ዘፍጥረት 35 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምእግዚአብሔር ያዕቆብን በቤትኤል መባረኩ 1 እግዚአብሔር ያዕቆብን “አሁን ተነሥተህ ወደ ቤትኤል ሂድና እዚያ ኑር፤ በዚያም ከወንድምህ ከዔሳው ሸሽተህ በሄድክ ጊዜ ለተገለጥኩልህ አምላክ ለእኔ መሠዊያ ሥራ” አለው። 2 ስለዚህ ያዕቆብ ለቤተሰቡና አብረውት ለነበሩት ሰዎች ሁሉ እንዲህ አላቸው፤ “በእናንተ ዘንድ ያሉትን ባዕዳን አማልክት አስወግዱ፤ ሰውነታችሁን አንጹ፤ ንጹሕ ልብስም ልበሱ፤ 3 ከዚህ ተነሥተን ወደ ቤትኤል እንውጣ፤ በዚያም ከዚህ በፊት በተቸገርኩ ጊዜ ጸሎቴን ሰምቶ ለረዳኝና በሄድኩበት ስፍራ ሁሉ ከእኔ ላልተለየኝ አምላክ መሠዊያ እሠራለሁ።” 4 ስለዚህም በእርሱ ዘንድ የነበሩትን ባዕዳን አማልክት ሁሉ አምጥተው ለያዕቆብ ሰጡት፤ እንዲሁም በየጆሮአቸው አድርገውት የነበረውን ጒትቻ ሁሉ አውልቀው ሰጡት፤ እርሱም ሁሉንም ወሰደና በሴኬም አጠገብ በነበረው የወርካ ዛፍ ሥር ቀበራቸው። 5 ያዕቆብና ልጆቹ ያንን ስፍራ ትተው ለመሄድ ተነሡ፤ እግዚአብሔር በዙሪያቸው በነበሩት ሰዎች ላይ ፍርሀትና ድንጋጤ ስላሳደረባቸው ሊያሳድዱአቸው አልደፈሩም። 6 ያዕቆብ አብረውት ከነበሩት ሰዎች ጋር ሆኖ ወደ ሎዛ ደረሰ፤ ሎዛ ቤትኤል ተብላ የምትጠራው በከነዓን ምድር የምትገኝ ስፍራ ናት። 7 ያዕቆብ እዚያ መሠዊያ ሠርቶ “ኤል ቤትኤል” ብሎ ሰየመው፤ ከወንድሙ ፊት ሸሽቶ በሄደበት ጊዜ እግዚአብሔር የተገለጠለት በዚህ ስፍራ ነበር። 8 እዚያም የርብቃ ሞግዚት ዴቦራ ሞተች፤ ከቤትኤል በስተደቡብ ባለውም ወርካ ሥር ተቀበረች፤ ስለዚህም ያ ዛፍ አሎን ባኩት ተባለ። 9 ያዕቆብ ከመስጴጦምያ በተመለሰ ጊዜ እግዚአብሔር ዳግመኛ ተገለጠለትና ባረከው። 10 ደግሞም “ስምህ ያዕቆብ ነው፤ ከእንግዲህ ወዲህ ግን እስራኤል ትባላለህ እንጂ ያዕቆብ ተብለህ አትጠራም” አለው። ስለዚህም እግዚአብሔር ያዕቆብን “እስራኤል” ብሎ ጠራው። 11 ደግሞም እግዚአብሔር ያዕቆብን እንዲህ አለው፦ “ሁሉን ቻይ አምላክ እኔ ነኝ፤ ብዙ ልጆች ይኑርህ፤ ዘርህም ይብዛ፤ የብዙ ሕዝብ አባት ሁን፤ ነገሥታትም ከአንተ ይወለዱ። 12 ለአብርሃምና ለይስሐቅ የሰጠሁትን ምድር ለአንተም እሰጥሃለሁ፤ ይህንኑ ምድር ከአንተም በኋላ ለዘርህ እሰጣለሁ።” 13 እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ከተነጋገረ በኋላ ከዚያ ስፍራ ወደ ላይ ወጣ። 14 ያዕቆብም፥ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር በተነጋገረበት ስፍራ መታሰቢያ የሚሆን የተቀደሰ ዐምድ አቆመ፤ የወይን ጠጅና ዘይት በላዩ አፈሰሰበት፤ 15 ያዕቆብ፥ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር የተነጋገረበትን ይህንኑ ስፍራ “ቤትኤል” ብሎ ጠራው። የራሔል ሞት 16 ያዕቆብና ቤተሰቡ ከቤትኤል ለቀው ሄዱ፤ ወደ ኤፍራታ ሊደርሱ ጥቂት ሲቀራቸው የራሔል መውለጃ ጊዜ ደረሰና በከባድ ምጥ ተያዘች። 17 ምጧ እየበረታ በሄደ ጊዜ አዋላጅዋ “ራሔል ሆይ፥ ሌላ ወንድ ልጅ መውለድሽ ስለ ሆነ አይዞሽ አትፍሪ” አለቻት። 18 እርስዋ ግን ልትሞት ታጣጥር ስለ ነበር ከመሞቷ በፊት ልጅዋን “ቤንኦኒ” አለችው፤ አባቱ ግን “ብንያም” አለው። 19 ከዚህ በኋላ ወዲያውኑ ራሔል ሞተች፤ አሁን ቤተ ልሔም ተብሎ በሚጠራው ወደ ኤፍራታ በሚወስደው መንገድ ዳር ተቀበረች። 20 ያዕቆብም በራሔል መቃብር ላይ ለመታሰቢያዋ የሚሆን የድንጋይ ሐውልት አቆመ። ይህም ሐውልት እስከ ዛሬ ድረስ የራሔልን መቃብር ያመለክታል። 21 ያዕቆብ ጒዞውን ቀጥሎ በዔዴር ግንብ ባሻገር ድንኳን ተክሎ ሰፈረ። የያዕቆብ ልጆች ( 1ዜ.መ. 2፥1-2 ) 22 ያዕቆብ በዚያ ምድር ሲኖር ሳለ፥ ሮቤል ወደ አባቱ ቁባት ወደ ባላ ገባ። ያዕቆብም ይህን ነገር ሰማ። የያዕቆብ ወንዶች ልጆች ዐሥራ ሁለት ናቸው። 23 የልያ ልጆች፥ የያዕቆብ የመጀመሪያ ልጅ ሮቤል፥ ስምዖን፥ ሌዊ፥ ይሁዳ፥ ይሳኮርና ዛብሎን ናቸው። 24 የራሔል ልጆች፥ ዮሴፍና ብንያም ናቸው። 25 የራሔል አገልጋይ የነበረችው የባላ ልጆች፥ ዳንና ንፍታሌም ናቸው። 26 የልያ አገልጋይ የነበረችው የዚልፋ ልጆች ጋድና አሴር ናቸው። እነዚህ ወንዶች ልጆች ያዕቆብ በመስጴጦምያ ሳለ የተወለዱለት ናቸው። የይስሐቅ ሞት 27 ያዕቆብ በኬብሮን አጠገብ መምሬ ወደምትባል ስፍራ ወደሚኖረው አባቱ ወደ ይስሐቅ ሄደ፤ ይህም ስፍራ አብርሃምና ይስሐቅ የኖሩበት ነው። 28 ይስሐቅ መቶ ሰማኒያ ዓመት ኖረ፤ 29 ዕድሜ ጠግቦ ካረጀ በኋላ ሞተ፤ ልጆቹም ዔሳውና ያዕቆብ ቀበሩት። |