Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


2 ሳሙኤል 5 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


የዳዊት የእስራኤልና የይሁዳ ንጉሥ መሆኑ
( 1ዜ.መ. 11፥1-9 ፤ 14፥1-7 )

1 ከዚህ በኋላ የእስራኤል ነገዶች ሁሉ በኬብሮን ወደነበረው ወደ ዳዊት ሄደው እንዲህ አሉት፦ “እነሆ እኛ የአጥንትህ ፍላጭ፥ የሥጋህ ቊራጭ የሆንን ወገኖችህ ነን።

2 ከአሁን በፊት ሳኦል የእኛ ንጉሥ በነበረ ጊዜ እንኳ በጦርነት እስራኤልን የምትመራ አንተ ነበርክ፤ እንዲሁም ሕዝቡን እስራኤልን እንድትመራና በእስራኤልም ላይ እንድትነግሥ እግዚአብሔር ቃል ገብቶልሃል።”

3 እንግዲህ የእስራኤል መሪዎች ሁሉ በኬብሮን ወደ ነበረው ወደ ዳዊት የመጡት በዚህ ዐይነት ነበር፤ እርሱም ከእነርሱ ጋር በእግዚአብሔር ፊት የቃል ኪዳን ስምምነት አደረገ፤ እነርሱም ቀብተው በእስራኤል ላይ አነገሡት።

4 ዳዊት በነገሠበት ጊዜ ዕድሜው ሠላሳ ዓመት ነበር፤ በጠቅላላ የነገሠበት ዘመን አርባ ዓመት ነበር።

5 ይኸውም በኬብሮን ሳለ በይሁዳ ላይ ሰባት ዓመት ተኩል፥ በኢየሩሳሌም ሆኖ በይሁዳና በመላው እስራኤል ላይ ሠላሳ ሦስት ዓመት ነገሠ።


ዳዊት ኢየሩሳሌምን ድል ማድረጉ

6 ንጉሡና ሰዎቹ ከኢያቡሳውያን ጋር ለመዋጋት በኢየሩሳሌም ላይ ዘመቱ፤ ዳዊት ወደዚያ የማይገባ መስሎአቸው የምድሪቱ ነዋሪዎች ዳዊትን “አንተ ወደዚህ ልትገባ አትችልም፤ ዕውሮችና አንካሶች እንኳ ይመልሱሃል” አሉት።

7 ዳዊት ግን በጽዮን የሠሩትን ምሽጋቸውን ያዘ፤ እርስዋም “የዳዊት ከተማ” ተብላ ተጠራች።

8 በዚያን ቀን ዳዊት አንዲህ አለ፦ “ኢያቡሳውያንን የሚመታ ዳዊት በሚጠላቸው በዕውሮችና በአንካሶች ላይ አደጋ ለመጣል በውሃው መተላለፊያ ይውጣ፤” ስለዚህም ዕውሮችና አንካሶች ወደ ቤተ መንግሥት አይገቡም ተባለ።

9 ዳዊት ምሽጉን ከያዘ በኋላ መኖሪያውን በዚያው ስፍራ አደረገ፤ እርስዋንም “የዳዊት ከተማ” ብሎ ጠራት፤ ከኮረብታው በስተ ምሥራቅ በኩል በዐፈር ከተደለደለው ስፍራ አንሥቶ በኮረብታው ዙሪያ ከተማይቱንም ሠራ።

10 የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ስለ ነበር ዳዊት በየጊዜው እየበረታ ሄደ።

11 የጢሮስ ንጉሥ ኪራም ለዳዊት ቤተ መንግሥት ይሠሩለት ዘንድ አናጢዎች፥ ግንበኞችና የሊባኖስ ዛፍ እንጨት አስይዞ መልእክተኞችን ወደ ዳዊት ላከ።

12 ዳዊትም እግዚአብሔር የእስራኤል ንጉሥ አድርጎ እንዳጸናውና ለሕዝቡም ሲል መንግሥቱን ከፍ እንዳደረገለት ተገነዘበ።

13 ዳዊት ከኬብሮን ወደ ኢየሩሳሌም ከመጣ በኋላ ሌሎች ተጨማሪ ሚስቶችና ቁባቶች እንዲኖሩት አደረገ። ብዙ ወንዶችና ሴቶች ልጆችም ተወልደውለት ነበር፤

14 በኢየሩሳሌምም የተወለዱት ልጆች፥ ሻሙዓ፥ ሾባብ፥ ናታን፥ ሰሎሞን፥

15 ይብሐር፥ ኤሊሹዓ፥ ኔፌግ፥ ያፊዓ፥

16 ኤሊሻማዕ፥ ኤልያዳዕና ኤሊፌሌጥ ነበሩ።


ዳዊት ፍልስጥኤማውያንን ድል ማድረጉ
( 1ዜ.መ. 14፥8-17 )

17 ዳዊት በእስራኤል ላይ መንገሡን ፍልስጥኤማውያን ሰሙ፤ ስለዚህም ሠራዊታቸው ዳዊትን ለመማረክ ገሥግሦ ሄደ፤ ዳዊት የእነርሱን መምጣት በሰማ ጊዜ ወደ ተመሸገ ስፍራ ወረደ፤

18 ፍልስጥኤማውያንም በራፋይም ሸለቆ ሰፍረው ለዝርፊያ ተበታትነው ተሰማሩ።

19 ዳዊትም “በፍልስጥኤማውያን ላይ አደጋ ልጣልባቸውን? ድልንስ ትሰጠኛለህን?” ሲል እግዚአብሔርን ጠየቀ። እግዚአብሔርም “አዎ በእነርሱ ላይ አደጋ ጣልባቸው! እኔ በእነርሱ ላይ ድልን እሰጥሃለሁ!” ሲል መለሰለት።

20 ስለዚህም ዳዊት ወደ ባዓል ፈራጺም ወርዶ ፍልስጥኤማውያንን ድል ካደረገ በኋላ “እግዚአብሔር በጠላቶቼ መካከል እንደ ጐርፍ ሰባብሮ ገባ” አለ፤ ስለዚህም የዚያ ስፍራ ስም “ባዓል ፈራጺም” ተብሎ ተጠራ።

21 ፍልስጥኤማውያን በሸሹ ጊዜ ጣዖቶቻቸውን ጥለው ሄዱ፤ ዳዊትና ተከታዮቹም ማርከው ወሰዱአቸው።

22 ከዚህ በኋላ ፍልስጥኤማውያን ወደ ራፋይም ተመልሰው እንደገና ሰፍረው ለዝርፊያ ተሰማሩ።

23 ዳዊትም እንደገና እግዚአብሔርን ጠየቀ፤ እርሱም እንዲህ ሲል መለሰለት “አሁን ካለህበት በኩል በእነርሱ ላይ አደጋ አትጣል፤ ነገር ግን ከወዲያ በኩል በስተ ኋላ በመዞር ከሾላ ዛፎች ፊት ለፊት ሆነህ በእነርሱ ላይ አደጋ ለመጣል ተዘጋጅ።

24 በሾላ ዛፎች ጫፍ ላይ የሰልፍ ድምፅ ስትሰማ በዚያን ጊዜ እግዚአብሔር የፍልስጥኤማውያንን ሠራዊት ለመምታት የወጣ መሆኑን ዐውቀህ ፈጥነህ አጥቃ።”

25 ዳዊትም እግዚአብሔር እንዳዘዘው አደረገ፤ ፍልስጥኤማውያንንም አሸነፈ፤ ከጌባዕ አንሥቶ እስከ ጌዜር ድረስም አባረራቸው።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos