኢያሱና ሠራዊቱ ከሊብና ወደ ላኪሽ ዘምተው ከበባ በማድረግ፥ አደጋ ጣሉባት፤ 32 እግዚአብሔርም ጦርነቱ በተጀመረ በሁለተኛው ቀን ለእስራኤላውያን በላኪሽ ላይ ድልን ሰጣቸው፤ በሊብና ባደረጉትም ዐይነት በከተማይቱ ያገኙትን ሰው ሁሉ በሰይፍ ፈጁ፤ 33 በዚህ ጊዜ የጌዜር ንጉሥ ሆራም ላኪሽን ለመርዳት መጥቶ ነበር፤ ነገር ግን ኢያሱ እርሱንና ሠራዊቱን ድል አደረገ፤ ከእነርሱም በሕይወት የተረፈ አንድ እንኳ አልነበረም። 34 ቀጥሎም ኢያሱና ሠራዊቱ ከላኪሽ ወደ ዔግሎን ዘምተው ከበባ በማድረግ አደጋ ጣሉበት፤ 35 በዚያኑም ዕለት ከተማይቱን ያዙ፤ በሰይፍ መቱአት፤ ልክ በላኪሽ እንዳደረጉት ዐይነት ያገኙትን ሰው ሁሉ ገደሉ። 36 ከዚህ በኋላ ኢያሱና ሠራዊቱ ከዔግሎን ወጥተው በኬብሮን ላይ አደጋ ጣሉባት። 37 እርስዋንም ይዘው ንጉሡን፥ በከተማይቱና በአካባቢዋም የገጠር ከተሞች ያገኙትን ሁሉ ገደሉ፤ ኢያሱም ልክ በዔግሎን ባደረገው ዐይነት ከተማይቱ እንድትደመሰስ ፈረደባት፤ በእርስዋም ውስጥ በሕይወት የተረፈ አንድም አልነበረም። 38 ከዚህ በኋላ ኢያሱና ሠራዊቱ ወደ ደቢር ተመልሰው በመዝመት አደጋ ጣሉባት፤ 39 ንጉሡንና ከተማዎቹን ሁሉ ያዙ፤ የከተማዎቹንም ሰዎች በሰይፍ ፈጁ፤ ልክ በኬብሮን፥ በሊብናና በነገሥታቱ ላይ እንዳደረጉት በዶቢርም አንድ ሰው እንኳ ሳይተርፋቸው በዚያ ያሉትን ሰዎች ሁሉ ፈጁ። 40 በዚህ ዐይነት ኢያሱ ምድሪቱን በሙሉ፥ የተራራማውን አገር፥ ኔጌብን፥ የተራራውን ቊልቊለትና ነገሥታቱን ሁሉ ያዘ፤ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ባዘዘው መሠረት ሁሉንም ፈጀ እንጂ አንድ ሰው እንኳ በሕይወት እንዲኖር አላስተረፈም። 41 ኢያሱም ከቃዴስ በርኔ እስከ ጋዛ የጎሼንን አካባቢ ሁሉ ጨምሮ፥ እስከ ገባዖን ድረስ ወግቶ ድል አደረገ። 42 ኢያሱ እነዚህን ነገሥታትና ግዛቶቻቸውን ሁሉ በአንድ ዘመቻ ድል ያደረገው የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ለእስራኤል ይዋጋላቸው ስለ ነበረ ነው። 43 ከዚህም በኋላ ኢያሱና ሠራዊቱ በጌልገላ ወደነበረው ሰፈር ተመለሱ። |