Biblia Todo Logo
La Biblia Online
- Anuncios -


2 ሳሙኤል 19 - አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም


የኢዮአብ ዳዊትን መውቀሱ

1 ንጉሥ ዳዊት ስለ ልጁ ስለ አቤሴሎም ሞት በብርቱ አዝኖ በማልቀስ ላይ መሆኑን ኢዮአብ ሰማ፤

2 እንዲሁም ንጉሡ በልጁ ሞት ምክንያት በሐዘን ላይ መሆኑን ስለ ሰሙ ወታደሮቹ ያገኙት የድል አድራጊነት ደስታ በዚያ ቀን ወደ ሐዘን ተለወጠባቸው።

3 ስለዚህ ከጦር ግንባር ተመልሰው ወደ ኋላ እንደሚሸሹ ወታደሮች ድምፃቸውን አጥፍተው በጸጥታ ወደ ከተማይቱ ገቡ፤

4 ንጉሡም ፊቱን ሸፍኖ “ልጄ ሆይ! ልጄ አቤሴሎም! አቤሴሎም ልጄ!” እያለ ድምፁን ከፍ አድርጎ ያለቅስ ነበር።

5 በዚህ ጊዜ ኢዮአብ ወደ ንጉሡ ቤት ሄዶ እንዲህ አለው፤ “የአንተን የወንዶችና የሴቶች ልጆችህን፥ የሚስቶችህንና የቊባቶችህን ሕይወት ያዳኑትን ሰዎች ዛሬ አሳፍረሃቸዋል፤

6 አንተ የሚወዱህን ትጠላለህ፤ የሚጠሉህን ግን ትወዳለህ! ስለ ጦር መኰንኖችህና ስለ ወታደሮችህ ሁሉ ምንም የማይገድህ መሆኑን በግልጥ አሳይተሃል፤ አቤሴሎም በሕይወት ቢኖርና እኛ ሁላችን ብንጠፋ ኖሮ እጅግ እንደምትደሰት ተገንዝቤአለሁ፤

7 ይልቅስ አሁን ተነሥና ወታደሮችህን አበረታታ፤ ይህንን ባታደርግ ግን ነገ ጠዋት ከእነርሱ አንዱ እንኳ ከአንተ ጋር እንደማይሆን በእግዚአብሔር ስም እምልልሃለሁ፤ ይህም በሕይወትህ ከደረሰብህ መከራ ሁሉ እጅግ የከፋ ይሆንብሃል።”

8 ከዚህ በኋላ ንጉሡ ከተቀመጠበት ተነሥቶ በመሄድ በከተማይቱ ቅጽር በር አጠገብ ተቀመጠ፤ ተከታዮቹም እዚያ መሆኑን ሰምተው ሁሉም በዙሪያው ተሰበሰቡ። በዚህን ጊዜ እስራኤላውያን ሁሉ ሸሽተው እያንዳንዱ ወደየቤቱ ሄዶ ነበር፤


ዳዊት ወደ ኢየሩሳሌም ለመመለስ ጒዞ መጀመሩ

9 በመላ አገሪቱም ሕዝቡ እርስ በርስ መጣላት ጀመረ፤ እርስ በርሳቸውም እንዲህ ተባባሉ፦ “ንጉሥ ዳዊት ከጠላቶቻችን እጅ አድኖናል፤ ከፍልስጥኤማውያንም እጅ አውጥቶናል፤ አሁን ግን ከአቤሴሎም ፊት በመሸሽ አገሪቱን ትቶ ሄዶአል።

10 መሪያችን ይሆን ዘንድ አቤሴሎምን ቀብተን አንግሠነው ነበር፤ ነገር ግን እርሱ በጦርነት ላይ ተገደለ፤ ታዲያ፥ ንጉሥ ዳዊትን መልሶ ለማምጣት የሚሞክር ሰው እንዴት ታጣ?”

11 ንጉሥ ዳዊትም እስራኤላውያን እርስ በርሳቸው የተናገሩትን ሰማ፤ ስለዚህም ካህናቱን ሳዶቅንና አብያታርን በመላክ የይሁዳን መሪዎች እንዲህ ብለው እንዲጠይቁአቸው አዘዘ፤ “ንጉሡን ረድታችሁ ወደ ቤተ መንግሥቱ ለመመለስ ስለምን እናንተ የመጨረሻዎቹ ትሆናላችሁ?

12 እናንተ እኮ ለእኔ የሥጋ ዘመዶቼ ናችሁ፤ ታዲያ፥ እኔን መልሶ ለመውሰድ የመጀመሪያዎቹ በመሆን ፈንታ ስለምን የመጨረሻዎቹ ትሆናላችሁ?”

13 እንዲሁም ለዐማሳ ሲናገር “አንተም ለእኔ የሥጋ ዘመድ ነህ፤ ከአሁን ጀምሮ በኢዮአብ ምትክ የሠራዊቴ አዛዥ አደርግሃለሁ፤ ይህንንም ባላደርግ እግዚአብሔር በሞት ይቅጣኝ!” ብላችሁ ንገሩት ሲል አዘዛቸው።

14 የዳዊት አነጋገር የይሁዳ ሕዝብ ሁሉ ለእርሱ ታማኞች እንዲሆኑ አደረጋቸው፤ ስለዚህም ከመኳንንቱ ሁሉ ጋር ተመልሶ እንዲመጣ ላኩበት።

15 ዳዊት በመመለስ ላይ እንዳለም የይሁዳ ሰዎች እስከ ዮርዳኖስ ወንዝ ድረስ ሄደው ተቀበሉት፤ አጅበውም ወንዙን ለማሻገር አስበው እስከ ጌልጌላ ድረስ መጡ፤

16 በዚያኑ ጊዜም የባሑሪም ተወላጅ የሆነው የጌራ ልጅ ብንያማዊው ሺምዒ ከይሁዳ ሰዎች ጋር ንጉሥ ዳዊትን ለመቀበል ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ ፈጥኖ ሄደ፤

17 ከእርሱም ጋር የብንያም ነገድ የሆኑ አንድ ሺህ ሰዎች ነበሩ፤ የሳኦል ቤተሰብ አገልጋይ የነበረው ጺባም ከዐሥራ አምስት ወንዶች ልጆቹና ከኻያ አገልጋዮቹ ጋር መጣ፤ ወደ ዮርዳኖስም ወንዝ እየተጣደፉ ደርሰው በንጉሡ ፊት ቀረቡ።

18 እነርሱም ንጉሡንና ተከታዮቹን በጀልባ አጅበው ወደ ማዶ ለማድረስና ንጉሡ የሚፈልገውን ሁሉ ለማድረግ የዮርዳኖስን ወንዝ ተሻገሩ። ንጉሡ ወንዙን ለመሻገር ሲዘጋጅ ሳለ የጌራ ልጅ ሺምዒ መጥቶ በፊቱ ተዘረጋና እንዲህ አለ፤


ዳዊት ለሺምዒ ይቅርታ ማድረጉ

19 “ንጉሥ ሆይ! ከኢየሩሳሌም ወጥተህ በሄድክበት ቀን ያደረግኹትን በደል እባክህ ይቅር በለኝ፤ ቂም በቀልም አትያዝብኝ፤ ዳግመኛም ስለ እርሱ አታስብ፤

20 ጌታዬ ሆይ! ኃጢአት እንደ ሠራሁ ዐውቃለሁ፤ ዛሬ ግን ከሰሜን የእስራኤል ነገዶች የመጀመሪያው በመሆን አንተን ለመቀበል መጥቼአለሁ።”

21 የጸሩያ ልጅ አቢሳም “እግዚአብሔር ቀብቶ ያነገሠውን ስለተሳደበ ሺምዒ በሞት መቀጣት ይገባዋል” ሲል ተናገረ።

22 ዳዊት ግን አቢሳንና ወንድሙን ኢዮአብን “ይህን አሳብ እንድታቀርቡ የጠየቃችሁ ማን ነው? ችግር ልታመጡብኝ ትፈልጋላችሁን? እነሆ፥ አሁን የእስራኤል ንጉሥ እኔ ነኝ፤ ደግሞም በዛሬው ዕለት ማንም እስራኤላዊ በሞት አይቀጣም” አላቸው።

23 ሺምዒንም “በሞት እንደማትቀጣ ቃል እገባልሃለሁ!” አለው።


ዳዊት ለመፊቦሼት ይቅርታ ማድረጉ

24 ከዚህ በኋላ የሳኦል የልጅ ልጅ መፊቦሼት ንጉሡን ለመቀበል ወረደ፤ ንጉሡ ከኢየሩሳሌም ከወጣበት ጊዜ አንሥቶ አሁን በድል አድራጊነት እስከ ተመለሰበት ጊዜ ድረስ መፊቦሼት እግሩን አልታጠበም፤ ጢሙን አልተላጨም፤ ልብሱንም አላጠበም።

25 መፊቦሼት ከኢየሩሳሌም ተነሥቶ ንጉሡን በሚቀበልበት ስፍራ በደረሰ ጊዜ ንጉሡ “መፊቦሼት ሆይ፥ ስለምን ከእኔ ጋር ሳትሄድ ቀረህ?” አለው።

26 መፊቦሼትም እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ንጉሥ ሆይ፥ እንደምታውቀው እኔ ሽባ ነኝ፤ ከአንተ ጋር ለመሄድ ፈልጌ አገልጋዬን ‘በቅሎዬን ጫንልኝ’ ብለው ከድቶኝ ሄደ፤

27 ንጉሥ ሆይ! እንዲያውም ስለ እኔ በውሸት ለአንተ የነገረህ ጉዳይ አለ፤ ነገር ግን አንተ እንደ እግዚአብሔር መልአክ ስለ ሆንክ መልካም መስሎ የታየህን አድርግ።

28 ንጉሥ ሆይ! የአባቴ ቤተሰብ ሁሉ በሞት መቀጣት የሚገባው ነበር፤ ንጉሥ ሆይ! አንተ ግን በገበታህ ቀርቤ እንድመገብ መብት ሰጠኸኝ፤ ከዚህ የበለጠም ቸርነት እንዲደረግልኝ መጠየቅ አይገባኝም።”

29 ንጉሡም “ከዚህ በላይ ብዙ መናገር አያስፈልግህም፤ አንተና ጺባ የሳኦል ንብረት ለሁለት እንድትካፈሉ ወስኛለሁ” ሲል መለሰ።

30 መፊቦሼትም “ንጉሥ ሆይ! ሁሉንም ሀብት ጺባ ይውሰደው፤ ለእኔ አንተ በሰላም ወደ ቤትህ መመለስህ ብቻ ይበቃኛል” አለ።


ዳዊት ለባርዚላይ ቸርነት ማድረጉ

31 ገለዓዳዊው ባርዚላይ ንጉሡን አጅቦ የዮርዳኖስን ወንዝ ለመሻገር ከሮገሊም መጣ፤

32 ባርዚላይ ሰማኒያ ዓመት የሞላው ሽማግሌ ሰው ነበር፤ በጣም ሀብታም ከመሆኑም የተነሣ ንጉሥ ዳዊት በማሕናይም በነበረበት ጊዜ ይኸው ባርዚላይ ምግብ ያቀርብለት ነበር፤

33 ንጉሡም ባርዚላይ “ከእኔ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም ና፤ እኔም በተድላና በደስታ እንድትኖር አደርግሃለሁ” አለው።

34 ባርዚላይ ግን እንዲህ ሲል መለሰ፤ “ንጉሥ ሆይ! ከእንግዲህ ወዲያ ብዙ ዘመን አልኖርም፤ ታዲያ፥ ከአንተ ጋር ወደ ኢየሩሳሌም መሄድ ምን ያስፈልገኛል?

35 እነሆ፥ እኔ አሁን የሰማንያ ዓመት ሰው ነኝ፤ የሚያስደስቱና የማያስደስቱ ነገሮችን መለየት እችላለሁን? የምበላውንም ሆነ የምጠጣውን ጣዕም መለየት እችላለሁን? ጆሮዬም የወንድና የሴት ዘፋኞችን ድምፅ መስማት ይችላልን? ንጉሥ ሆይ! በጌታዬ ላይ ለምን ተጨማሪ ሸክም እሆንብሃለሁ?

36 ደግሞም ንጉሡ ይህን ያኽል ታላቅ ወሮታ የሚከፍለኝ ለምንድን ነው? ነገር ግን የዮርዳኖስን ወንዝ ተሻግሬ ከአንተ ጋር ጥቂት መንገድ ብቻ እሄዳለሁ።

37 ከዚያም በኋላ እኔ አገልጋይህ ወደ ቤቴ ተመልሼ እንድሄድና በወላጆቼ መቃብር አጠገብ እንዳርፍ ፍቀድልኝ፤ እነሆ፥ ይህ ልጄ ኪምሀም ያገለግልሃል፤ ንጉሥ ሆይ! እርሱን ይዘኸው ሂድ፤ የወደድከውንም ለእርሱ አድርግለት።”

38 ንጉሡም “እርሱን ይዤ እሄዳለሁ፤ እንዳደርግለት የምትፈልገውንም ሁሉ አደርግለታለሁ፤ ለአንተም ቢሆን የምትጠይቀውን ሁሉ እፈጽማለሁ” አለው።

39 ከዚህ በኋላ ዳዊትና ተከታዮቹ ሁሉ የዮርዳኖስን ወንዝ ተሻገሩ፤ ዳዊትም ባርዚላይን ሳመውና ባረከው፤ ባርዚላይም ወደ ቤቱ ተመልሶ ሄደ።


የይሁዳና የእስራኤል ሕዝብ ስለ ንጉሥ ዳዊት መከራከራቸው

40 ንጉሥ ዳዊት በይሁዳ ሕዝብ ሁሉና በእስራኤል ሕዝብ እኩሌታ ታጅቦ ወንዙን ከተሻገረ በኋላ ወደ ጌልጌላ አቀና፤ ኪምሀምም አብሮት ተሻገረ፤

41 ከዚህ በኋላ እስራኤላውያን ሁሉ ወደ ንጉሡ ቀርበው “ንጉሥ ሆይ! ወንድሞቻችን የይሁዳ ሰዎች አንተን ወስደው የራሳቸው ለማድረግ፥ እንዲሁም አንተንና ቤተሰብህን፥ ተከታዮችህንም ሁሉ አጅበው የዮርዳኖስን ወንዝ ለማሻገር መብት እንዳላቸው ስለምን ያስባሉ?” ሲሉ ጠየቁት።

42 የይሁዳም ሰዎች “እኛ ይህን ያደረግነው ንጉሡ የእኛ ወገን ስለ ሆነ ብቻ ነው፤ ታዲያ፥ እናንተስ በዚህ ነገር ስለምን ትቈጣላችሁ? እርሱ ለምግባችን ምንም የከፈለን ነገር የለም፤ ሌላም ምንም ነገር አልሰጠንም” ሲሉ መለሱላቸው።

43 እስራኤላውያንም “እርሱ የእናንተ ወገን ቢሆንም እንኳ እናንተ ከምትፈልጉት ይበልጥ እኛ እንፈልገዋለን፤ ከመንግሥቱ ዐሥሩ እጅ የሚገባው ለእኛው ነው፤ እናንተ እኛን የምትንቁት ስለምንድን ነው? ንጉሡን ስለ መመለስ በመጀመሪያ ጥያቄ ያቀረብነው እኛ መሆናችንን ልትዘነጉ አይገባም!” አሉአቸው። ነገር ግን ከእስራኤል ሰዎች ይልቅ የይሁዳ ሰዎች ዳዊትን የራሳቸው ለማድረግ በብርቱ ተከራከሩ።

© The Bible Society of Ethiopia, 2005

© የኢትዮጵያ መጽሐፍ ቅዱስ ማኅበር፥ 1997

Bible Society of Ethiopia
Síguenos en:



Anuncios


¡Síguenos en WhatsApp! Síguenos