ዘፍጥረት 34 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምየያዕቆብ ሴት ልጅ የዲና መደፈር 1 ከዕለታት አንድ ቀን ልያ ለያዕቆብ የወለደችለት ዲና በዚያ አካባቢ የሚኖሩትን ከነዓናውያት ሴቶች ለማየት ወጣች፤ 2 የአገሩ ገዢ የሒዋዊው የሐሞር ልጅ ሴኬም ባያት ጊዜ ያዛት፤ በማስገደድም ክብረ ንጽሕናዋን ደፈረ። 3 በውበቷ ተማርኮ እጅግ ወደዳት፤ እርስዋም እንድትወደው ለማድረግ በፍቅር ቃል አነጋገራት። 4 አባቱንም “ከዚህች ልጅ ጋር አጋባኝ” አለው። 5 ያዕቆብ ልጁ ዲና ክብረ ንጽሕናዋ እንደ ተደፈረ ሰማ፤ ነገር ግን ወንዶች ልጆቹ የከብት መንጋ ይዘው ተሰማርተው ስለ ነበር፥ እነርሱ እስከሚመጡ ዝም ብሎ ቈየ፤ 6 ከዚህ በኋላ የሴኬም አባት ሐሞር፥ ያዕቆብን ለማነጋገር ወጣ፤ 7 ልክ በዚያኑ ጊዜ የያዕቆብ ልጆች ከተሰማሩበት መጡ፤ ስለ ተፈጸመው ድርጊት በሰሙ ጊዜ እጅግ ደነገጡ፤ ይህ ነገር መደረግ ስላልነበረበት ሴኬም የያዕቆብን ልጅ በመድፈር የእስራኤልን ሕዝብ በማዋረዱም እጅግ ተቈጡ። 8 ሐሞር ግን እንዲህ አላቸው፤ “ልጄ ሴኬም ልጃችሁን በጣም ወዶአታል፤ ስለዚህ እንዲያገባት ፍቀዱለት፤ 9 እንዲያውም በመካከላችን የጋብቻ ውል እናድርግ፤ እኛ የእናንተን ሴቶች ልጆች እናግባ፤ እናንተም የእኛን ሴቶች ልጆች አግቡ። 10 በዚህ ዐይነት በአገራችን ላይ ከእኛ ጋር መኖር ትችላላችሁ፤ በፈለጋችሁበት ስፍራ በመዘዋወር እየሠራችሁና እየነገዳችሁ ርስትም ይዛችሁ መኖር ትችላላችሁ።” 11 ሴኬምም፥ በበኩሉ የዲናን አባትና ወንድሞችዋን እንዲህ አላቸው፤ “ሐሳቤን ብትፈጽሙልኝ የምትፈልጉትን ሁሉ አደርጋለሁ፤ 12 ለሙሽራዋም ጥሎሽ የፈለጋችሁትን ያኽል ጠይቁኝ፤ እርስዋን እንዳገባ ፍቀዱልኝ እንጂ፥ የፈለጋችሁትን ሁሉ ለመስጠት ዝግጁ ነኝ።” 13 ሴኬም እኅታቸውን ዲናን አስነውሮ ስለ ነበር የያዕቆብ ልጆች ለእርሱና ለአባቱ ለሐሞር በተንኰል እንዲህ ሲሉ መለሱላቸው፤ 14 “እኅታችንን ያልተገረዘ ሰው እንዲያገባት አንፈቅድም፤ ይህ ለእኛ ታላቅ ውርደት ነው፤ 15 እርስዋን ለመስጠት የሚያስችለን አንድ መንገድ ብቻ አለ፤ ይኸውም አንተና የአገርህ ወንዶች ሁሉ እንደኛ የተገረዛችሁ እንደ ሆነ ነው። 16 እንዲህ ከሆነ እናንተ የእኛን ሴቶች ልጆች ታገባላችሁ፤ እኛም የእናንተን ሴቶች ልጆች እናገባለን፤ አንድ ሕዝብ ሆነንም አብረን እንኖራለን። 17 ሐሳባችንን ባትቀበሉና ባትገረዙ ግን እኅታችንን ይዘን እንሄዳለን።” 18 ይህም አባባል ለሐሞርና ለልጁ ለሴኬም መልካም መስሎ ታያቸው፤ 19 ሴኬም፥ የያዕቆብን ልጅ እጅግ ወዶአት ስለ ነበር የተነገረውን ሁሉ ለማድረግ ምንም ጊዜ አልወሰደበትም፤ ከዚህም በላይ በቤተሰቡ ውስጥ እጅግ የተከበረ በመሆኑ የፈለገውን ለማድረግ መብት ነበረው። 20 ስለዚህ ሐሞርና ልጁ ሴኬም በከተማው በር አጠገብ ወዳለው መሰብሰቢያ ቦታ ሄዱ፤ ለከተማይቱ ነዋሪዎች እንዲህ በማለት ንግግር አደረጉ፤ 21 “እነዚህ ሰዎች ከእኛ ጋር የሚኖሩት በሰላም ነው፤ በምድሪቱ ላይ አብረውን ይቀመጡ፤ በነጻም ይዘዋወሩባት፤ እነሆ፥ ምድሪቱ ለእኛም ለእነርሱም ትበቃናለች፤ የእነርሱን ሴቶች ልጆች እናግባ፤ የእኛንም ሴቶች ልጆች እንዳርላቸው። 22 ሆኖም እነዚህ ሰዎች አብረውን ለመኖርና ከእኛም ጋር አንድ ሕዝብ ለመሆን ፈቃደኞች የሚሆኑት ወንዶች የሆንን ሁሉ እንደ እነርሱ ለመገረዝ የተስማማን እንደ ሆነ ነው። 23 እንዲህ ብናደርግ መንጋዎቻቸውና ከብቶቻቸው፥ ሌላውም ንብረታቸው ሁሉ የእኛ ይሆን የለምን? ስለዚህ ከእነርሱ ጋር ስምምነት እናድርግ፤ እነርሱም ከእኛ ጋር ይኑሩ።” 24 የከተማይቱ ነዋሪዎች ሁሉ ሐሞርና ሴኬም ባቀረቡት ሐሳብ ተስማምተው ወንዶች ሁሉ ተገረዙ። የዲና ወንድሞች በቀል 25 በሦስተኛው ቀን ሰዎቹ ገና ከመገረዝ ቊስል ሳይድኑ ከያዕቆብ ልጆች መካከል ሁለቱ የዲና ወንድሞች ስምዖንና ሌዊ ሰይፍ፥ ሰይፋቸውን ይዘው ማንም ሳያውቅባቸው፥ ወደ ከተማ ገቡና ወንዶቹን ሁሉ ገደሉ። 26 ሐሞርንና ልጁን ሴኬምን ሳይቀር በሰይፍ ከገደሉ በኋላ፥ ዲናን ከሴኬም ቤት ወስደው ሄዱ። 27 የቀሩትም የያዕቆብ ልጆች ወደሞቱት ሰዎች ቤት እየገቡ እኅታቸው የተደፈረችበትን ከተማ በሙሉ ዘረፉ። 28 የበግና የፍየል መንጋዎቻቸውን፥ ከብቶቻቸውን፥ አህዮቻቸውንና በከተማና ከከተማ ውጪ የነበራቸውን ንብረት ሁሉ ዘርፈው ወሰዱ። 29 ሴቶችንና ሕፃናትን ማረኩ፤ በየቤቱ ያገኙትን ሀብት ሁሉ ዘረፉ። 30 ያዕቆብ ስምዖንንና ሌዊን እንዲህ አላቸው፤ “በእኔ ላይ ከባድ ችግር አመጣችሁብኝ፤ እነሆ በዚህ ድርጊት የተነሣ በዚህች ምድር የሚኖሩ ከነዓናውያንና ፈሪዛውያን ይጠሉኛል፤ እኛ በቊጥር አነስተኞች ነን፤ እነርሱ ተባብረው ቢያጠቁን እኔና ቤተሰቤ እንጠፋለን።” 31 እነርሱ ግን “እኅታችን እንደ አመንዝራ ሴት ትደፈርን?” አሉ። |