Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ኤርምያስ 52 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


የኢየሩሳሌም አወዳደቅ
( 2ነገ. 24፥18-20 ፤ 25፥1-7 )

1 ሴዴቅያስ በይሁዳ በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ኻያ አንድ ዓመት ነበር፤ እርሱም በኢየሩሳሌም ዐሥራ አንድ ዓመት ገዛ፤ የእናቱም ስም ሐሙጣል ይባል ነበር፤ እርስዋም የሊብናው የኤርምያስ ልጅ ነበረች።

2 ከዚያ በፊት ንጉሥ ኢዮአቄም እንዳደረገው ሁሉ ንጉሥ ሴዴቅያስም እግዚአብሔርን አሳዘነ።

3 ስለዚህም እግዚአብሔር በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ሕዝብ ላይ ተቈጥቶ ከፊቱ አስወገዳቸው። ሴዴቅያስም በባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ላይ ዐመፀ፤

4 ሴዴቅያስ በነገሠ በዘጠነኛው ዓመት በዐሥረኛው ወር፥ በዐሥረኛው ቀን የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ሠራዊቱን ሁሉ አስከትቶ በመምጣት በኢየሩሳሌም ላይ አደጋ ለመጣል አስከበባት፤ ሠራዊቱም በከተማይቱም ዙሪያ ሰፈረ፤ በቅጥሩም ዙሪያ ዐፈር ቈለለ።

5 ሴዴቅያስ እስከ ነገሠበት እስከ ዐሥራ አንደኛ ዓመት ድረስ ከበቡአት።

6 በዚያው ዓመት በአራተኛው ወር፥ በዘጠነኛው ቀን፥ ሕዝቡ የሚመገቡት አጥተው ራብ ጸና።

7 የከተማይቱ ቅጽሮች ተጣሱ፤ ባቢሎናውያን ከተማይቱን ከበው ሳለ ወታደሮቹ በሌሊት አምልጠው ነበር፤ ወደ ንጉሡ የአትክልት ቦታ በሚወስደው መንገድ በኩል በማለፍ ሁለቱን ቅጽሮች በሚያገናኘው በቅጽር በር ወጥተው ወደ ዮርዳኖስ ሸለቆ አቅጣጫ ሸሹ፤

8 ነገር ግን የባቢሎን ሠራዊት ሴዴቅያስን አሳዶ በኢያሪኮ አጠገብ በሚገኝ ሜዳ ላይ ማረከው፤ ወታደሮቹም ሁሉ ከድተውት ተበታተኑ።

9 ሴዴቅያስም ወደ ንጉሥ ናቡከደነፆር ተወሰደ፤ ናቡከደነፆር በዚያን ጊዜ በሐማት ግዛት ሪብላ ተብላ በምትጠራ ከተማ ውስጥ ነበር፤ እዚያም ናቡከደነፆር በሴዴቅያስ ላይ የፍርድ ውሳኔ አስተላለፈበት።

10 ይኸውም በሪብላ ሴዴቅያስ ራሱ በዐይኑ እያየ ወንዶች ልጆቹ ተገደሉ፤ እንዲሁም የይሁዳን ባለ ሥልጣኖች አስገደለ።

11 ከዚያም በኋላ የሴዴቅያስን ዐይኖች አውጥቶ በእግር ብረት በማሰር ወደ ባቢሎን ወሰደው፤ እስከ ሞተበትም ጊዜ ድረስ በባቢሎን እስረኛ አደረገው።


የቤተ መቅደሱ መፍረስ
( 2ነገ. 25፥8-17 )

12 ናቡከደነፆር በባቢሎን በነገሠ በዐሥራ ዘጠነኛው ዓመት በአምስተኛው ወር በዐሥረኛው ቀን የንጉሡ የክብር ዘብ አዛዥ የሆነው ናቡዛርዳን ኢየሩሳሌም ገባ፤

13 ቤተ መቅደሱን፥ ቤተ መንግሥቱንና በኢየሩሳሌም የነበሩ የታላላቅ ሰዎችን መኖሪያ ቤቶች እንዲሁም ታላላቅ ሕንጻዎችን አቃጠለ፤

14 በክብር ዘቡ አዛዥ ይመራ የነበረው ሠራዊት የኢየሩሳሌምን ቅጽር አፈራረሰ።

15 የክብር ዘቡ አዛዥ ናቡዛርዳን ከሕዝቡ መካከል በጣም ድኻ የሆኑትን፥ በከተማ ውስጥ ቀርተው የነበሩትን፥ በመክዳት ወደ ባቢሎን ሠራዊት ተጠግተው የነበሩትንና ከእጅ ባለሙያዎች መካከል ቀርተው የነበሩትን ሁሉ ማርኮ ወደ ባቢሎን ወሰዳቸው።

16 ነገር ግን በይሁዳ የመጨረሻ ድኾች የነበሩትን ሕዝብ ተወ፤ እነርሱም የወይን ተክል ኰትኳቾችና አራሾች እንዲሆኑ አደረገ።

17 ባቢሎናውያን በቤተ መቅደስ የነበሩትን ከነሐስ የተሠሩ ዐምዶችን፥ ተሽከርካሪ የዕቃ ማስቀመጫዎችንና፥ ከነሐስ የተሠራውንም የውሃ ማጠራቀሚያ ገንዳ ሰባበሩ፤ ነሐሱንም ሁሉ ወደ ባቢሎን ወሰዱት።

18 ድስቶችን መሠዊያውን የሚያጸዱበትን የአካፋ ቅርጽ ያለውን መጫሪያውንና የዐመድ ማጠራቀሚያዎቹን ጐድጓዳ ሳሕኖችን፥ ጭልፋዎችንና ለቤተ መቅደሱ አገልግሎት ከነሐስ የተሠሩ ሌሎችንም ንዋያተ ቅድሳት ሁሉ ወሰዱ።

19 የክብር ዘቡ አዛዥ ጐድጓዳ ሳሕኖችን፥ የዕጣን ማጠኛዎችን፥ ጐድጓዳ ወጭቶችን፥ ድስቶችን፥ መቅረዞችን፥ ጭልፋዎችን፥ የመጠጥ መሥዋዕት ማቅረቢያዎችን፥ በወርቅና በብር የተሠሩ ዕቃዎችን ሁሉ ወሰደ።

20 እንዲሁም ሁለቱን ምሰሶዎች፥ አንዱን ገንዳ፥ ዐሥራ ሁለት በኰርማ ቅርጽ ከነሐስ የተሠሩትን የገንዳ ማስቀመጫዎች፥ ንጉሥ ሰሎሞን ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መገልገያ አሠርቶአቸው የነበሩትን ተሽከርካሪ መቆሚያዎችን ሁሉ ወሰደ። እነዚህ ዕቃዎች የተሠሩበት ነሐስ ከባድ ከመሆኑ የተነሣ ሊመዘን አልተቻለም።

21 ሁለቱ ዐምዶች አንድ ዐይነት ቅርጽ ያላቸው ሆነው እያንዳንዳቸው ስምንት ሜትር ቁመትና አምስት ሜትር የሚያኽል ዙሪያ ነበራቸው፤ ውስጣቸውም ክፍት ነበር፤ ብረቱም ሰባ አምስት ሚሊ ሜትር ውፍረት ነበረው፤

22 የእያንዳንዱም ምሰሶ ጒልላት ከነሐስ የተሠራ ሆኖ ሁለት ሜትር ያኽል ከፍታ የነበረውና በመረብና በሮማን ፍሬ ቅርጽ የተጌጠ ነበር።

23 በስተውጪ በኩል ዘጠና ስድስት የሮማን ፍሬ ቅርጾች የነበሩ ሲሆን በመረቡ ዙሪያ መቶ የሮማውያን ፍሬ ቅርጾች ነበሩ።


የይሁዳ ሕዝብ ወደ ባቢሎን መወሰዱ
( 2ነገ. 25፥18-21 ፤ 27-30 )

24 ከዚያም ሁሉ ጋር የሠራዊቱ አዛዥ ናቡዛርዳን ሊቀ ካህናቱን ሠራያን፥ በማዕርግ የእርሱ ምክትል የሆነውን ካህኑን ሶፎንያስንና ሌሎችንም ሦስት የቤተ መቅደስ በር ጠባቂዎችን አስሮ ወሰደ፤

25 ከከተማይቱም የወታደሮች አዛዥ የሆነ አንድ ባለ ሥልጣንና እስከዚያ ጊዜ ድረስ በከተማይቱ ውስጥ የተገኙትን ሰባቱን የንጉሡን አማካሪዎች፥ የወታደራዊ ጉዳዮች ጸሐፊ የነበረውን የጦር አዛዡን ረዳትና ሌሎችንም ሥልሳ ታላላቅ ሰዎች ወሰደ፤

26 ናቡዛርዳን እነዚህን ሁሉ በሐማት ግዛት ውስጥ በሪብላ ከተማ ወደነበረው ወደ ባቢሎን ንጉሥ ወሰዳቸው፤

27 ንጉሡም በዚያው አስደብድቦ በማሠቃየት በሞት ቀጣቸው። በዚህም ዐይነት የይሁዳ ሕዝብ ከአገራቸው ተማርከው ተወሰዱ፤

28 ናቡከደነፆር ማርኮ የወሰዳቸው ሰዎች ብዛት ማስታወሻ ይህ ነው፤ በነገሠ በሰባተኛ ዓመቱ የማረካቸው ሦስት ሺህ ኻያ ሦስት አይሁድ፥

29 በነገሠ በዐሥራ ስምንት ዓመቱ ስምንት መቶ ሠላሳ ሁለት ሰዎች ከኢየሩሳሌም፥

30 እንዲሁም በነገሠ በሃያ ሦስት ዓመቱ ሰባት መቶ አርባ አምስት አይሁድ በናቡዛርዳን እጅ ተማርከው ተወስደዋል፤ በጠቅላላው ተማርከው የተወሰዱት ሰዎች ቊጥር አራት ሺህ ስድስት መቶ ነበር።

31 የይሁዳ ንጉሥ ኢኮንያን በተማረከ በሠላሳ ሰባተኛው ዓመት በዐሥራ ሁለተኛው ወር ከወሩም በሃያ አምስተኛው ቀን የባቢሎን ንጉሥ ኤዌል መሮዳክ በነገሠበት ዓመት የይሁዳን ንጉሥ ኢኮንያንን ከእስር ፈታው።

32 ኤዊል መሮዳክ ኢኮንያንን በመልካም ሁኔታ አነጋገረው፤ እንደ እርሱ ተማርከው በባቢሎን በስደት ከሚኖሩት ነገሥታት ሁሉ የላቀ የክብር ቦታ ሰጠው።

33 ስለዚህም ኢኮንያን በእስር ቤት የነበረውን ልብስ ለውጦ እስከ ዕድሜው ፍጻሜ ድረስ ከንጉሡ ማዕድ ዘወትር እንዲመገብ ተፈቀደለት።

34 በሚኖርበት ዘመን ሁሉ በየቀኑ ለማናቸውም ለሚያስፈልገው ነገር ያውለው ዘንድ የዘወትር አበል ይሰጠው ነበር።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos