አሞጽ 1 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም1 ዖዝያን በይሁዳ፥ የዮአስ ልጅ ኢዮርብዓምም በእስራኤል ላይ በነገሡበት ዘመን፥ በተቆዓ ከሚገኙ እረኞች አንዱ የሆነው አሞጽ የምድር መናወጥ ከመሆኑ ሁለት ዓመት በፊት ስለ እስራኤል የተናገረው የትንቢት ቃል ይህ ነው። 2 አሞጽ እንዲህ አለ፦ “እግዚአብሔር በጽዮን ተራራ ሆኖ እንደሚያገሣ አንበሳ የሚያስፈራ ድምፁን ያሰማል፤ ቃሉም ከኢየሩሳሌም ያስተጋባል፤ እረኞች መንጋ የሚያሰማሩበት መስክ ይጠወልጋል፤ በቀርሜሎስ ተራራ የሚገኘውም ልምላሜ ይደርቃል።” የእግዚአብሔር ፍርድ በእስራኤል ጐረቤት አገሮች ላይ ሶርያ 3 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የደማስቆ ሕዝብ ደጋግመው ስለ ሠሩት ኃጢአት ያለ ጥርጥር እቀጣቸዋለሁ፤ እነርሱ የገለዓድን ሕዝብ የብረት ጥርስ ባለው መንኰራኲር አበራይተው አሠቃይተዋቸዋል። 4 በንጉሥ ሐዛኤል ቤተ መንግሥት ላይ እሳት እለቅበታለሁ፤ እሳቱም ንጉሥ ቤንሀዳድ የሠራቸውንም ምሽጎች ያቃጥላል። 5 የደማስቆን ከተማ የቅጽር በር መዝጊያ ሁሉ እሰባብራለሁ፤ በአዌን ሸለቆ የሚኖሩትን ሕዝቦችና የቤትዔደንን መሪ አስወግዳለሁ፤ የሶርያም ሕዝብ ተማርከው ወደ ቂር ይወሰዳሉ።” ፍልስጥኤም 6 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የጋዛ ሕዝብ ደጋግመው ስለ ሠሩት ኃጢአት ያለ ጥርጥር እቀጣቸዋለሁ፤ እነርሱ የሀገሩን ሕዝብ ሁሉ ከማረኩ በኋላ ለኤዶም ሰዎች አሳልፈው ሰጥተዋቸዋል። 7 ስለዚህ በጋዛ ከተማ ቅጽር ላይ እሳት እለቅበታለሁ፤ ምሽጎችዋንም ያቃጥላል፤ 8 በአሽዶድ የሚኖሩትን ሕዝቦችና የአስቀሎናን መሪ አጠፋለሁ፤ የዔቅሮን ከተማ ኗሪዎችንም እቀጣለሁ፤ የተረፉትም ፍልስጥኤማውያን ይሞታሉ።” ጢሮስ 9 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “የጢሮስ ሕዝብ ደጋግመው ስለ ሠሩት ኃጢአት ያለ ጥርጥር እቀጣቸዋለሁ፤ የገቡበትን የወንድምነት ቃል ኪዳን አፍርሰው የማረኳቸውን ሕዝቦች ለኤዶም አሳልፈው ሰጥተዋል፤ 10 ስለዚህ በጢሮስ ከተማ ቅጽር ላይ እሳት እለቅበታለሁ፤ ምሽጎችዋንም ያቃጥላል።” ኤዶም 11 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የኤዶም ሕዝብ ደጋግመው ስለ ሠሩት ኃጢአት ያለ ጥርጥር እቀጣቸዋለሁ፤ እነርሱ ወንድሞቻቸውን እስራኤላውያንን በሰይፍ አሳደዋቸዋል፤ ከያዙአቸውም በኋላ ርኅራኄ አላደረጉላቸውም፤ በእነርሱ ላይ ያላቸው ቊጣ ሊበርድም አልቻለም፤ 12 ስለዚህ በቴማን ከተማ ላይ እሳት እለቅበታለሁ፤ የቦጽራንም ምሽጎች ያቃጥላል።” ዐሞን 13 እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ “የዐሞን ሕዝብ ደጋግመው ስለ ሠሩት ኃጢአት ያለ ጥርጥር እቀጣቸዋለሁ፤ እነርሱ ግዛት ለማስፋፋት ባደረጉት ወረራ በገለዓድ የሚኖሩትን እርጉዞች ሴቶች እንኳ ሆዳቸውን ቀደዋል። 14 ስለዚህ በራባ ከተማ ቅጽር ላይ እሳት እለቅበታለሁ፤ ምሽጎችዋንም ያቃጥላል፤ ከዚህ በኋላ በጦርነቱ ቀን ጩኸትና ሁካታ ይበዛል፤ ጦርነቱም እንደ ዐውሎ ነፋስ ይፈጥናል፤ 15 ንጉሣቸውና መሳፍንቱ ተማርከው ይሄዳሉ።” |