ኤርምያስ 39 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየኢየሩሳሌም በጠላት እጅ መውደቅ 1 ሴዴቅያስ በይሁዳ በነገሠ በዘጠነኛው ዓመት በዐሥረኛው ወር የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ከሠራዊቱ ሁሉ ጋር መጥቶ በኢየሩሳሌም ላይ ከበባ አደረገ። 2 ሴዴቅያስ በነገሠ በዐሥራ አንደኛው ዓመት፥ በአራተኛው ወር፥ በዘጠነኛው ቀን የከተማይቱ ቅጽሮች ተጣሱ። 3 የኢየሩሳሌም ከተማ በተያዘች ጊዜ የባቢሎን ንጉሥ ባለ ሥልጣኖች መጥተው በመካከለኛው ቅጽር በር ስፍራ ስፍራቸውን ያዙ፤ ከእነርሱም መካከል፥ ኔርጋልሻሬጼር፥ ሣምጋር ነቦ፥ ሣርሰኪምና ሌላው ኔርጋልሻሬጼርና እንዲሁ ሌሎችም ይገኙባቸዋል። 4 ንጉሥ ሴዴቅያስና ወታደሮቹ ሁሉ የሆነውን ነገር ባዩ ጊዜ በሌሊት ከከተማይቱ ወጥተው ለማምለጥ ሞከሩ፤ በቤተ መንግሥቱ የአትክልት ቦታ በኩል አድርገው ሁለቱን ቅጽሮች በሚያገናኘው መውጫ በር አቋርጠው ወደ ዮርዳኖስ ሸለቆ አቅጣጫ አመለጡ። 5 ነገር ግን የባቢሎን ሠራዊት ከኋላቸው ተከትሎ በማሳደድ በኢያሪኮ አጠገብ በሚገኝ ሜዳ ላይ ደረሱበትና ሴዴቅያስን ማረኩት፤ ከዚህ በኋላ ወደ ንጉሥ ናቡከደነፆር አመጡት፤ በዚያን ጊዜ ንጉሥ ናቡከደነፆር በሐማት ግዛት ሪብላ ተብላ በምትጠራ ከተማ ውስጥ ነበር፤ ንጉሥ ናቡከደነፆርም እዚያው በሴዴቅያስ ላይ የፍርድ ውሳኔ አስተላለፈበት። 6 ይኸውም በሪብላ ንጉሥ ሴዴቅያስ ዐይኑ እያየ ልጆቹ እንዲገደሉ ተደረገ፤ የይሁዳ ባለሥልጣኖችም ሁሉ ሞት ተፈረደባቸው። 7 ከዚህም ሁሉ በኋላ የሴዴቅያስን ዐይኖች አወጣ፤ ወደ ባቢሎንም ለመውሰድ በነሐስ ሰንሰለት አሰረው። 8 ባቢሎናውያንም የኢየሩሳሌምን ቅጽር ሁሉ አፈረሱ፤ ቤተ መንግሥቱንና የሕዝቡን መኖሪያ ቤት ሁሉ በእሳት አቃጠሉ፤ 9 በመጨረሻም የባቢሎን ንጉሥ የክብር ዘቡ አዛዥ ናቡዛርዳን በከተማ የቀሩትን ሕዝብና ቀደም ብለው ወደ እርሱ ከድተው የገቡትንም ሁሉ በአንድነት ሰብስቦ በእስረኛነት ወደ ባቢሎን ወሰዳቸው፤ 10 ምንም ሀብት ያልነበራቸውን ድኾች ብቻ በይሁዳ ምድር ተወ፤ ለእነርሱም የወይን ተክል ቦታዎችንና የሚያርሱት መሬት ሰጣቸው። የኤርምያስ መፈታት 11 ናቡከደነፆር የክብር ዘብ አዛዡን ናቡዛርዳንን እንዲህ ሲል አዘዘው፤ 12 “ሂድ፥ ኤርምያስን ፈልገህ አግኘውና ተገቢውን ጥንቃቄ አድርግለት፤ እርሱ የሚፈልገውን ሁሉ አድርግለት እንጂ በምንም ነገር እንዳትጐዳው።” 13 ስለዚህም ናቡዛርዳን፥ ናቡሻዝባንና ኔርጋልሻሬጼር ተብለው ከሚጠሩትና ከሌሎችም የባቢሎን ባለ ሥልጣኖች ጋር ሆኖ፥ 14 ታስሬበት ከነበረው በቤተ መንግሥቱ ግቢ ከሚገኘው ዘብ ጠባቂዎች ክፍል እንድወጣ አስደረገ፤ እኔም የሳፋን የልጅ ልጅ በሆነው በአሒቃም ልጅ በገዳልያ እጅ ወደ ቤቴ ተወሰድኩ፤ እኔም ከሕዝቤ ጋር በዚያ ኖርኩ። ለአቤሜሌክ የተሰጠ ተስፋ 15 በቤተ መንግሥቱ አደባባይ በእስራት ላይ ሳለሁ የእግዚአብሔር ቃል ወደኔ መጣ፤ 16 የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ለኢትዮጵያዊው አቤሜሌክ እንዲህ ብዬ እንድነግረው አዘዘኝ፦ “ልክ ከዚህ በፊት እንደ ተናገርኩት በዚህች ከተማ ላይ ብልጽግናን ሳይሆን ጥፋትን አመጣለሁ፤ በዚህችም ከተማ ሆነህ ይህ ሁሉ ሲፈጸም በዐይንህ ታያለህ፤ 17 ነገር ግን በዚያን ቀን እኔ እግዚአብሔር አንተን አድንሃለሁ፤ ለምትፈራቸው ጠላቶችህ ተላልፈህ አትሰጥም፤ 18 እኔ በሰላም ስለምጠብቅህ አትሞትም፤ በእኔ ስለ ታመንክ በሕይወት ትተርፋለህ፤ እኔ እግዚአብሔር ይህን ተናግሬአለሁ።” |