ሐዋርያት ሥራ 5 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምሐናንያና ሰጲራ 1 ሐናንያ የሚባል አንድ ሰው ሰጲራ ከምትባለው ሚስቱ ጋር ሆኖ መሬት ሸጠ፤ 2 ሚስቱም እያወቀች ከመሬቱ ሽያጭ ከፊሉን አስቀረና ከፊሉን አምጥቶ ለሐዋርያት አስረከበ፤ 3 ጴጥሮስ ግን እንዲህ አለው፦ “ሐናንያ ሆይ! በመንፈስ ቅዱስ ላይ እንድትዋሽና ከመሬቱም ሽያጭ ከፊሉን እንድታስቀር ያደረገህ ሰይጣን ስለምን ወደ ልብህ ገባ? 4 ሳትሸጠው በፊት መሬቱ የአንተ አልነበረምን? ከሸጥከውስ በኋላ ገንዘቡ የአንተው አልነበረምን? ታዲያ፥ ይህን ነገር ስለምን በልብህ አሰብክ? የዋሸኸው በእግዚአብሔር ላይ ነው እንጂ በሰው ላይ አይደለም።” 5 ሐናንያ ይህን ቃል በሰማ ጊዜ ወደቀና ሞተ፤ ይህን ነገር የሰሙ ሰዎች ሁሉ እጅግ ፈሩ። 6 ጐልማሶች ተነሥተው አስከሬኑን ከፈኑና ወስደው ቀበሩት። 7 ከሦስት ሰዓት ያኽል በኋላ የሐናንያ ሚስት በባልዋ ላይ የደረሰውን ሁናቴ ሳታውቅ መጣች። 8 ጴጥሮስም “እስቲ ንገሪኝ መሬታችሁን የሸጣችሁት ይህን ለሚያኽል ገንዘብ ነውን?” አላት። እርስዋም “አዎ! ይህን ለሚያኽል ገንዘብ ነው” አለች። 9 በዚህ ጊዜ ጴጥሮስ “የእግዚአብሔርን መንፈስ ለመፈታተን እንዴት ተስማማችሁ? እነሆ! ባልሽን ቀብረው የሚመለሱት ሰዎች በበር ናቸው፤ አንቺንም ወስደው ይቀብሩሻል” አላት። 10 እርስዋም በድንገት በእግሩ ሥር ወደቀችና ሞተች፤ ጐልማሶችም ሲገቡ ሞታ አገኙአትና ወስደው በባልዋ አጠገብ ቀበሩአት። 11 በቤተ ክርስቲያን ሁሉና ይህን ነገር በሰሙ ሰዎች ሁሉ ላይ ታላቅ ፍርሀት ሆነ። በሐዋርያት እጅ የተደረጉ ተአምራትና ድንቅ ነገሮች 12 ብዙ ተአምራትና ድንቅ ነገሮች በሕዝቡ መካከል በሐዋርያት እጅ ይደረጉ ነበር፤ ሁሉም በአንድ ልብ ሆነው በሰሎሞን መመላለሻ ይሰበሰቡ ነበር። 13 ከእነርሱ ውጪ ከሆኑት ሰዎች አንድ እንኳ ከእነርሱ ጋር ለመሆን የሚደፍር አልነበረም፤ ይሁን እንጂ ሕዝቡ ያከብራቸው ነበር። 14 በጌታ የሚያምኑ ወንዶችና ሴቶች ቊጥራቸው በጣም እየበዛ ይሄድ ነበር። 15 ሰዎች ብዙ በሽተኞችን ወደ መንገድ እያወጡ በአልጋ ላይና በቃሬዛ ላይ ያስተኙአቸው ነበር፤ እንዲህም ያደረጉት ጴጥሮስ በዚያ በኩል ሲያልፍ ጥላው እንኳ በአንዳንዶቹ ላይ እንዲያርፍባቸው ነበር። 16 ሰዎች በኢየሩሳሌም ዙሪያ ካሉት ከተሞች በሽተኞቻቸውንና በርኩሳን መናፍስት የሚሠቃዩትን ያመጡ ነበር፤ ሁሉም ይድኑ ነበር። በሐዋርያት ላይ ስደት መነሣቱ 17 የካህናት አለቃውና ከእርሱ ጋር የነበሩት የሰዱቃውያን ወገኖች ሁሉ በቅንነት ተሞልተው በእነርሱ ላይ ተነሡ፤ 18 ሐዋርያትን ያዙና በሕዝቡ ወህኒ ቤት አስገቡአቸው። 19 የእግዚአብሔር መልአክ ግን በሌሊት የወህኒ ቤቱን በሮች ከፍቶ፥ አስወጣቸውና፥ 20 “ሂዱ! በቤተ መቅደስ ቆማችሁ የዚህን ሕይወት ቃል ሁሉ ለሕዝቡ ንገሩ!” አላቸው፤ 21 ሐዋርያቱም ትእዛዙን ተቀብለው በማለዳ ወደ ቤተ መቅደስ ገቡና ማስተማር ጀመሩ። በዚያን ጊዜ የካህናት አለቃውና ከእርሱ ጋር የነበሩት መጥተው የሸንጎውን አባሎችና የአይሁድ ሽማግሌዎችን ሁሉ በአንድነት ሰበሰቡ፤ ሐዋርያትንም እንዲያመጡአቸው ሰዎችን ወደ ወህኒ ቤት ላኩ። 22 የዘብ ኀላፊዎቹ ግን ወደ ወህኒ ቤት ሄደው ሐዋርያትን በዚያ አላገኙአቸውም፤ ተመልሰውም መጡና 23 “የወህኒ ቤቱ በር በጥብቅ ተቈልፎ ጠባቂዎችም በበሩ ፊት ቆመው አገኘናቸው፤ የወህኒ ቤቱን በር በከፈትነው ጊዜ ግን በውስጥ ማንንም አላገኘንም” ብለው ተናገሩ። 24 የቤተ መቅደሱ የዘብ አዛዥና የካህናት አለቆች ይህን በሰሙ ጊዜ “ይህ ነገር ምን ይሆን?” በማለት ግራ ተጋቡ። 25 በዚህ ጊዜ አንድ ሰው መጣና “በወህኒ ቤት ያስገባችኋቸው ሰዎች እነሆ፥ በቤተ መቅደስ ቆመው ሕዝቡን ያስተምራሉ” ብሎ ነገራቸው። 26 ወዲያውኑ የቤተ መቅደሱ የዘበኞች አለቃና ሎሌዎቹ ሄደው አመጡአቸው፤ ያመጡአቸውም በኀይል ሳይሆን በማግባባት ነው፤ ይህንንም ያደረጉት ሕዝቡ በድንጋይ እንዳይወግራቸው በመፍራት ነው። 27 አምጥተውም በሸንጎው ፊት አቆሙአቸው፤ የካህናት አለቃውም እንዲህ ሲል ጠየቃቸው፤ 28 “የኢየሱስን ስም በመጥራት እንዳታስተምሩ በጥብቅ አዘናችሁ ነበር፤ ነገር ግን እነሆ፥ ኢየሩሳሌምን በትምህርታችሁ ሞላችኋት፤ እናንተ ለዚያ ሰው ሞት እኛን ተጠያቂዎች ልታደርጉን ትፈልጋላችሁ።” 29 ጴጥሮስና ሌሎች ሐዋርያት ግን እንዲህ ሲሉ መለሱ፦ “ለሰው ከመታዘዝ ለእግዚአብሔር መታዘዝ ይገባናል፤ 30 የአባቶቻችን አምላክ እናንተ በእንጨት ላይ ሰቅላችሁ የገደላችሁትን ኢየሱስን ከሞት አስነሣው፤ 31 እግዚአብሔር ለእስራኤል ሕዝብ ንስሓንና የኃጢአትን ይቅርታ እንዲሰጥ ኢየሱስን መሪና አዳኝ አድርጎ በቀኙ በክብር እንዲቀመጥ አድርጎታል፤ 32 ስለዚህ ነገር እኛ ምስክሮች ነን፤ እግዚአብሔር ለሚታዘዙት ሁሉ የሰጣቸው መንፈስ ቅዱስም ምስክር ነው።” 33 የሸንጎ አባሎች ይህን በሰሙ ጊዜ በጣም ተቈጥተው ሐዋርያቱን ለመግደል ፈለጉ። 34 ነገር ግን በሕዝቡ ዘንድ የተከበረና የሕግ መምህር የሆነ፥ ገማልያል የተባለ አንድ ፈሪሳዊ የሸንጎ አባል ተነሣና ለጥቂት ጊዜ ሐዋርያቱን ገለል እንዲያደርጉአቸው አዘዘ። 35 ከዚህ በኋላ የሸንጎውን አባሎች እንዲህ አላቸው፦ “የእስራኤል ሰዎች ሆይ! በእነዚህ ሰዎች ላይ በምታደርጉት ነገር ተጠንቀቁ። 36 ከዚህ በፊት ቴዎዳስ የሚባል ሰው ‘እኔ ትልቅ ሰው ነኝ’ ብሎ ተነሥቶ ነበር፤ አራት መቶ የሚያኽሉም ሰዎች ከእርሱ ጋር ተባብረው ነበር። ነገር ግን እርሱ ተገደለ፤ ተከታዮቹ ተበታተኑ፤ ዓላማውም እንዳልነበረ ሆነ። 37 ከዚያም በኋላ የሕዝብ ቈጠራ በተደረገበት ዘመን ገሊላዊው ይሁዳ ተነሥቶ ብዙ ሰዎች እንዲከተሉት አድርጎ ነበር፤ እርሱም ተገደለ፤ የተከተሉትም ሁሉ ተበታተኑ። 38 ስለዚህ አሁንም እኔ የምላችሁ ከነዚህ ሰዎች እንድትርቁና እንድትተዉአቸው ነው፤ ይህ አሳብ ወይም ሥራ ከሰው የመጣ ከሆነ ይጠፋል። 39 ከእግዚአብሔር የመጣ ከሆነ ግን እነርሱን ልታጠፉአቸው አትችሉም፤ እንዲያውም ከእግዚአብሔር ጋር መጣላት ይሆንባችኋል።” እነርሱም የገማልያልን ምክር ተቀበሉ። 40 ከዚህ በኋላ ሐዋርያቱን ወደ እነርሱ ጠርተው አስገረፉአቸው፤ የኢየሱስንም ስም በመጥራት እንዳይናገሩ አዘዙአቸውና ለቀቁአቸው። 41 ሐዋርያት ግን ስለ ኢየሱስ ስም ውርደት ለመቀበል የተገቡ በመሆናቸው ደስ እያላቸው ከሸንጎው ወጥተው ሄዱ፤ 42 በየቀኑም በቤተ መቅደስና በየቤቱም ስለ መሲሑ ስለ ኢየሱስ ማስተማርንና የምሥራች መናገርን አላቋረጡም ነበር። |