ዘፍጥረት 48 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምያዕቆብ ኤፍሬምንና ምናሴን እንደ ልጆቹ አድርጎ በመቀበል መባረኩ 1 ጥቂት ጊዜ ካለፈ በኋላ “አባትህ ታሞአል” ተብሎ ለዮሴፍ ተነገረው፤ ስለዚህ ዮሴፍ ሁለቱን ልጆቹን ምናሴንና ኤፍሬምን ይዞ ያዕቆብን ለማየት ሄደ። 2 ያዕቆብ ልጁ ዮሴፍ ሊጐበኘው መምጣቱን በሰማ ጊዜ ሰውነቱን አበረታቶ በመኝታው ላይ ተቀመጠ። 3 ያዕቆብ ዮሴፍን እንዲህ አለው፤ “ሁሉን የሚችል አምላክ በከነዓን ምድር ሎዛ በምትባል ቦታ ተገለጠልኝ፤ ባረከኝም፤ 4 ደግሞም ‘ዘርህን አበዛለሁ፤ ተወላጆችህም ብዙ ሕዝቦች ይሆናሉ፤ ይህችንም ምድር ከአንተ በኋላ ለሚመጡት ዘሮችህ ለዘለዓለም ርስት አድርጌ እሰጣቸዋለሁ’ አለኝ።” 5 ያዕቆብ ንግግሩን በመቀጠል እንዲህ አለ፤ “ልጄ ዮሴፍ እኔ እዚህ ከመምጣቴ በፊት በግብጽ ምድር የተወለዱልህ ሁለት ልጆችህ ከእንግዲህ የእኔ ልጆች ናቸው፤ ኤፍሬምና ምናሴ እንደ ሮቤልና እንደ ስምዖን ይቈጠራሉ። 6 ከእንግዲህ ወዲህ ሌሎች ልጆች ቢወለዱልህ የአንተ ናቸው፤ ርስት የሚያገኙትም በኤፍሬምና በምናሴ ስም በመጠራት ይሆናል። 7 ከመስጴጦምያ ስመለስ በከነዓን ምድር ገና ከኤፍራታ ሳልርቅ እናትህ ራሔል ሞተችብኝ፤ እርስዋን ወደ ኤፍራታ በሚወስደው መንገድ ዳር ቀበርኋት።” (ይህችም ኤፍራታ ዛሬ ቤተልሔም ተብላ የምትጠራው ቦታ ነች።) 8 ያዕቆብ የዮሴፍን ልጆች ባየ ጊዜ “እነዚህ ልጆች እነማን ናቸው?” ብሎ ጠየቀ። 9 ዮሴፍም “እነዚህ እግዚአብሔር በዚህ አገር ሳለሁ የሰጠኝ የእኔ ልጆች ናቸው” ብሎ ለአባቱ መለሰለት። ያዕቆብም “እባርካቸው ዘንድ ወደ እኔ አቅርብልኝ” አለው። 10 የያዕቆብ ዐይኖች በእርጅናው ምክንያት ስለ ደከሙ አጥርቶ ማየት አይችልም ነበር፤ ስለዚህ ዮሴፍ ልጆቹን ወደ እርሱ አቀረበለት፤ እርሱም ዕቅፍ አድርጎ ሳማቸው። 11 ዮሴፍንም “አንተን እንደገና አያለሁ ብዬ አላሰብኩም ነበር፤ እግዚአብሔር ግን አንተን ብቻ ሳይሆን ልጆችህንም ጭምር አሳየኝ” አለው። 12 ዮሴፍ ልጆቹን ከያዕቆብ ጒልበት ፈቀቅ አደረገና ወደ መሬት ጐንበስ ብሎ ሰገደ። 13 ዮሴፍ ሁለቱን ልጆቹን ወስዶ ኤፍሬምን በቀኙ ለያዕቆብ በስተግራው በኩል፥ ምናሴን በግራው ለያዕቆብ በስተቀኝ በኩል አድርጎ አቀረበለት። 14 ያዕቆብ ግን እጆቹን በማመሳቀል አስተላልፎ ቀኝ እጁን በታናሹ በኤፍሬም ራስ ላይ፥ ግራ እጁን በበኲሩ በምናሴ ራስ ላይ አኖረ። 15 ከዚህ በኋላ ዮሴፍን እንዲህ ሲል ባረከው፦ “አባቶቼ አብርሃምና ይስሐቅ መንገዱን በመከተል ያገለገሉትና እኔንም ሕይወቴን ሙሉ እስከ ዛሬ ድረስ እረኛ ሆኖ የጠበቀኝ አምላክ እነዚህን ልጆች ይባርክ! 16 እኔን ከጒዳት ሁሉ ያዳነኝ መልአክ እነርሱንም ይጠብቃቸው። የእኔ ስም፥ የአባቶቼም የአብርሃምና የይስሐቅ ስም በነዚህ ልጆች ሲታወስ ይኑር፤ ዘራቸውም በምድር ላይ ይብዛ።” 17 ዮሴፍ አባቱ ቀኝ እጁን በኤፍሬም ራስ ማድረጉን ባየ ጊዜ ቅር ተሰኘ፤ ስለዚህ ከኤፍሬም ራስ ላይ አንሥቶ በምናሴ ራስ ላይ ለማኖር የአባቱን እጅ ያዘ፤ 18 “አባቴ ሆይ፥ እንደዚህ አይደለም፤ በኲሩ ይህኛው ስለ ሆነ ቀኝ እጅህን በእርሱ ራስ ላይ አኑር” አለው። 19 አባቱ ግን “ዐውቄአለሁ፤ ልጄ ዐውቄአለሁ፤ የምናሴም ዘር ታላቅ ሕዝብ ይሆናል፤ ይሁን እንጂ የእርሱ ታናሽ ወንድም ከእርሱ ይበልጥ ታላቅ ይሆናል፤ ዘሮቹም ታላላቅ ሕዝቦች ይሆናሉ” አለ። 20 ስለዚህ በዚያን ቀን እንዲህ ሲል ባረካቸው፤ “እስራኤላውያን በሚመርቁበት ጊዜ የእናንተን ስም በማስታወስ፥ ‘እግዚአብሔር እንደ ኤፍሬምና እንደ ምናሴ ያድርጋችሁ’ ይላሉ።” በዚህ አኳኋን ያዕቆብ ኤፍሬምን ከምናሴ አስቀደመው። 21 ከዚህ በኋላ ያዕቆብ ዮሴፍን እንዲህ አለው፤ “እነሆ፥ እኔ የምሞትበት ጊዜ ተቃርቦአል፤ ነገር ግን እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ነው፤ ወደ ቀድሞ አባቶቻችሁም ምድር ይመልሳችኋል፤ 22 በሰይፌና በቀስቴ ከአሞራውያን እጅ የወሰድኩትን ለሙን ምድር ሴኬምን፥ ከወንድሞችህ ጋር ከምታገኘው ድርሻ በላይ ለአንተ ብቻ ሰጥቼሃለሁ።” |