ኤርምያስ 40 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምከገዳልያ ጋር የኤርምያስ አኗኗር 1 የክብር ዘብ አዛዡ ናቡዛርዳን እኔን በራማ ነጻ ከለቀቀኝ በኋላ እግዚአብሔር ተናገረኝ፤ ከዚያ በፊት እኔ እዚያ የተወሰድኩት አሁን ከኢየሩሳሌምና ከይሁዳ በመማረክ ታስረው ወደ ባቢሎን ከተወሰዱት ሕዝብ ሁሉ ጋር በሰንሰለት ታስሬ ነበር። 2 የክብር ዘብ አዛዡ እኔን ገለል አድርጎ ለብቻ እንዲህ አለኝ፦ “አምላክህ እግዚአብሔር ይህችን ምድር እንደሚያጠፋት አስቀድሞ ተናግሮ ነበር፤ 3 አደርጋለሁ ብሎ ያቀደውን ሁሉ እነሆ አሁን ፈጽሞታል፤ ይህም ሁሉ የሆነው እናንተ ኃጢአት በመሥራታችሁና ለእግዚአብሔር ባለመታዘዛችሁ ምክንያት ነው። 4 እነሆ እኔ በእጅህ ላይ ያለውን ሰንሰለት ፈትቼ ነጻ አደርግሃለሁ፤ ከእኔ ጋር ወደ ባቢሎን ለመውረድ ብትፈልግ እንደ ወደድክ አድርግ፤ እኔም ለአንተ እንክብካቤ አደርግልሃለሁ፤ ወደዚያ ለመሄድ ካልፈለግህ ግን መቅረት ትችላለህ፤ እነሆ አገሪቱ በሞላ በፊትህ ስለ ሆነች ወደ መረጥከው ቦታ መሄድ ትችላለህ።” 5 እኔም መልስ ሳልሰጥ ናቡዛርዳን “እንግዲያውስ የሳፋን የልጅ ልጅ ወደ ሆነው ወደ አሒቃም ልጅ ወደ ገዳልያ ዘንድ ሂድ፤ የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ገዳልያን የይሁዳ ከተሞች ገዢ አድርጎ ሾሞታል፤ ስለዚህም ከእርሱ ጋር ሆነህ በሕዝቡ መካከል መኖር ትችላለህ፤ ወይም ይጠቅመኛል ብለህ ወደምታስበው ስፍራ ሁሉ መሄድ ትችላለህ።” ከዚያም በኋላ ልዩ ስጦታና ይዤው የምሄደውንም ስንቅ ሰጥቶ አሰናበተኝ። 6 እኔም ከገዳልያ ጋር ለመኖር ወደ ምጽጳ ሄድኩ፤ እዚያም በምድሪቱ ላይ በቀሩት ሕዝብ መካከል አብሬ ኖርኩ። ገዳልያ የይሁዳ ገዢ ሆኖ መሾሙ ( 2ነገ. 25፥22-24 ) 7 ከይሁዳ የጦር መኰንኖችና ወታደሮች ጥቂቶቹ ገና እጃቸውን አልሰጡም ነበር፤ እነርሱም የባቢሎን ንጉሥ ገዳልያን በሀገሪቱ ላይ ገዢ አድርጎ እንደ ሾመውና ወደ ባቢሎን ሳይወሰዱ በሀገሪቱ ለቀሩት ድኾች ኀላፊ ያደረገው መሆኑን ሰሙ፤ 8 ስለዚህ የነታንያ ልጅ እስማኤል፥ የቃሬሐ ልጆች ዮሐናንና ዮናታን፥ የታንሑሜት ልጅ ሠራያ፥ ከነጦፋ የዔፋይ ልጆች፥ ከማዕካም የዛንያ ከሰዎቻቸው ሁሉ ጋር በምጽጳ ወደሚገኘው ወደ ገዳልያ መጡ። 9 ገዳልያም እንዲህ ሲል ማለላቸው፦ “በእውነት ቃል ልግባላችሁ፤ ለባቢሎናውያን እጃችሁን ስለ መስጠት ምንም የሚያስፈራችሁ ነገር የለም፤ በዚህች ምድር ሰፍራችሁ ኑሮአችሁን መሥርቱ፤ ለባቢሎን ንጉሥ ገብሩ፤ ለእናንተም ሁሉ ነገር መልካም ይሆንላችኋል፤ 10 እኔም በዚህቹ በምጽጳ ከእናንተ ጋር ስለምኖር ባቢሎናውያን በሚመጡበት ጊዜ የእናንተ ወኪል ሆኜ እቆምላችኋለሁ፤ እናንተ ግን በምትኖሩባቸው መንደሮች ሁሉ የወይኑን ዘለላ፥ የወይራውን ዘይትና የሌላውን ተክል ፍሬ ሰብስባችሁ አከማቹ” 11 ይህ በዚህ እንዳለ በሞአብ፥ በዐሞን፥ በኤዶምና በሌሎችም አገሮች የሚኖሩ እስራኤላውያን የባቢሎን ንጉሥ ጥቂት የአይሁድ ቅሪቶችን ማስቀረቱንና ለእነርሱም ገዳልያን ገዢ አድርጎ መሾሙን ሰሙ፤ 12 ስለዚህም ተበታትነው የሚኖሩባቸውን ስፍራዎች ሁሉ ትተው ወደ ይሁዳ ተመለሱ፤ በምጽጳ ወደሚገኘው ወደ ገዳልያም መጥተው እጅግ ብዙ የሆነ የወይን ዘለላና የሌላውንም ተክል ፍሬ በመሰብሰብ አከማቹ። የገዳልያ መገደል ( 2ነገ. 25፥25-26 ) 13 ከዚህ በኋላ ዮሐናንና ቀደም ብለው እጃቸውን ያልሰጡ የጦር አለቆች ሁሉ በምጽጳ ወደሚገኘው ወደ ገዳልያ መጥተው፥ 14 “እስማኤል አንተን እንዲገድልህ የዐሞን ንጉሥ በዐሊስ የላከው መሆኑን አታውቅምን?” ብለው ጠየቁት። ገዳልያ ግን ይህን አላመነም፤ 15 ከዚህም በኋላ ዮሐናን በምጽጳ በግል እንዲህ አለው፦ “ይህን ያደረገ ማን እንደ ሆነ ሳይታወቅ ሄጄ እስማኤልን ልግደለው፤ እንዴት እርሱ አንተን ሊገድልህ ይደፍራል? እርሱ ከገደለህ እኮ በዙሪያህ ለተሰበሰቡት አይሁድ መበታተን ምክንያት ይሆናል፤ በይሁዳ ምድር ከምርኮ በቀሩትም ሕዝብ ላይ ታላቅ ጥፋትን ያመጣል።” 16 ገዳልያ ግን “ስለ እስማኤል የምትለው ሁሉ እውነት አይደለምና ከቶ ይህን አታድርግ” ሲል መለሰለት። |