Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


2 ሳሙኤል 20 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


ሼባዕ የፈጸመው ዐመፅ

1 በዚያን ጊዜ ሼባዕ ተብሎ የሚጠራ ጠባዩ የተበላሸ የማይረባ አንድ ሰው በጌልገላ ይኖር ነበር፤ እርሱም ትውልዱ ከብንያም ነገድ ሲሆን አባቱ ቢክሪ ይባላል፤ ይህም ሼባዕ እምቢልታ ነፍቶ “ከዳዊት ጋር ምንም ድርሻ የለንም! ከእሴይ ልጅ ጋር ምንም ዕድል ፈንታ የለንም! የእስራኤል ሕዝብ ሆይ! እያንዳንድህ ወደ ቤትህ ግባ!” ሲል ድምፁን ከፍ አድርጎ ተናገረ።

2 ስለዚህም እስራኤላውያን ዳዊትን ከድተው ከሼባዕ ጋር ሄዱ፤ የይሁዳ ሕዝብ ግን ታማኝነታቸውን በማጽናት ከዮርዳኖስ እስከ ኢየሩሳሌም ዳዊትን ተከትለው ሄዱ።

3 ዳዊት በኢየሩሳሌም ወደሚገኘው ቤተ መንግሥቱ በደረሰ ጊዜ፥ ቤተ መንግሥቱን እንዲጠብቁለት ትቶአቸው የነበሩትን ዐሥር ቊባቶቹን ወደ ሌላ ወስዶ በዘበኛ እንዲጠበቁ አደረገ፤ የሚያስፈልጋቸው ነገር ሁሉ እንዲሰጣቸው አዘዘ፤ ይሁን እንጂ ከእነርሱ ጋር ግንኙነት አልፈጸመም፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ እስከ ዕለተ ሞታቸው በቤት ተወስነው እንደ መበለቶች በመሆን ኖሩ።

4 ንጉሡም ዐማሣን “የይሁዳን ሰዎች ሁሉ ጠርተህ በአንድነት ሰብስብና ከነገ ወዲያ ይዘሃቸው ወደዚህ ተመለስ” አለው።

5 ዐማሣም ሊጠራቸው ሄደ፤ ነገር ግን ንጉሡ በቀጠረው ቀን ተመልሶ ሊመጣ አልቻለም።

6 ስለዚህ ንጉሡ አቢሳን “ሼባዕ ከአቤሴሎም ይበልጥ የከፋ ችግር ይፈጥርብናል፤ ወታደሮቼን ይዘህ ተከታተለው፤ አለበለዚያ የተመሸጉ ከተሞቼን ይዞ ከእኛ እጅ ሊያመልጥ ይችላል” አለው።

7 ስለዚህ የኢዮአብ ወታደሮች፥ የንጉሡ የክብር ዘበኞችና ሌሎች ወታደሮችም ከአቢሳ ጋር ከኢየሩሳሌም ወጥተው የቢክሪን ልጅ ሼባዕን በመከታተል አሳደዱት።

8 በገባዖን ወደሚገኘው ወደ ትልቁ ድንጋይ በደረሱ ጊዜ ዐማሣ አገኛቸው፤ በዚህን ጊዜ ኢዮአብ ሰይፉን በሰገባው ከቶ፥ ሰገባውንም በመታጠቂያው ላይ አስሮ ለጦርነት ተዘጋጅቶ ነበር፤ እየተራመደ ወደ ፊት ሲሄድ ሳለም ሰይፉ ወደቀ፤

9 ኢዮአብም ዐማሣን “ወዳጄ ሆይ! እንደምንድን ነህ?” አለውና የሚስመው በማስመሰል ሪዙን በቀኝ እጁ ያዘ፤

10 ኢዮአብ በሌላው እጁ የያዘውን ሰይፍ ስላላየ ዐማሣ አልተጠነቀቀም ነበርና ኢዮአብ በሆዱ ሻጠበት፤ የሆድ ዕቃውም መሬት ላይ ተዘረገፈ፤ ወዲያውኑ ስለ ሞተም ኢዮአብ በድጋሚ አልወጋውም። ከዚህ በኋላ ኢዮአብና ወንድሙ አቢሳ የቢክሪን ልጅ ሼባዕን ማሳደዳቸውን ቀጠሉ።

11 ከኢዮአብ ወታደሮች አንዱ በዐማሳ ሬሳ አጠገብ ቆሞ “ኢዮአብንና ዳዊትን የምትከተሉ ሁሉ ኢዮአብን ተከተሉ!” ሲል ድምፁን ከፍ አድርጎ ተናገረ።

12 የዐማሳ ሬሳ በደም እንደ ተበከለ በመንገዱ መካከል ተዘርሮ ነበር፤ ያም ሰው የኢዮአብ ወታደር ሁሉ ቆሞ ሲመለከት አይቶ ሬሳውን በመጐተት ወደ እርሻ ወሰደውና በልብስ ሸፈነው።

13 ሬሳው ከመንገዱ መካከል ከተነሣ በኋላ ሰዎች ሁሉ የቢክሪን ልጅ ሼባዕን ለማሳደድ ኢዮአብን ተከትለው ሄዱ።

14 ሼባዕ በእስራኤል ነገዶች ግዛት ሁሉ አልፎ በመሄድ አቤልቤትማዕካ ወደተባለች ከተማ ደረሰ፤ የቢክሪ ጐሣ አባሎች የሆኑ ሁሉ ተሰብስበው ሼባዕን በመከተል ወደ ከተማይቱ ገቡ፤

15 የኢዮአብ ወታደሮች ሼባዕ እዚያ መሆኑን ስለ ሰሙ ሄደው ከተማይቱን ከበቡ፤ በስተውጪ በኩል ቅጽሩን አስደግፈው የዐፈር ቊልል ሠሩ፤ ቀጥሎም ቅጽሩ እንዲወድቅ ከስሩ መቈፈር ጀመሩ።

16 በከተማይቱ ውስጥ የምትኖር አንዲት ብልኅ ሴት በቅጽሩ ላይ ሆና ድምፅዋን ከፍ በማድረግ “ስሙ! ስሙ! ኢዮአብ ወደዚህ ይመጣ ዘንድ ንገሩት፤ እኔ ላነጋግረው እፈልጋለሁ!” አለች።

17 ኢዮአብ ወደዚያ በሄደ ጊዜም ሴትዮዋ “ኢዮአብ የምትባለው አንተ ነህን?” ስትል ጠየቀችው። እርሱም “አዎ እኔ ነኝ” አላት። እርስዋም “ጌታዬ፥ እስቲ አድምጠኝ” አለችው፤ እርሱም “እነሆ፥ አዳምጥሻለሁ” አላት።

18 እርስዋም እንዲህ አለችው፤ “በድሮ ዘመን ‘ወደ አቤል ከተማ ሄዳችሁ የጥያቄአችሁን መልስ ከዚያ ታገኛላችሁ’ ይባል ነበር፤ ሰዎችም የሚያደርጉት ይህንኑ ነበር።

19 የእኔ ከተማ ግን ታላቅ ከተማ ናት፤ በእስራኤል ሰላም የሰፈነባትና ታማኝ ከተማ እርስዋ ናት፤ ታዲያ፥ አንተ ይህችን ከተማ ለመደምሰስ ለምን ታቅዳለህ? የእግዚአብሔር ርስት የሆነውን ነገር ለማፍረስ ትፈልጋለህን?”

20 ኢዮአብም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “እኔ ከተማችሁን አልደመስስም! ከቶም አላፈርስም!

21 የእኛ ዕቅድ ይህ አይደለም፤ የተራራማው የኤፍሬም አገር ተወላጅ የሆነ ሼባዕ ተብሎ የሚጠራ የቢክሪ ልጅ በንጉሥ ዳዊት ላይ ዐመፅ አስነሥቶአል፤ ብቻ ይህ ሰው ይሰጠኝ እንጂ እኔ ከተማይቱን ለቅቄ እሄዳለሁ።” እርስዋም “ራሱን ቈርጠን በግንብ ላይ እንወረውርልሃለን” አለችው።

22 ይህንንም ዕቅድ በተግባር ለመግለጥ ወደ ከተማይቱ ሕዝብ ሄደች፤ እነርሱም የቢክሪን ልጅ የሺባዕን ራስ ቈርጠው በግንቡ ላይ ለኢዮአብ ወረወሩለት፤ እርሱም ወታደሮቹ ከተማይቱን ለቀው ይወጡ ዘንድ ምልክት እንዲሆን እምቢልታ ነፋ፤ እነርሱም ወደየቤታቸው ተመለሱ፤ ኢዮዓብም ንጉሡን ለማግኘት ወደ ኢየሩሳሌም ሄደ።


የዳዊት ባለሟሎች

23 ኢዮአብ የእስራኤል ሠራዊት አዛዥ ሲሆን፥ የዮዳሄ ልጅ በናያ የዳዊት ክብር ዘብ ኀላፊ ነበር፤

24 አዶኒራም ነጻ አገልግሎት የሚሰጡ ገባሮች ኀላፊ ሲሆን፥ የአሒሉድ ልጅ ኢዮሣፍጥ ታሪክ ጸሐፊ ነበር፤

25 ሱሳ የቤተ መንግሥት ጸሐፊ ሲሆን፥ ሳዶቅና አብያታር ካህናት ነበሩ፤

26 እንዲሁም የያዒር ከተማ ተወላጅ የሆነው ዒራ ከዳዊት ካህናት አንዱ ነበር።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos