Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


ዘዳግም 2 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


የእስራኤል ሕዝብ በበረሓ የተንከራተቱባቸው ዓመቶች

1 “እግዚአብሔር በነገረኝ መሠረት ወደ ምድረ በዳ ተመልሰን ወደ ቀይ ባሕር በሚወስደው አቅጣጫ በመጓዝ የኤዶምን ኮረብታማ ቦታ ለብዙ ቀን ዞርን።

2 ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር እንዲህ ሲል ነገረኝ፦

3 ‘በእነዚህ ኮረብታማ አገሮች የተንከራተታችሁበት ጊዜው ረጅም ነው፤ አሁን ግን ወደ ሰሜን አቅጣጫ ሂዱ፤

4 ሕዝቡንም እንዲህ ብለህ እዘዝ፤ ዘመዶቻችሁ የዔሳው ዘሮች በሚኖሩበት በኮረብታማው በኤዶም አገር በኩል ታልፋላችሁ፤ እነርሱ እናንተን ይፈሩአችኋል፤ ነገር ግን ተጠንቀቁ፤

5 የኤዶምን ኮረብታማ አገር ለዔሳው ርስት አድርጌ ስለ ሰጠሁ ከምድራቸው የጫማ መርገጫ ታኽል እንኳ አልሰጣችሁምና በእነርሱ ላይ ጦርነት አታንሡ።

6 የሚያስፈልጋችሁን ምግብና ውሃ በገንዘብ ግዙ።’

7 “በእርግጥ አምላካችሁ እግዚአብሔር በሠራችሁት ሥራ ሁሉ ብዙ በረከት ሰጥቶአችኋል፤ በዚህ በሰፊው በረሓ በሄዳችሁበት ሁሉ ተንከባክቦአችኋል፤ በእነዚህ በአርባ ዓመቶች እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ስለ ነበረ ምንም የጐደለባችሁ ነገር አልነበረም።

8 “ስለዚህም ወንድሞቻችን የዔሳው ዘሮች የሚኖሩበትን የኤዶምን አገር አልፈን ከኤላትና ከኤጽዮንጋብር በሚመጣው መንገድ በአራባ በኩል አድርገን ወደ ሞአብ ምድረ በዳ አቅጣጫ ተመለስን።

9 እግዚአብሔርም እንዲህ አለኝ፤ ‘የሎጥ ዘሮች የሆኑትን ሞአባውያንን አታስቸግሩ፤ ከእነርሱም ጋር ጦርነት ለመግጠም አታነሣሡአቸው፤ የዔርን ከተማ ለእነርሱ መኖሪያ ሰጥቼአለሁ፤ ስለዚህም ከእነርሱ ምድር ምንም አልሰጣችሁም።’ ”

10 [ኤሚም ተብለው የሚጠሩ ብርቱ የሆኑ ብዙ ሕዝብ በዔር ይኖሩ ነበር፤ እነርሱም ግዙፋን እንደ ሆኑት እንደ ዐናቅ ነገዶች ቁመተ ረጃጅሞች ነበሩ።

11 እንደ ዐናቃውያንም ረፋያውያን ተብለው ይጠሩ ነበር። ሞአባውያን ግን ኤሚማውያን ብለው ይጠሩአቸው ነበር።

12 ሖራውያንም በኤዶም ይኖሩ ነበር፤ ነገር ግን የዔሳው ዘሮች ሖራውያንን ነቃቅለው በማባረር በእነርሱ ቦታ ሰፍረውበት ነበር፤ ይኸውም እስራኤላውያን ዘግየት ብለው እግዚአብሔር በሰጣቸው ምድር ላይ እንዳደረጉት ዐይነት መሆኑ ነው።]

13 “ከዚህም በኋላ እግዚአብሔር በነገረን መሠረት የዘሬድን ወንዝ ተሻገርን፤

14 ይህም የሆነው ቃዴስ በርኔን ትተን ከሄድን ከሠላሳ ስምንት ዓመት በኋላ መሆኑ ነው፤ እግዚአብሔር ስለ እነርሱ አስቀድሞ በመሐላ በተናገረው መሠረት ለጦርነት የደረሱ የዚያ ትውልድ ወንዶች ሁሉ አልቀው ነበር።

15 እግዚአብሔርም በሙሉ እስኪደመስሳቸው ድረስ እነርሱን ከመቃወም አልተመለሰም።

16 “እነርሱ ሁሉ ካለቁ በኋላ፥

17 እግዚአብሔር እንዲህ ብሎ ተናገረኝ፦

18 ‘የሞአብ ክልል በሆነው በዔር በኩል ዛሬውኑ ማለፍ አለባችሁ።

19 ከዚህም በኋላ የሎጥ ዘሮች ወደሚኖሩበት ወደ ዐሞናውያን ምድር ትቃረባላችሁ፤ እነርሱንም አታስቸግሩአቸው፤ ወይም ከእነርሱ ጋር ጦርነት ለመግጠም አታነሣሡአቸው፤ ለእነርሱ ከሰጠኋት ምድር ለእናንተ ምንም አልሰጣችሁም።’ ”

20 [ይህም ግዛት በዚያ ይኖሩ በነበሩ ሕዝብ ይጠሩ በነበሩበት ስም የረፋያውያን ምድር ተብሎ ይጠራ ነበር፤ ዐሞናውያን በበኩላቸው ዛምዙሚም ብለው ይጠሩአቸው ነበር።

21 እነርሱም እንደ ዐናቃውያን ቁመተ ረጃጅሞች፥ ብርቱና ብዙ ሕዝብ ነበሩ፤ ነገር ግን በእግዚአብሔር ኀይል ዐሞናውያን ስለ ደመሰሱአቸው ምድራቸውን ወርሰው ራሳቸው ሰፍረውበት ነበር።

22 እግዚአብሔር ኮረብታማ በሆነችው በኤዶም ለሚኖሩት ለዔሳው ዘሮችም እንደዚሁ አድርጎላቸው ነበር፤ ይኸውም ቀድሞ የኖሩባትን ሖራውያንን ደምስሶ እስከ አሁን የሚኖሩባትን ምድራቸውን ኤዶማውያን ወርሰው እንዲሰፍሩባት አድርጎአል።

23 ቀርጤስ ተብላ ከምትጠራ ደሴት የመጡ ሕዝቦች በጋዛ አካባቢ የሚኖሩ ኤዋውያን ተብለው የሚጠሩ ነዋሪዎችን ደምስሰው በእነርሱ ቦታ ሰፈሩ።]

24 “በሞአብ በኩልም ካለፍን በኋላ እግዚአብሔር እንዲህ አለን፦ ‘አሁን ተነሥታችሁ የአርኖንን ወንዝ ተሻገሩ፤ በሐሴቦን ተቀምጦ የሚገዛውን የአሞራውያንን ንጉሥ ሲሖንን ከነምድሩ ለእናንተ አሳልፌ ሰጥቻችኋለሁ፤ እርሱን ወግታችሁ ምድሩን ውረሱ፤

25 ከዛሬ ጀምሮ በየትኛውም ስፍራ የሚኖሩ ሕዝቦች እናንተን እንዲፈሩ አደርጋለሁ፤ ስለ እናንተ በሰሙ ቊጥር ሁሉም በፍርሃት ይንቀጠቀጣሉ።’


የንጉሥ ሲሖን በእስራኤላውያን ድል መመታት
( ዘኍ. 21፥21-30 )

26 “ከዚህም በኋላ የሰላም መልእክት የያዙ መልእክተኞችን ከቅዴሞት በረሓ ወደ ሐሴቦን ንጉሥ ወደ ሲሖን እንዲህ ስል ላክሁ፤

27 ‘በእናንተ አገር በኩል አልፈን እንድንሄድ ፍቀድልን፤ ከመንገዱ ሳንወጣና ወደ ቀኝም ወደ ግራም ሳንል በቀጥታ እንሄዳለን፤

28 ለምንበላው ምግብና ለምንጠጣው ውሃ ዋጋ እንከፍላለን፤ እኛ የምንፈልገው በአንተ አገር በኩል ማለፍ እንዲፈቀድልን ብቻ ነው።

29 በኤዶም የሚኖሩ የዔሳው ዘሮችና በዔር የሚኖሩ የሞአብ ዘሮች በግዛታቸው በኩል እንድናልፍ እንደ ፈቀዱልን ሁሉ የዮርዳኖስን ወንዝ ተሻግረን እግዚአብሔር ወደሚያወርሰን ምድር እስክንገባ ድረስ በዚያ ለማለፍ ፍቀድልን።’

30 “ነገር ግን ሲሖን ንጉሥ ሴዎን በእርሱ ግዛት ውስጥ አልፈን እንድንሄድ ባለመፍቀዱ፥ አሁን እንዳደረገው አምላካችሁ እግዚአብሔር በእጃችሁ አሳልፎ ሊሰጠው ስለ ፈቀደ ትዕቢተኛና እልኸኛ አደረገው።

31 “ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር እንዲህ አለኝ፤ ‘ተመልከት እኔ ንጉሥ ሲሖንንና ምድሩን በእጅህ አሳልፌ ሰጥቼሃለሁ፤ አሁን ድል በማድረግ ምድሩን ወርሰህ ስፈርበት።’

32 ንጉሥ ሲሖንም ያለውን ሰው ሁሉ አሰልፎ በያሐጽ ከተማ አጠገብ ከእኛ ጋር ለመዋጋት ወጣ፤

33 ነገር ግን እግዚአብሔር አምላካችን በእኛ እጅ ስለ ጣለው እርሱንና ልጆቹን፥ ያለውንም ሰው ሁሉ ገደልን።

34 ወዲያውም እያንዳንዱን ከተማ ወረን አቃጠልነው፤ በነዚያ ከተሞች የነበሩትንም ሰዎች ወንዶችንና ሴቶችን፥ ሕፃናትንም ጭምር አንድ እንኳ በሕይወት ሳናስቀር ሁሉንም ደመሰስን።

35 ከብቱን ወሰድን፤ ከተሞችንም በዘበዝን።

36 በአርኖን ሸለቆ ጠረፍ ከምትገኘው ከአሮዔርና በሸለቆው ከሚገኘው ከተማ ጀምሮ እስከ ገለዓድ ድረስ እኛን ሊቋቋመን የሚችል ከተማ አልነበረም፤ አምላካችን እግዚአብሔር ሁሉንም አሳልፎ ሰጠን።

37 ነገር ግን ወደ ዐሞናውያን ግዛት አጠገብ ወይም ወደ ያቦቅ ወንዝ ዳርቻ ወይም ወደ ኮረብታማይቱ አገር ከተሞች ወይም እግዚአብሔር እንዳንደርስባቸው ወዳዘዘን እነዚህን ከመሳሰሉት አገሮች ወደ አንዲቱ እንኳ አልቀረብንም።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos