ዮናስ 2 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየዮናስ ጸሎት 1 ዮናስ በዓሣው ሆድ ውስጥ ሆኖ እንዲህ ሲል ወደ አምላኩ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ፤ 2 “እግዚአብሔር ሆይ! ተጨንቄ ሳለሁ ወደ አንተ ተጣራሁ፤ አንተም መለስክልኝ፤ ርዳታህን ለማግኘት ጥልቅ ከሆነው ከሙታን ዓለም ወደ አንተ ጮኽኩ፤ አንተም ሰማኸኝ። 3 ጥልቅ ወደ ሆነው ወደ ባሕር መሠረት ጣልከኝ፤ በዙሪያዬም ውሃ ከበበኝ፤ ማዕበልህና ሞገድህ በላዬ ላይ አለፉ። 4 እኔ ከፊትህ የጠፋሁ ነኝ፤ ይሁን እንጂ ቅዱስ መቅደስህን እንደገና አያለሁ። 5 ውሃ እስከ አንገቴ ድረስ አጠለቀኝ፤ ባሕርም ፈጽሞ አሰጠመኝ፤ በባሕር ውስጥም የበቀለው ሣር ቅጠል በራሴ ላይ ተጠመጠመብኝ። 6 ወደ ተራራዎች ሥር ወረድኩ፤ ከዚያ በታች ባለው ምድርም ውስጥ ለዘለዓለም ሊዘጋብኝ ነበር፤ አንተ ግን እግዚአብሔር አምላኬ ሆይ! እኔን ከጥልቁ ውሃ አውጥተህ ሕይወቴን ታድናለህ። 7 ሕይወቴ እየተዳከመ በሄደ ጊዜ እግዚአብሔርን አስታወስኩ፤ ወደ አንተ ወደ አምላኬ ጸለይኩ፤ ጸሎቴም ወደ ቤተ መቅደስህ ወደ አንተ መጣ። 8 የሐሰት አማልክትን የተከተሉ ሁሉ፥ ለአንተ ያላቸውን ታማኝነት ትተዋል። 9 ደኅንነት ከእግዚአብሔር ነው፤ ስለዚህ ከምስጋና መዝሙር ጋር መሥዋዕትን ለአንተ አቀርባለሁ፤ የተሳልኩትንም እሰጣለሁ።” 10 ከዚህ በኋላ በእግዚአብሔር ትእዛዝ ዓሣው ዮናስን በደረቅ ምድር ላይ ተፋው። |