Biblia Todo Logo
La Biblia Online

- Anuncios -


መክብብ 9 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም

1 ስለ ነዚህ ሁሉ ነገሮች ለረጅም ጊዜ በብርቱ ካሰብኩ በኋላ የደጋግና የጥበበኞች ሰዎችን ሥራ በእግዚአብሔር እጅ እንደ ሆነ ተረዳሁ፤ ስለዚህ ወደፊት የሚገጥመውን ነገር ፍቅርም ሆነ ጥላቻ አስቀድሞ የሚያውቅ ሰው የለም።

2 ምንም ዐይነት ልዩነት ሳይደረግ ለጻድቅና ለኃጢአተኛ ለደግና ለክፉ፥ ለንጹሓንና ንጹሓን ላልሆኑ መሥዋዕት ለሚያቀርቡትና ለማያቀርቡትም የሚገጥማቸው ዕድል አንድ ዐይነት ነው፤ ይኸውም ደጉ ሰው ከኃጢአተኛው የተሻለ ዕድል የለውም፤ መሐላን የሚፈራው መሐላን ከሚደፍረው ሰው ተለይቶ አይታይም።

3 የሁሉም ዕድል ፈንታው አንድ ዐይነት ነው፤ ይህም በዓለም እንደሚደረገው እንደማንኛውም ነገር ሁሉ እጅግ የከፋ ነው፤ ሰዎችም በሚኖሩበት ዘመን ሁሉ አእምሮአቸው በክፋትና በእብደት የተሞላ ሆኖ በመጨረሻ ይሞታሉ።

4 ከሞተ አንበሳ ይልቅ በሕይወት ያለ ውሻ ይሻላል፤ በሕያዋን ምድር የሚኖር ሰው የተሻለ ተስፋ አለው፤

5 በሕይወት ያሉ ሰዎች አንድ ቀን እንደሚሞቱ ያውቃሉ፤ ሙታን ግን አንዳች ነገር አያውቁም፤ ፈጽሞ የተረሱ በመሆናቸውም ዋጋ የላቸውም።

6 ፍቅራቸው፥ ጥላቻቸውና ቅናታቸው ሁሉ ከእነርሱ ጋር አብሮ ሞቶአል፤ በዚህ ዓለም በሚሆነው ነገር ሁሉ እንደገና እስከ ዘለዓለም ተካፋይነት አይኖራቸውም።

7 እግዚአብሔር ቀድሞ የፈቀደልህ ይህ በመሆኑ ሂድ፤ ምግብህን ተመግበህ፥ የወይን ጠጅህንም ጠጥተህ በመርካትህ ደስ ይበልህ።

8 ሁልጊዜ ነጭ ልብስ ለብሰህ ጠጒርህን ተቀባ።

9 በዚህ ዓለም እግዚአብሔር በሰጠህ ከንቱ በሆነ ኑሮህ ከምትወዳት ሚስትህ ጋር ደስ ይበልህ፤ ስለ መከራህና ስለ ድካምህ ሁሉ ዋጋ ሆኖ የተሰጠህ ዕድል ፈንታ ይኸው ብቻ ስለ ሆነ ከንቱ ዘመንህን፥ እያንዳንዱን ቀን ተደሰትበት።

10 ባለህ ኀይል ሥራህን ሁሉ በትጋት ፈጽም፤ ወደ ሙታን ዓለም ከወረድህ በኋላ በዚያ ሥራና ሐሳብ፥ ዕውቀትና ጥበብ የለም።

11 በዚህ ዓለም የተመለከትኩት ሌላም ነገር አለ፤ ይኸውም ፈጣን ሯጮች በአሸናፊነት አይወጡም፤ ጀግኖችም በጦርነት ድል አያደርጉም፤ ጠቢባን የዕለት እንጀራን፥ ብልኆች ሀብትን አያገኙም፤ ችሎታ ያላቸውም ሰዎች በማዕርግ አያድጉም፤ ነገር ግን ሁሉንም ጊዜና ዕድል ያጋጥማቸዋል፤

12 ይሁን እንጂ እያንዳንዱ ሰው ይህ መጥፎ ዕድል መቼ እንደሚገጥመው አያውቅም፤ ወፍ በራ በወጥመድ ውስጥ እንደምትገባ፥ ዓሣም በመጥፎ አጋጣሚ በመረብ እንደሚያዝ እንዲሁም የሰው ልጅ ሁሉ ሳያስበው ድንገት በሚደርስበት በክፉ አጋጣሚ ይጠመዳል።


የጥበብ ልዕልና

13 በዚህ ዓለም የተመለከትኩት ሌላም ነገር ደግሞ አለ፤ ይኸውም የጥበብ ታላቅ ምሳሌነት ነው።

14 ጥቂት ሕዝብ የሚኖርባት አንዲት ትንሽ ከተማ ነበረች፤ አንድ ኀይለኛ ንጉሥ አደጋ ሊጥልባት ተነሣ፤ ትልቅ ምሽግ ሠርቶም ከበባት።

15 በዚያች ከተማ የሚኖር ጥበበኛ የሆነ አንድ ድኻ ሰው ከተማይቱን በጥበቡ አዳናት፤ ይሁን እንጂ ያንን ድኻ ማንም አላስታወሰውም።

16 ጥበብ ከኀይል እንደሚበልጥ ተናግሬአለሁ፤ ነገር ግን የድኻ ሰው ጥበብ የተናቀ ነው፤ ለንግግሩም ዋጋ የሚሰጠው የለም።

17 በሞኞች ጉባኤ ከሚሰማው የአገረ ገዥ የጩኸት ድምፅ ይልቅ በዝግታ የሚነገር የጥበበኛ ቃል ይሻላል።

18 ከጦር መሣሪያ ይልቅ ጥበብ ትሻላለች፤ ነገር ግን አንድ ኃጢአተኛ ብዙ መልካም ነገርን ያጠፋል።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos