2 ሳሙኤል 8 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉምዳዊት በጦርነት የተቀዳጃቸው ድሎች ( 1ዜ.መ. 18፥1-17 ) 1 ጥቂት ዘግየት ብሎም ዳዊት ፍልስጥኤማውያንን ድል አድርጎ በቊጥጥሩ ሥር አደረጋቸው፤ “ሜቴግ አማ” የተባለችውንም ከተማ ከእነርሱ እጅ ወሰደ። 2 ቀጥሎም ንጉሥ ዳዊት ሞአባውያንን ድል አደረገ፤ እስረኞቹ በመሬት ላይ እንዲጋደሙ አድርጎ ከየሦስቱ ሰዎች ሁለት ሁለቱ በሞት እንዲቀጡ አደረገ። ስለዚህም ሞአባውያን የእርሱ ተገዢዎች በመሆን ይገብሩለት ነበር። 3 ከዚያም በኋላ ዳዊት የሶርያ ግዛት የሆነችው የጾባ ንጉሥ የሆነውን የረሖብን ልጅ ሀዳድዔዜርን ድል አደረገ፤ ሀዳድዔዜር ድል በተመታበትም ጊዜ በላይኛው ኤፍራጥስ ወንዝ የሚገኘውን ግዛቱን ለማስመለስ በጒዞ ላይ ነበር። 4 ዳዊትም ከሀዳድዔዜር አንድ ሺህ ሰባት መቶ ፈረሰኞችንና ኻያ ሺህ እግረኛ ወታደሮችን ማረከበት፤ ሠረገላ ለመሳብ የሚያገለግሉ አንድ መቶ ፈረሶችን አስቀርቶ፥ የቀሩትን ፈረሶች በሙሉ ቋንጃቸውን ቈርጦ ከአገልግሎት ውጪ እንዲሆኑ አደረገ። 5 በደማስቆ የሚኖሩ ሶርያውያንም ንጉሥ ሀዳድዔዜርን ለመርዳት ሠራዊት በላኩ ጊዜ ዳዊት አደጋ ጥሎ ኻያ ሁለት ሺህ ጭፍሮችን ገደለ። 6 ከዚያም በኋላ በግዛታቸው ውስጥ የጦር ሰፈሮችን አቋቋመ፤ ሶርያውያንም ለእርሱ ተገዢዎች ሆነው ገበሩለት፤ እግዚአብሔርም ዳዊትን በሄደበት ስፍራ ሁሉ ድልን እንዲቀዳጅ አደረገው። 7 ዳዊት የሀዳድዔዜር መኳንንት ያነገቡአቸውን ከወርቅ የተሠሩ ጋሻዎችን ማርኮ ወደ ኢየሩሳሌም ወሰዳቸው፤ 8 እንዲሁም ንጉሥ ዳዊት ሀዳድዔዜር ከሚያስተዳድራቸው ቤጣሕና ቤሮታይ ተብለው ከሚጠሩት ከተሞች እጅግ ብዙ የሆነ ነሐስ ወሰደ። 9 የሐማት ንጉሥ ቶዒ ዳዊት የሀዳድዔዜርን ሠራዊት በሙሉ ድል ማድረጉን ሰማ። 10 ስለዚህም ንጉሥ ሀዳድዔዜርን ድል በመንሣቱ ሰላምታና የደስታ መግለጫ ያቀርብለት ዘንድ ልጁን ዮራምን ወደ ንጉሥ ዳዊት ላከው፤ ቀደም ሲልም ቶዒ በሀዳድዔዜር ላይ ጦርነት ሲያካሄድ የነበረ ነው፤ ዮራምም ከወርቅ፥ ከብርና ከነሐስ የተሠሩ ልዩ ልዩ ስጦታዎችን ለዳዊት ይዞለት ሄደ። 11-12 ንጉሥ ዳዊትም ድል ካደረጋቸው ከኤዶም፥ ከሞአብ፥ ከዐሞን፥ ከፍልስጥኤምና ከዐማሌቅ ከወሰደው ብርና ወርቅ፥ እንዲሁም ከሀዳድዔዜር ከወሰደው ምርኮ ጋር እነዚህንም ደግሞ ለእግዚአብሔር የተለዩ አደረገ። 13 ዳዊት የጨው ሸለቆ ተብሎ በሚጠራው ስፍራ ዐሥራ ስምንት ሺህ ኤዶማውያንን ገድሎ በተመለሰ ጊዜ ዝነኛ ሆነ፤ 14 በመላው ኤዶም ብዙ የጦር ሰፈሮችን አቋቋመ፤ በዚያም የሚኖሩ ሰዎች የእርሱ ተገዢዎች ሆኑ፤ እግዚአብሔር ዳዊትን በሄደበት ስፍራ ሁሉ ድልን ሰጠው። የዳዊት መንግሥት ሹማምንት 15 በዚህ ዐይነት ዳዊት የመላው እስራኤል ንጉሥ ሆኖ ሕዝቡ ዘወትር ትክክለኛ ፍርድ ማግኘት እንዲችል ጥረት ያደርግ ነበር፤ 16 የጸሩያ ልጅ ኢዮአብ የሠራዊቱ አለቃ ሲሆን የአሒሉድ ልጅ ኢዮሣፍጥ ታሪክ ጸሐፊ ነበር፤ 17 የአሒጡብ ልጅ ሳዶቅና የአብያታር ልጅ አቤሜሌክ ካህናት ነበሩ፤ ሠራያ ደግሞ ጸሐፊ ነበረ፤ 18 የዮዳሄ ልጅ በናያ የዳዊት ክብር ዘብ አዛዥ ነበር፤ የዳዊትም ልጆች አማካሪዎቹ ነበሩ። |